"እንደምፈታ ያወቅኩት ባለፈው መስከረም ነበር" አንዷለም አራጌ

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
“ኢትዮጵያ የሚያስፈጋት ስር ነቀል ለውጥ ነው። 27 ዓመት ከበቂ በላይ ነው።” - አንዷለም አራጌ

የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ መስራች እና ሊቀ-መንበር አንዷለም አራጌ ከስድስት ዓመታት ተኩል እስር በኋላ ባለፈው የካቲት ወር ከተፈታ ከወራት በኋላ በአውሮፓ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል። ጉዞውን ከማድረጉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገው አንዷለም ወደ ተቃውሞ ፖለቲካ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን እና አዲስ ፓርቲ የመመሥረት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግሯል።

ረዥም ጊዜ ተለይቶ ለብቻው በመታሰሩ ለዓመታት የሰው ዐይን ሲራብ መቆየቱን የሚገልፀው አንዷለም፤ ዛሬ በወዳጅ በአድናቂዎች ተከብቦ በሰው ፍቅር እየተካሰ ይመስላል።

"አጋጣሚ ኖሮኝ በዚህ ህዝብ መሃል መንከላወሱ፤ መመላለሱ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው" ይላል አንዷለም።

ቢሆንም ግን ከእስር እንደወጣ ወዲያው በተቃውሞ ፖለቲካ እንዲሁም በፅሁፍ ሥራዎች የመጠመድ ሃሳቡ እንዳልተሳከለት አይደብቅም።

ለዚህ አንድም መፈታቱን ተከትሎ የነበረው የጠያቂና የጎብኝ ብዛት የሚያፈናፍን ስላልነበር፥ በሌላ በኩል ደግሞ ከእስር በኋላ ካለው ህይወት ጋር መለማመድ የራሱን ፈተናዎች ይዞ በመምጣቱ ምክንያት እንደሆነ ይገልፃል።

በእስር ቤት ቆይታው ህይወቱን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች መትሮ ይመራ እንደነበር ይናገራል አንዷለም።

"ማንዴላ እንዳሉት የአሳሪው ዓላማ ታሳሪውን በአካልም በመንፈስም ሰብሮ ማውጣት ነው፤ የታሳሪው ዓላማ ደግሞ በአካልም በመንፈስም ጠንክሮ መውጣት ነው። ይህ ለረጅም ጊዜ የእኔ መርኅ ነበር። በአካል በመንፈስም ለመጠንከር የሚረዱኝ ነገሮች ነበሩኝ፤ የተከፋፈለ ህይወት ነበረኝ።" በማለት ህይወቱ በፀሎት፣ በአካላዊ እንቅስቃሴ እና በማንበብ እንዲሁም ዘወትራዊ ክንውኖችን በመፈፀም ያሳልፍ እንደነበር ይናገራል።

በዚህ መልኩ ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ ወደ ውጪው ዓለም መቀላቀል የራሱ ግርታዎች እንደነበሩት ለቢቢሲ ተናግሯል።

"እንደምፈታ ያወቅኩት ባለፈው መስከረም ነበር"

ከእስር ከመፈታቱ ስድስት ወራት ቀደም ብሎ ጉዳዩም ጎልቶ መስተዋል ከመጀመሩ በፊት እንደሚፈታ እርግጠኛ ሆኖ እንደነበርና ራሱን አዘጋጅቶ፣ ሻንጣውንም ሸክፎ እንደነበርም ይገልፃል።

ከዚያ ቀደም በነበረው የእስር ቆይታ በመንግሥት ቀናኢነት ላይ የነበረው ጥርጣሬ እፈታለው የሚል ሃሳብ እንዳይኖረው አድርጎት ነበር።

"የተፈረደብኝን የዕድሜ ልክ እስራት ለመጨረስ ተዘጋጅቼ ነበር። ምንም እንኳ የማይገባኝን ዋጋ ከነልጆቼ ለዓመታት ብከፍልም፤ የገዥው መንግሥት ልሂቃን ፈርጣ እጆች እስካልላሉ ድረስ ለሌሎች ማስፈራሪያ ለማድረግ ሲሉ እስር ቤት ሊያቆዩኝ እንደሚችሉ አምን ነበር። ነገር ግን ምንም እንኳ ከባድ ቢሆንም ይቅርታ በመጠየቅ ልጆቼን አንገት የሚያስደፋ፥ ማኅበራዊ ልዕልና የሚያሳጣ ነገር ላለማድረግ ወስኜ ነበር።"

