የቢላል አዛን የናፈቃቸው ሀበሾች

ራውዳ አሰፋ፣በክሪስቲያንሳንድ፣ ክሪስቲያን IV ጋታ መንገድ, የረመዳን መባቻ፣ የኖርዌይ ብሔራዊ ቀን ለማክበር
የምስሉ መግለጫ,

ራውዳ አሰፋ፣በክሪስቲያንሳንድ፣ ክሪስቲያን IV ጋታ መንገድ, የረመዳን መባቻ፣ የኖርዌይ ብሔራዊ ቀን ለማክበር

የረመዳን ፆም ጀምበር ወጥታ እስክትጠልቅ ይፀናል። ፀሐይ ስትጠልቅ ደግሞ 'ማፍጠር' ይከተላል። ግን ቆይ! ፀሐይ በጄ ብላ ባትጠልቅስ? እምቢኝ አሻፈረኝ ብትልስ? ሌሊቱ ብራ እንደሆነ ቢነጋስ? ሳይበላ ሊቀር!?

የኢትዮጵያን ሸላይ ፀሐይ ብቻ እየሞቀ ያደገ ሀበሻ "ያ አኺ! ምንድነው ምታወራው?" ሊል ይችላል። አትፍረዱበት። አንድ ፀሐይ ነው የሚያውቀው። ምድር ላይ ስንትና ስንት 'ዐዛ' የሚያደርጉ ፀሓያት እንዳሉ አያውቅም።

የአገር ቤት ፀሐይ እንደ እንጀራችን ክብና ገራገር ናት። በ12 ግድም ወጥታ፣ በ12 ግድም ትጠልቃለች። መዓልትና ሌቱ ስምም ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ሙስሊምም የቀኑን እኩሌታ ፆሞ፣ እኩሌታውን ይፈስካል። ኻላስ!

ይህ ግን ሁሉ አገር አይሠራም።

በየዓለማቱ እንደ አሸዋ የተበተነው ሕዝባችን እስከ አርክቲክ ተረጭቷል። ፀሐይ እስከማትጠልቅበት አፅናፍ ድረስ።

ከ'ቢላዱል ሀበሺ' ብዙ ሺህ ማይሎችን ርቀው፣ የምድር ድንበር ላይ የሚኖሩ፣ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ምዕመናንን ጠይቀናል፤ "ኧረ ለመሆኑ ፆሙ እንዴት ይዟችኋል?" ስንል።

ግሪንላንድ፣ አይስላንድ፣ ቻይና፣ ሰሜን ራሺያ፣ ሰሜን ስዊድን፣ ሰሜን ፊንላንድ፣ ምዕራብ ካናዳ፣ ደቡብ ኖርዌይ እንዲሁም መካከለኛው አውሮፓ ከሚኖሩትና በስልክ ካነጋገርናቸው ውስጥ የጥቂቱን ብቻ ለዛሬ 'መርሃባ!' ብለናል።

"በቀን ለ21 ሰዓት እንም ነበር" ራውዳ አሰፋ (ኖርዌይ)

በኖርዌይ መንገዶች ባለሥልጣን የዊንዶስ ሲስተም ባለሞያ ነኝ። ኖርዌይ መኖር ከጀመርኩ 10 ዓመት ሆነኝ። አሁን ክሪስቲያንሳንድ የምትባል ከተማ ነው የምኖረው። ከኦስሎ በመኪና የአራት ሰዓት መንገድ ቢሆን ነው።

እኔና ባለቤቴ አሁን ለ18 ሰዓት ነው እየፆምን ያለነው። የምንጾምበት ሰዓት በየቀኑ 6 ደቂቃ ስለሚጨምር በወሩ መጨረሻ ለ19 ሰዓት እንፆማለን ማለት ነው።

