በዳንጎቴ ሰራተኞች ግድያ ከ15 በላይ ጥይቶች ተተኩሰዋል

የዲፕ ካማራ እና የሹፌራቸው አስክሬን (ግራ) እና ሲጓዙበት የነበረው መኪና (ቀኝ)
አጭር የምስል መግለጫ የዲፕ ካማራ እና የሹፌራቸው አስክሬን (ግራ) እና ሲጓዙበት የነበረው መኪና (ቀኝ)

የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ሰዎች በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው አለፈ።

ትናንት ማምሻውን ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ መኖሪያቸው አዲስ አበባ ከተማ እየተጓዙ ሳሉ ማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ሁለት ግለሰቦች በመኪናው ላይ ተኩስ በመከፈቱ ስራ አስኪያጁን ጨምሮ አብረዋቸው ሲጓዙ የነበሩት ጸሃፊያቸውን እና ሹፌሩ ተገድለዋል።

የዓይን እማኞች እንደነገሩን ከሆነ ህንዳዊ ዜግነት ያለቸው ዲፕ ካማራ ሲጓዙበት የነበረው ቶዮታ ላንድክሩዘር መኪና አካባቢ ወደ 17 የሚሆኑ የጥይት ቀለሃዎች አይተዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በቦታው ላይ የተገኙ የዓይን እማኞቹ እንደሚሉት ከሆነ ሲጓዙበት የነበረው መኪናው ተጋጭቶ እንደቆመ ምልክቶች ያሳያሉ። ጥቃት አድራሾቹ ዲፕ ካማራን በ7 ጥይት በመምታት ገድለዋል።

የአድዓ በርጋ የኦህዴድ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ድሪርሳ ታደሰ ደግሞ በስራ አስኪያጁ እና በሁለቱ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃቱ የተሰነዘረው ጋቲራ ተብሎ በሚጠራ ቦታ እንደሆነ ጠቅሰው ግለሰቦቹን ለመግደል ቢያንስ 15 ጥይቶች ተተኩሷል ብለዋል።

አቶ ድሪርሳ ''የድርጅቱ ሹፌሮች ከአስተዳደሩ ጋር አለመግባባት ውስጥ ቆይተው ላለፉት ወራት ስራ ላይ አልነበሩም። ከዚህ በተጨማሪም ከፋብሪካው ጋር አብረው ከሚሰሩ ኤጀንሲዎች ጋርም የተለመዱ የሚባሉ አይነት አለመጋባባቶች እንደነበሩ እናውቃለን።'' ብለዋል።

Image copyright Facebook
አጭር የምስል መግለጫ ዲፕ ካማራ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካን ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ አስተዳድረዋል

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፋብሪካው ሰራተኛ ለቢቢሲ እንዳሉት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከባድ ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች ላይ ጥቃት ተሰንዝሮ እንደነበር አስታውሰው፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዲፕ ካማራን ጨምሮ የፋብሪካው ሃላፊዎች ከአካባቢው ማህበረሰበ ጋር ባካሄዱት ተደጋጋሚ ውይይት በፋብሪካው እና በአካባቢው ማህብረሰብ ዘንድ መልካም የሚባል ግንኙነት ተፍጥሮ ነበር።

የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ያስተዳደሩት ዲፕ ካማራ በአከባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ተወዳጅ ናቸው፤ የቅጽል ስምም ወጥቶላቸው ነበር ሲሉ የፋብሪካው ሰራተኛ ነግረውናል።

በተያያዘ ዘገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በግለሰቦቹ ላይ በተፈፀመው ግድያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እጅግ ማዘናቸውንና መንግሥታቸው በወንጀሉ ፈፃሚዎች ላይ ምርመራ በማድረግ ጉዳዩን ለፍትህ እንደሚያቀርቡ አስታወቀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች