አዲሷ የአሜሪካ የሰላዮች አለቃ

ጂና ሃስፕል Image copyright Getty Images

የአሜሪካው የስለላ መሥሪያ ቤት ሲአይኤ ከተመሠረተ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት አለቃ አግኝቷል። ፕሬዝደንት ትራምፕ በኦፊሴላዊ የትዊተር ገፃቸው ጂና ሃስፕል የሲአይኤ ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውን አስታውቀዋል።

የአሜሪካው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት 54 ለ45 በሆነ ድምፅ ነው ጂና ሃስፕል የሲአይኤ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው እንዲሾሙ ያፀደቀው።

ከዚህ ቀደም የደህንነት መሥሪያ ቤቱን ያገለገሉት ጂና ከመስከረም 11 የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ታይላንድ ውስጥ 'ጥቁር ሥፍራ' እየተባለ የሚጠራ ተልዕኮ ይመሩ ነበር።

የስለላ መሥሪያ ቤቱ የቀድሞ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው አይዘነጋም።

የሪፐብሊክ ፓርቲ አባል የሆኑት ጆን ማኬይን ጂና የስለላ መሥሪያ ቤቱን ለመምራት አይመጥኑም ሲሉ ይሞግቱ እንደነበር ይታወሳል።

ጂና ወንበሩን እንዲያዙ ድምፅ ከሰጡ ፖለቲከኞች መካከል 6 የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት መኖራቸው ብዙዎችን አስገርሟል። ሁለት የሪፐብሊክ ፓርቲ አባላት ደግሞ የተቃውሞ ድምጽ አሰምተዋል።

የስለላ መሥሪያ ቤቱን ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ያገለገሉት የ61 ዓመቷ ጂና ብዙዉን ጊዜ በሕቡዕ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ይነገርላቸዋል።

'ጥቁር ሥፍራ' እየተባለ የሚጠራውን ተልዕኮ ይመሩ በነበረ ጊዜም በእርሳቸው ትዕዛዝ ብዙዎች እንደተሰቃዩ ሲዘገብ ቆይቷል።

እርሳቸው ይጠቀሙባቸው ነበሩ ከተባሉ ምስጢር ማውጫ ማሰቃያ መነገዶች የተወሰኑቱ በፕሬዝደንት አቦማ ዘመነ-መንግሥት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እግዳ ተጥሎባቸው ነበር።

ተጠርጣሪዎች ሲሰቃዩ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስል የተቀረፃባቸው 92 ያክል ካሴቶች ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑም አዘዋል።

ጂና ከታይላንድ ከተመለሱ ወዲህም ሌላ የምርመራ ተልዕኮ እንደተሰጣቸው ቢታመንም የተጨበጠ መረጃ ግን ሊገኝ አልቻለም።