እዚህ ደቡባዊ ኖርዌይ መኖር ከመጀመሬ በፊት ቡዶ (Bodø) የምትባል ከተማ ነበር የምኖረው። ከአርክቲክ ሰርክል በሰሜናዊ አቅጣጫ የምትገኝ ትንሽዬ የኖርዌይ ከተማ ናት። እዚያ እያለሁ ለ21 ሰዓታት እንፆም ነበር።

ቡዶ ፀሐይ ስትጠልቅ ዐይተናት አናውቅም። ከሌሊቱ 10 ሰዓት ፀሐይ ፍጥጥ ብላ ትታያለች። በዚህን ጊዜ 'ፉጡር' እና 'ሱሁር' አንድ ይሆናሉ። *('ፉጡር'-ጦም መግደፊያ ሲሆን 'ሱሁር' ግን አዲስ ጦም ለመጀመር ሲባል ከንጋት በፊት የሚቀመስ አፍ-ማሟሻ ነው።)

በጁን 21 ደግሞ ፀሐይ ጭራሽ ሳትጠልቅ ቀኑ ይቀየራል። እኔ ወደ ክሪስቲያንሳንድ ከመጣሁ በኋላ እንደሰማሁት ደግሞ በኖርዌይ ቡዶ ጀምበር ስለማትጠልቅ የ'ኢፍጣር' ሰዓታቸውን በቅርብ ከሚገኝ ሙስሊም አገር አስማምተው መፆም እንደጀመሩ ነው።

ዊንተር (የፈረንጆቹ ክረምት) ላይ በተቃራኒው ፆሙ ለአጭር ሰዓት ይጸናል። ፀሐይዋ አረፋፍዳ ስለምትወጣ ሱብሂ ሶላት (*ለወትሮ ማለዳ ወፍ ጭጭ ሳይል የሚደረግ ስግደት) የምንሰደግደው ሥራ ገብተን ነው። ፆም የምንገድፈው ደግሞ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል አካባቢ ነው።

እውነቱን ለመናገር ማጠሩን "ሰለብሬት" አላደርገውም። ብዙም ምቾት አይሰጠኝም። አጅሩ ( *መለኮታዊ ሽልማቱ) በዚያ መጠን የሚቀንስ ስለሚመስለኝ ይሆን ይሆናል።

እዚህ ኖርዌይ ለረዥም ሰዓት ስለምንፆም አገር ቤት እንደለመድነው ዘይት የሚበዛባቸው ምግቦችን፤ እነ ሳንቡሳን፤ ብዙም አንወስድም። ከዚያ ይልቅ ፕሮቲን ያላቸው፣ ሳይፈጩ መቆየት የሚችሉ ምግቦችን እናዘወትራለን። እንቅስቃሴያችንም የተገደበ ይሆናል። ለምሳሌ እኔና ባለቤቴ ልጆቻችንን ለብስክሌት ግልቢያ መስክ ይዘናቸው አንወጣም።

ኖርዌይ ከባለቤቴ ጋር ተጋግዘን ነው የምንሠራው። እሱ ቤት ማጽዳት፣ ልብስ ማጠብ፣ ልጆቹን ቁርስ ማብላትና መንከባከብ ላይ ያተኩራል። እኔ ምግብ ማዘጋጀቱን እመርጣለሁ። አልፎ አልፎ ኢትዮጵያ ስንሄድ ግን ባለቤቴ "ኢትዮጵያዊ ባል" ነው የሚሆነው። (ሳቅ)

ረመዳን በኢትዮጵያ የሚናፍቅ ነገር አለው። በተለይ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እያለን ከእኩዮቼ ጋር አብረን እያፈጠርን፣ ለሱሁር አብረን እየተነሳን፣ ተራዊህ ( *ምሽት ከእቅልፍ በፊት የሚሰገድ ዘለግ ያለ ስግደት) አብረን እየሰገድን የማይረሳ ጊዜ አሳልፈናል። ከሁሉ ከሁሉ የረመዳን የመጨረሻዎቹን አስር ቀናትን እናዘወትርበት የነበረው ሸጎሌ የሚገኘው ሼክ ሆጀሌ መስጊድ እጅግ አድርጎ ንፍቅ ይለኛል።

