የዓለም መሪዎች የፆታ እኩልነትን እንዲያሰፍኑ ጥሪ ቀረበ

ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ ቻድዊክ ቦዝማን፣ ሌና ዱንሀም

የፎቶው ባለመብት, Reuters/Getty

ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባሉ ታዋቂ ግለሰቦች የፆታ እኩልነትን እንዲያረጋግጡ ለዓለም መሪዎች ጥሪ አድርገዋል።

ጥሪው የቀረበው በደብዳቤ ሲሆን ዝነኛዎቹ ኦፕራ ዊንፍሬይና ሜሪል ስትሪፕም ከእንቅስቃሴው መሪዎች መካከል ይገኙበታል።

ዋን ተብሎ የሚጠራ የዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅትም ጥሪውን ያስተባብራል።

መንግሥታት ያላቸውን ስልጣን በመጠቀም ልጃገረዶች የሚማሩበትንና "ለሴቶች ታሪካዊ ለውጥ" የሚመጣበትን ሀኔታ እንዲያረጋግጡ በመጠየቅ 140 የሚሆኑ ታዋቂ ግለሰቦችም ፊርማቸውን አስቀምጠዋል።

የታዋቂው ፊልም "ብላክ ፓንተርስ" ተዋናዮች ሌቲታ ራይትና ቻድዊክ ቦስማን ፊርማቸውን ካስቀመጡት ውስጥ ይገኙበታል።

ከነዚህም በተጨማሪ የእንግሊዝ ተዋናዮቹ ሚካኤል ሺን፣ ታንዲ ኒውተንና ናታሊ ዶርመር የሚገኙበት ሲሆን አሜሪካውያኖቹ ተዋናዮች ሌና ደንሀም፣ ናታሊ ፖርትማንና ኢሳሬም በዚሁ ድርጅት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ደግፈውታል።

ፆታዊ ትንኮሳዎች ከፍተኛ ውግዘት እየደረሰባቸው ባለበት በዚህ ወቅት "በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ስርዓታዊ የፆታ አለመመጣጠን እንዲሁም ጭቆናዎች ትኩረት እየተደረገባቸው ነው" በማለት የናሽቪል ፊልም ተዋናይ ኮኒ ብሪተን በመግለጫዋ አትታለች።

ለኤሚ ውድድር የተመረጠችው ይህች ተዋናይት በተጨማሪም " በዚህ ዓመት ሁላችንም በተለይም መሪዎቻችን ለእኩልነት ሊታገሉ ይገባል" ብላለች።

ደብዳቤው ድህነትን "አድሏዊ" ያለው ሲሆን " ደሀ ሴቶች ተድበስብሰውና ሲታለፉ ዝም ብለን አንመለከትም" ይላል።

በባለፈው ዓመት የአለም አቀፉ የኢኮኖሚ ፎረምም በወንዶችና በሴቶች መካከል እኩልነት ለማስፈን 100 ዓመት እንደሚወስድ ተገልፆ ነበር።

ለሁሉም ክፍት የሆነውን ይህንን ደብዳቤም ብዙዎች እንደሚፈርሙም ተስፋ ተደርጓል።

በመዝናኛው ዘርፍ ውጭ ካሉ ታዋቂ ሰዎችም በተጨማሪ የአሜሪካ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማድሊን ኦልብራይት፣ የሀፊንግተን ፖስት መስራች አሪያና ሀፊንግተን፣ የቀድሞ የናይጀሪያ የገንዘብ ሚኒስትር ጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ እንዲሁም የሞዛምቢክ ፖለቲከኛ ግራሻ ማሼል ደብዳቤውን ደግፈውታል።