ታዲያ እነዴት እርግጠኛ ሊሆን ቻለ? ለዚህ ምክንያታዊ መልስ እንደሌለው ይናገራል፤ "እንዲሁ ቀልቤ፥ ደመነብሴ ነው የነገረኝ። የአምላክ መንገድ ብዙ ነውና በራሱ መንገድ እንደሚያወጣኝ አምን ነበር።"

አንዷለም የእስር ቆይታው እየገፋ ሲሄድ የመዘንጋት ስጋት በርትቶብኝ ነበር ይላል። "ፓርቲዬ ፈርሷል፤ ሰውም ረስቶኛል ብየ አስብ ነበር፤ ጊዜው ስለረዘመ ሰዎች የረሱኝ ይመስለኝ ነበር።"

በእስር ቤት ዋነኛ የመረጃ ምንጮቹ ብሄራዊውና ክልላዊው የመንግስት የቴሌቭዥንጣብያዎች ነበሩ።ከጣቢያዎቹ የሚያገኛቸው መረጃዎች ስለ አገሪቷ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ሙሉ እውነታ ባይሰጡትም ከጠያቂ ዘመድ ወዳጆች ግርድፍ መረጃዎችን ያገኝ እንደነበር ይገልፃል።

"እንዲያም ቢሆን ከእስር ስወጣ ያስተዋልኩት ነገር ከጠበቅኩት እጅግ የላቀ ነው" ይላል።

"እኔ ስታሰር የነበረችው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው በፍርሃት በጣም የተቀፈደደ ህዝብ ነበር" የሚለው አንዷለም የመታሰሩ ምክንያት ይሄንን ፍርሃት ለመስበር በመትጋቱ እንደሆነ ያምናል። ከእስር የባሰ መዘዝንም ሲጠብቅ እንደነበርም ይናገራል፤ "ሊገድሉን እንደሚችሉኝ ሁሉ አምን ነበር። ያለማገነን ሞትን በየቀኑ እለማመደው ነበር። ሞት የሚያስፈራ ቢሆንም፥ መታሰር የሚያስፈራ ቢሆንም ያንን ደረጃ ማለፍ ካለተቻለ ለውጥ እንደማይመጣ አምን ነበር።"

ፍርሃትና ተስፋ

ይሁንና በወቅቱ ሲያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች በበርካታ ሰዎች ዘንድ ራስ ላይ አደጋን እንደመጋበዝ ወይንም በህይወት ውስጥ ስኬት ከማጣት የመነጨ እርምጃ ተደርገው ይቆጠሩ እንደነበር ይናገራል።

ከእስር ሲወጣ ያስተዋለው ግን ከዚህ እጅግ የተለየ ሁኔታ እንደነበር ይገልፃል።

"ህዝቡ በከተማም በገጠርም ተነቃቅቶ፥ እኛም እንደ ጀግና ተቆጥረን ሲታይ እውን የሆነ፥ የማይጨበጥ ይመስል የነበረ፥ ነገር ግን አሁን የተጨበጠ ህልም ነው ለእኔ። ህዝቡ ፍርሃትን አሸንፏል፤ የመጡት ለውጦችም ትልቅ ናቸው። በዲሞክራሲ ትግል ውስጥ ትልቁ ነገር ፍርሃትን ማሸነፍ ነው። ለፍርሃት የማይገብር ሕዝብ ካለ አገዛዝ በጫንቃው ላይ ሊሰፍር አይችልም።"

ይህ እውነታ ከገዥው ቡድን እልፍኝም መግባቱን እንደታዘበ ይገልፃል አንዷለም። "በውጭ የተደረገው ትግል፥ ኢህአዴግ ውስጥም መነቃነቅ የፈጠረ ይመስለኛል።" የሚለው አንዷለም ኢህአዲግን በሊቀ መንበርነት፥ አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመሩ የተሾሙት ሰው በብዙኃን ዘንድ ተስፋ መፈንጠቃቸውን ባይክድም፥ ጥያቄዎቹን መሰንዘሩ ግን አልቀረም፤

"የተባለውን ነገር በተግባር መተርጎም ይችላሉ ወይ? የተባለውስ በቂ ነው ወይ? ጥገናዊ ለውጥ ነው ወይ የሚያስፈልገው? አይመስለኝም። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ስር ነቀል ለውጥ ነው። ሃያ ሰባት ዓመት ከበቂ በላይ ነው።"በማለት ጥያቄውን ይመልሳል።

ከዚህ በኋላ ከኢህአዴግ በሚሰፈር ዳረጎ የሚኖርበት ጊዜ እንዳበቃ የሚያምነው አንዷለም በቀጣይ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደርጋሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ያስረዳል።

ተያያዥ ርዕሶች