የቼልሲው ባለቤት አብራሞቪች የእንግሊዝ ቪዛ ማሳደስ አልቻሉም

ሮማን አብራሞቪች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሩስያዊው ቢሊዬነር እና የቼልሲ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት ሮማን አብራሞቪች በእንግሊዝ የመኖሪያ ቪዛቸውን ለማሳደስ እንተቸገሩ ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

አብራሞቪች ቡድናቸው ቼልሲ የኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜን ማንቸስተር ዩናይትድን በማሸነፍ ሲረታ ሊመለከቱ እንዳልቻሉ ተዘግቧል።

ለ51 ዓመቱ ጉምቱ ቱጃር ቅርብ የሆኑ ምንጮች ቪዛቸውን ማሳደስ ከእንደዚህ በፊቱ ካለው ላቅ ያለ ጊዜ እንደወሰደባቸው ተናግረዋል።

ይህ ለምን ሆነ ተብለው ለተየጠቁት ጥያቄ የእንግሊዙ ደህንነት ሚኒስትር "በመሰል የግለሰብ ጉዳዮች ላይ አስተያየት አንሰጥም" ሲሉ መልሰዋል።

የአብራሞቪች ቢሮ ሰዎችም እንዲህ ባለ ግለሰባዊ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየት አንሰጥም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት የቢሊየነሩ የኢንስትመንት ቪዛ መታደስ ካለባቸው ጊዜ ሶስት ሳምንት አልፏቸዋል።

በለንደን እና በሞስኮው መካከል ካለው ውጥረት ጋር ተያይዞም የአብራሞቪች ቪዛ እደሳ መዘግየት ጉዳይ የብዙዎችን ጆሮ መግዛት ችሏል።

የቢቢሲው ዳንኤል ሳንድፎርድ እንደሚናገረው አብራሞቪች በሩስያ ያለምንም ስጋት መዋዕለ-ንዋያችውን የሚያፈሱ ሲሆን ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ያላቸው ቅርበትም ላቅ ያለ ነው።

የእንግሊዝ ቪዛ እደሳቸው መዝግየት ጉዳይ ግን ከሁለቱ ሃገራት ሰሞንኛ ፍጥጫ ጋር ይያያዝ አይያያዝ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።

ከነዳጅ እና ጋዝ በተገናኘ ገንዘብ የናጠጡት አብራሞቪች በአውሮፓውያኑ 2003 ነበር የእንግሊዙን እግር ኳስ ክለብ የግል ንብረታቸው ያደረጉት።

9.3 ቢሊዮን ዩሮ በማካበትም እንግሊዝ ውስጥ ካሉ ቱጃሮች 13ኛ ደረጃን ይዘው ይገኛሉ ሲል ሰንደይ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።

በፈረንጆቹ ጥር ወር በግል አውሮፕላናቸው እንግሊዝን ለቀው ከወጡ ወዲህ ሞስኮ፣ ኒው ዮርክ፣ ሞናኮና ስዊዘርላንድ ቢዘዋወሩም ወደ እንግሊዝ የተመለሱት በቅርቡ ነው።

አብራሞቪች ሩስያ አሉኝ ከምትላቸው ቱጃሮች አንዱ ሲሆኑ ወደ ሃብት ጣሪያ ከመመንጠቃቸው በፊት አሻንጉሊት ይሸጡ ነበር።

ኋላም ከቀድሞው የሩስያ ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሰን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ተጠቅመው በነዳጅና ጋዝ ንግድ አማካይነት ሊበለፅጉ እንደቻሉ ይነገርላቸዋል።

የሩስያዋ ቹኮታ ክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ ሆነውም አገልግለዋል፤ ከወቅቱ የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸውም ይነገራል፤ ሮማን አብራሞቪች።