የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ማስጠንቀቂያ ምን ያህል ተጨባጭ ነው?

Yohannes

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት በውጭ ሃገር ባንኮች ገንዘብ ያላቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን በመግለፅ አስጠንቅቀዋል።በሂደት የምርመራው ውጤት ይፋ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

ቀደም ሲልም የባለስልጣናት የሃብት ምዝገባን በሚመለከት የተጀመሩ እርምጃዎች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን ዛሬ ነገሩ ምን ላይ ደረሰ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ይህን ጥያቄ እንዲሁም የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ማስጠንቀቂያ ምን ያህል መሰረት ያለው ነው?

በዚህ መልኩ ባለስልጣናትን እንዴት ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል ስንል የደርግ ከፍተኛ አመራሮችን ለመክሰስ ተቋቁሞ በነበረው ልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት፣ በኋላም በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዓቃቤ ሕግነት ከዚያም በቀድሞው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ክፍል ሃላፊ የነበሩት አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤልን አነጋግረናል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የግልግል ዳኝነት ተቋም ዳይሬክተር ናችው።

ከአቶ ዮሃንስ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

የባለስልጣናት ሃብት ምዝግባ ከምን ደረሰ?

ባለስልጣናት በራሳቸው እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው ስም ያለና አለን ያሉት ሃብትን እንዳስመዘገቡ አውቃለሁ።መረጃውም አለኝ።ብዙዎቹ ይህን ያደረጉት ወደው ሳይሆን ተገደው ነው።ምዝገባው ከተካሄደ በኋላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መረጃውን ይዘው አልፎ አልፎ ባለስልጣናትን ያስፈራሩበት(blackmail)እንደነበር አውቃለሁ።በሌላ በኩል ሲፈልጉ መርጠው የከሰሷቸው ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በኮሚሽነርነትና ሚኒስትርነት ሃላፊነት ያሉ ባለስልጣናት አሉ።

ምዝገባው ምን ያህል ትክክለኛ ነበር?

ያስመዘገቡትና በመጨረሻ የተገኘባቸው የተለያየ፤ ሊኖራቸው ከሚችለው በላይ ሃብት ይዘው የተገኙና የተከሰሱ ባለስልጣናት ነበሩ።የተከሰሱት ግን በፖለቲካ አለመግባባትና ልዩነት የተፈጠረ ጊዜ ብቻ ነው።የባለስልጣናት የሃብት ምዝገባን የሚመለከቱ መረጃዎች ለህዝብ ይፋ መሆን የነበረባቸው ቢሆንም ባንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ሳይገለፁ ቀርተዋል።እስከ አራትና አምስት መቶ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሃብት አስመዝግበው ይህን እንዴት ሊያገኙ እንደቻሉ ሲጠየቁ ከዚህ መንግስት ወይም ከዚያ ኮሚሽን ተከፍሎን የሚሉ ባለስልጣናት መኖራቸውን አውቃለሁ።በዚህ መልኩ ያሉ ክሶችም አሉ።

የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ማስጠንቀቂያስ ምን ያህል ተጨባጭ ነው?

እንደሚገባኝ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አባልና መስራች የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር ማስጠንቀቂያቸው በጣም ተጨባጭ ይመስለኛል።በአለም አቀፍ የፀረ ህገወጥ ገንዘብ ዝውውር ስምምነቶች መሰረት አንድ ሰው በሌላ ሃገር ባንክ ገንዘብ ሲያስቀምጥና አጠራጣሪ ነገሮች ካሉ የሚመለከታቸው አገራት ባንኮች መረጃውን የሚለዋወጡበት ስርአቶች አሉ።የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ከነዚህ ነገሮች አንፃር ነው የተመለከትኩት።ስለዚህ ይህም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማስጠንቀቂያ ይበልጥ ተጨባጭ የሚያደርገው ይመስለኛል።

ማስጠንቀቂያው ወደ ተግባር ይቀየራል?

ወደ ተግባር ለመተርጎምና እርምጃ ለመውሰድ ዋና የሚያስፈልገው የመንግስት መልካም ፍቃድ ነው እሱም አለ ብዬ አምናለሁ።ትልቁ ስጋቴ ይህ ሃላፊነት የሚሰጠው ለማንና ለየትኛው ተቋም ነው?የሚለው ነው።ቀድሞ ፀረ ሙስና የሚባለው ተቋም አቅም የሌለው ከመሆኑ ባሻገር ራሱ በሙስና ውስጥ ወድቆ መጨረሻው ውድቀት ሆኗል።

ከዚያ ደግሞ ሃላፊነቱ ለፍትህ ሚኒስቴርና ፌደራል ፖሊስ ተሰጠ።በሙስና በውጭ ሃገር የተቀመጠ ገንዘብን የሚመለከት መረጃ ቢመጣለትም ፌደራል ፖሊስ በመረጃው መሰረት መንቀሳቀስ የሚጠይቀው አቅም አለው ብዬ አላምንም።የቀድሞ ፍትህ ሚኒስቴር ያሁኑ ጠቅላይ አቃቤ ህግም ያሁኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ የማድረግ አቅም አለው ብዬ አላምንም።ምናልባት አሁን አዲስ በሚደረግ ሹመት ለውጦች ካልመጡ፤ በርግጥ አሁን የተሾሙት አዳዲስ ሰዎችም ተስፋ የሚሰጡ ሆነው አይታዩኝም።

በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ ባደንቅም ሃላፊነቱን መውሰድ ያለባቸው ተቋማት ከአቅም በታች መሆን ግን ነገሩን አሳዛኝ ያደረገዋል።

ተያያዥ ርዕሶች