የኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ

የኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ Image copyright Clive Brunskill

ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በመቀጠል ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው የኤፍ ኤ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ቅዳሜ ዕለት በማንቸስተር ዩናይትድና በቼልሲ መካከል ይካሄዳል። ውጤት ገማች ደንበኛችን ላውሮ እነሆ የጨዋታው ውጤት ትንበያዬ ይላል።

ማንቸስተር ዩናይትድ

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንኖ የኤፍ ኤ ዋንጫን ማንሳት ግድ ይሆንባቸዋል፤ ምክንያቱም ይህን ዋንጫ አነሱ ማለት የተሳካ የውድድር ዘመን አሳለፉ ማለት ስለሆነ።

ይህን ዋንጫ ማንሳት ለክለቡም ሆነ ለሆዜ ሞሪንሆ አስፈላጊነቱ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ ጨዋታ የውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ከመሆኑም ባሻገር ለዩናይትድ ደጋፊዎች ብቸኛ ተስፋቸውም ነው።

ዩናይትድ ይህንን ጨዋታ አሸነፈ ማለት ደግሞ ከሚቀጥለው የውድድር ዘመን ቀደም ብሎ በሚካሄደው 'ኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫ' ላይ ከከተማ ተቀናቃኛቸው ሲቲ ጋር የመጫወት ዕድል አጋጠማቸው ማለት ነው። የሆዜና የጋርዲዮላ ፍጥጫን ማዬት ማንም ይጠላል ብዬ አላስብም።

ምንም እንኳ ሮሜሉ ሉካኩ ጉዳት ላይ እንዳለ ቢነገርም ለዚህ ጨዋታ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ። ሉካኩ ምርጥ አቋም ላይ በሚገኝ ሰዓት አስፈሪ ተጫዋች ነው። ከቀድሞ ክለቡ ጋር መጫወት እንደሚያስደስተውም እምነቴ ነው።

ቢሆንም የሉካኩ አቋም አስተማማኝ ነው ስለማላስብ ዩናይትዶች ተስፋቸውን በሳንቼዝ ላይ ቢጥሉ የተሻለ ይሆናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሳንቼዝ አቋም የተሻለ እየሆነ መጥቷል።

ሳንቼዝ እና ፖል ፖግባ መልካም አቋም ላይ የሚሆኑ ከሆነ ለዩናይትድ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ።

Image copyright Getty Images

ቼልሲ

የዚህ ጨዋታ ውጤት ምንም ሆነ ምን የቼልሲው አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ በቡድኑ ይቆያሉ ብዬ አላምንም፤ እንዲያውም ክለቡን እንደለቀቁት ነው የማስበው።

ለሰማያዊዎቹ ይህ ጨዋታ ለኮንቴ የተዘጋጀ ድግስ ዓይነት ነው፤ ማሸነፍ ከቻሉ ደግሞ በደስታ ይለያያሉ።

ብራዚላዊው ዊሊያን በዚህ የውድድር ዘመን ለቼልሲ ጥሩ ሲጫወቱ ከነገሩ እግርኳሰኞች ግንባር ቀደሙ ነው። የዚህ ልጅ አቋም ጥሩ ሆኖ ከኤደን ሃዛርድ ጋር ጥሩ መጣመር ከቻሉ ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉ።

ያም ሆነ ይህ የኤፍ ኤ ፍፃሜውን ቼልሲ ያሸንፋል ብዬ አምናለሁ።

ግምት፡ ቼልሲ 1 - 0 ዩናይትድ