ፎቶ ግራፍን ለታሪክ መንገሪያ

ማርታ ታደሰ

የፎቶው ባለመብት, Martha Tadesse

የፎቶ ግራፍ ባለሙያዋ ማርታ ታደሰ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ በኮምፒውተር ሳይንስ አግኝታለች። የሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በዴቬሎፕመንታል ሳይንስ ሰርታለች።

ፎቶን ማንሳት በልጅነቷ የጀመረችው ማርታ፤ የትኛውም ትምህርት ቤት፣ የትኛውም ተቋም ደጃፍ ፎቶ ግራፍ ለመማር ብላ አለመርገጧን ትናገራለች።

"ራሴን ነው ያስተማርኩት" የምትለው ማርታ ፎቶዎቿን ለአድናቂዎቿ የምታደርሰው ኢንስታግራምን በመጠቀም ነው።

የፎቶግራፍ ሙያዋንም ሀ ብላ የጀመረችውም በልጅነቷ ቤት ውስጥ ባገኘቸው ካሜራ ሲሆን 14 ዓመት አብራት የኖረችዋን ውሻ በማንሳት ነው።

"ካሜራውን የገዛችው እህቴ ናት" ትላለች።

የቤተሰቦቿን ሞባይል ስጡኝ እያለች ስታስቸግር ያየችው እህቷ ካሜራ ገዝታ እንደሰጠቻትም ታስታውሳለች።

በካሜራው ቀኑን ሙሉ ውሻዋን ስታነሳ ትውል እንደነበር የምትናገረው ማርታ በሂደት "ጓደኞቿን እስቲ ላንሳችሁ እያለች በመጠየቅ" እጇን ማፍታታት ክህሎቷን ማዳበር ቀጠለች።

"እህቴ ያንን ካሜራ ገዝታ ባትሰጠኝ ኖሮ ዛሬ ያለሁበት ስፍራ ላይ እገኛለሁ ብዬ አላስብም" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Martha Tadesse

ከንግግርና ከፅሑፍ ይልቅ ፎቶ

ማርታን የሚያውቋት ሲናገሩ በፎቶ ብቻ ሳይሆን በፅሑፍም ራሷን መግለፅ ጎበዝ እንደሆነች ይናገራሉ።

እርሷ ግን ወደፎቶ የማድላቷን ምክንያት ሁለቱ ክህሎቶቿ መግለፅ የምትፈልጋቸውን ነገሮች የበለጠ ለመግለጥ ስላልረዷት እንደሆነ ትናገራለች።

ፎቶ የበለጠ ዝንባሌዋ እንደሆነ የምትናገረው ማርታ በብዛት በምታነሳቸው ፎቶዎች የሰው ልጅ ፊትን ማሳየት ትመርጣለች።

"ታሪካችን ከማንነታችን ጋር ይያያዛል፤ ያ ደግሞ የበለጠ ፊታችን ላይ ይነበባል። ፎቶዎቹ ለምፅፋቸው ነገሮች የበለጠ የሚጨምሩልኝ ነገሮች አሉ "ትላለች።

ማርታ በምታነሳቸው ፎቶ ግራፎች ምን ማድረግ እችላለሁ? ብላ ዘወትር ስታስብ በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ አካላት ያለባቸውን ችግር፣ ጉዳታቸውን፣ በደላቸውን ለቀሪው ማህበረሰብ በማሳየት መርዳት እንደምትፈልግ ትናገራለች።

"ለምሳሌ በአሁኑ ሰአት የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን ለማስተዋወቅ አንድ ፕሮጀክት ይዤ እየሰራሁ ነው። ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ታሪክ፣ የእነሱን ጉዳት በፎቶ ለመናገር ብችል ደስ ይለኛል ትላለች። በሙያዬ ስለተገፉ ሰዎች ለሌሎች ብናገር እና ታዳሚዬ አንድ ነገር ማድረግ ቢችል ደስታዬ ወደር የለውም።" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Martha Tadesse

ስርአተ ፆታ እኩልነት

ማርታ በፎቶ ታሪክን ስትናገር በዋናነት የስርአተ ዖታ እኩልነት ላይ ታዘነብላለች። በፎቶዎቿ የተወሰነ ክፍል ላይ ብቻ ማተኮር እንደማትፈልግ የምትናገረው ማርታ የተመጣጠነ ውክልና በስራዎቿ ውስጥ ቢታይ ቀዳሚ ፍላጎቷ ነው።

በተለያየ የብዙሃን መገናኛ ውስጥ የአንድ ወገን ውክልና ግዘፍ ነስቶ ሊታይ እንደሚችል የምትጠቅሰው ማርታ እንደ ጾታ እኩልነት አቀንቃኝነቴ የሁለቱም ወገኖች ውክልናን በስራዬ ማሳየት አላማዬ ነው ትላለች።

የማርታ ታደሰ ስራዎች የሰራተኛውን መደብ፣ የሰው ልጅ የእለት ተእለት እንቅስቃሴዎች ላይም ያተኩራሉ።

ማርታ ስለ አዲስ አበባ ሲወራ ስለልማቷ ብቻ መወራት እንደሌለበትና ፤ ከዚህ በስተጀርባ ያለ ሕዝብ፣ በተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚኖር አዲስ አበቤን በፎቶ መወከል አለብኝ የሚል ፅኑ አቋም አላት።

"መወከል የምፈልገው ሁሉንም ነው፤ በክልል፣ በፆታ፣ በእድሜ፣ በሐይማኖት ከፋፍዬ ታሪክን መንገር አልፈልግም" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Martha Tadesse

ፎቶን በምክንያት

ማርታ የሚያስደስታትን ፎቶ እንደምታነሳ ብትናገርም ፎቶዎቿን በምክንያት ብቻ ማንሳት እንደሚኖርባት ሁሌም ታስባለች።

"ፎቶን ሳነሳ አንድ ምክንያት መኖር አለበት፤ እኔ ራሴን የጎዳና ላይ ፎቶ ግራፍ አንሺ ነኝ ብዬ አላስብም። በርግጥ የሚያስደስተኝን ነገር አነሳለሁ። ግን ሰበብ ነገር በስራዎቼ ውስጥ ቢኖሩ እመርጣለሁ" ትላለች።

አንድን ፎቶ ለማንሳት ታሪኩ መጀመሪያ መረዳት የመጀመሪያ ስራዋ ሲሆን ከታሪኩ ጋር ራሷን ካዛመደች በኋላ ፎቶዎችን እንደምታነሳ ትናገራለች።

ይህንን ማድረጓ ደግሞ የሚረዳት የፎቶዎቿን ተመልካቾች ከአልፎ ሂያጅ አድናቂነት ወደ ጠያቂነት እንዲመጡ ለማድረግ እንደሆነ ትናገራለች።

"ፎቶዎቼን የሚያዩ ሰዎች ይሄ ፎቶ ሲያምር ብቻ ብለው እንዲሄዱ አልፈልግም። ካዩ በኋላ ምን ማድረግ እችላለሁ የሚለው ጥያቄ በውስጣቸው ቢነሳ እመርጣለሁ" በማለት ታስረዳለች።

እንደምሳሌነት ስትጠቅስም በጾታ ጥቃት ላይ የሰራችው ፕሮጀክትን ታስታውሳለች።

ለዚህ የፎቶ ስራ ያቀረበችው ከ 4 እስከ 6 የሚሆኑ ፎቶዎችን እንደነበሩ የምታስታውሰው ማርታ ፎቶዎቹን ያዩ ግለሰቦች ስለ ጾታዊ ጥቃት ግንዛቤያቸውን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ከዛ በኋላ ምን ማድረግ አለብኝ የሚለው ላይ ውይይት በመፍጠር ረገድ የበኩሏን አስታዋፅኦ ማድረጓን ትናገራለች።

ማርታ በስራዎቿ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ብቻ ሳይሆን በወር አበባ ወቅት የሴቶች ልምድ እንዲሁም የወንዶች አረዳድ ምን ይመስላል በሚል የፎቶ ስራዎቿን ሰርታለች።

ይህ በመሀል ከተማም ሆነ በክልል ከተሞች እንደነውር የሚቆጠር እና ግልፅ ውይይት የማይደረግበት ጉዳይ በመሆኑ በግልፅ መነጋገር በሴቶቹ ጤና ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ለማሳየት በኢንስታግራም ላይ ፎቶዎቿን አጋርታለች።

ይህ ደግሞ በወጣቶቹ ዘንድ መነጋገርን በመፍጠር ለውጥ ለማምጣት እንደረዳት ታስታውሳለች።

የፎቶው ባለመብት, Martha Tadesse

ኢንስታግራምን እንደ መድረክ

ማርታ ስራዎቿን በዋናነት የምታቀርበው የማህበራዊ ሚዲያ በሆነው በኢንስታግራም በኩል ነው። ኢንስታግራምን ስትጠቀም ይኸኛው ወገን ቢያየው ብላ አስባ እንዳልሆነ የምትናገረዋ ማርታ በመጀመሪያ እንዲሁ ስራዎቿን ለማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው የማጋራት ሀሳብ ብቻ እንደነበራት ታስታወሳለች።

እግረ መንገድ ግን ከሐገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዋነኛ የስራዎቿ ተደራሽ እንደሆኑ ትናገራለች።

በተለይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለስራ ስትንቀሳቀስ የምታነሳቸውን ፎቶግራፎች መሃል ከተማ ተቀምጦ ሌሎቹን የሀገሪቷን ክፍሎች ላላየው እንዲሁም ከሀገር ውጭ ለሚኖረው ስለነዛ ስፍራዎች ፎቶዎቿ ጠቋሚ መረጃዎች በመስጠት የራሳቸውን ድርሻ እንደሚጫወቱ ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Martha Tadesse

በአዲስ አበባ እና በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በፎቶዎቿ ስለሌሎች አካባቢዎች በአፍ ከሚነገሩ ታሪኮች ውጭ እውነታውን ማሳየት እንደምትፈልግም ትናገራለች።

ከዚህም በተጨማሪ የምዕራቡ አለም መገናኛ ብዙሃን ስለኢትዮጵያ እና አፍሪካ ያላቸውን አንድ ጥግ የያዘ ግንዛቤ ሌላ እውነታም አለ የሚለውን ለማሳየት እንደምትጠቀምበትም ታስረዳለች።

ከኢንስታግራም በተጨማሪ ከሁለት ጓደኞቿ ጋር በመሆን የሴት ልጅ ግርዛት፣ ጥቃት እና መደፈር ላይ የፎቶ አውደ ርዕይ አዘጋጅታ ታውቃለች።

እንዲሁም የተፈጥሯዊ ፀጉር በሚል ርዕስ ክሮሲንግ ባውንደሪስ ባዘጋጀው አውደ ርዕይ ላይም ተሳትፋለች።