የምስሉ መግለጫ,

በከሪ ኑሪ እና ሱረያ ዲኖ በጀርመን ፍራንክፈርት

"ረመዳን በካናዳ ምንም ደስ አይልም" ልማ ጉዮ

ተወልጄ ያደኩት ቦረና ነው፤ ያቤሉ ውስጥ። አሁን የምኖረው ምዕራብ ካናዳ ነው፤ ኤድመንተን-አልበርታ።

ኢትዮጰያ 12 ሰዓት ጀምረህ ማታ 12 ሰዓት ታፈጥራለህ። ደስ ይላል። እዚህ ግን ሌሊት 2፡50AM (በኢትዮጰያ ሌሊት 8 ሰዓት፡ከ50) ፆም መያዝ የጀመርን ማታ 10፡00 PM (አራት ሰዓት በኢትዮጵያ) ነው የምንፈታው። በመሐል ያለው 4 ወይም 5 ሰዓት ብቻ ነው።

እኛ እዚህ ስናፈጥር ኢትዮጰያ 'ተራዊህ' እየተሰገደ ነው። እኛ 'ተራዊህ' ሰግደን እንደጨረስን የአዲሱ ቀን ፆም ይጀምራል።

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ረመዳንን በካናዳ ፆሜያለሁ። በቀን ከ20 ሰዓት በላይ ነው የምንፆመው። እዚህ ሁሉንም ነገር ገዝተህ ታገኛለህ። ግን ደስ አይልም። ኢትዮጵያ ብሆን ይሻለኛል። ኢትዮጵያ ቤተሰብ አለ፣ ጎረቤት አለ፣ ፍቅር አለ። እዚህ ምን አለ?

ሥጋ ራሱ ቦረና "ኦርጋኒክ" ነው፤ እዚህ ካናዳ ግን "ፍሮዝን" ነው። ከትውልድ አገሬ ቦረና ኡጂና ሳምቡሳ እጅግ ይናፍቁኛል። "ኡጂ" ታውቃለህ?

"ከኤርትራዊያን ጋር ነው የምናፈጥረው" በክሪ ኑሪ እና ሱረያ ዲኖ

በክሪ እባላለሁ። ባለቤቴ ሱረያ ትባላለች። ጀርመን ፍራንክፈርት እሷ 10 ዓመት፣ እኔ 6 ዓመት ኖረናል። እዚህ ረመዳንና Summer በመገጣጠሙ ወደ 17/18 ሰዓት ነው የምንፆመው። ሌሊት 10 ሰዓት መፆም የጀመርን ማታ 21 ሰዓት (ምሽት 3፡00 ሰዓት) ነው የምንበላው።

እዚህ በበጋና በክረምረት መፆም ልዩነት አለው።

በጋ ላይ ረዥም ሰዓት መፆሙ ብቻ ሳይሆን ሙቀቱ እስከ 35 ዲግሪ ስለሚደርስ ይደክማል። በክረምት ግን ለአጭር ሰዓት ነው የሚፆመው፤ ኾኖም በጣም ይርባል፡፡ በክረምት አጭር ሰዓት ከመፆም በበጋ ረዥም ሰዓት መፆም ነው የሚሻለው።

አንድ ሁለት ጊዜ ረዥም ሰዓት መፆም አቅቶኝ አቋርጬ አውቃለሁ። ለረዥም ሰዓት ምግብ ስለማልበላ ጨጓራዬ ተቀሰቀሰብኝና አቋረጥኩት። ቢሆንም ግን በክረምት መፆም የባሰ ነው፤ በጣም ይርባል፤ ሰዓቱ ማጠሩን ማየት የለብህም። ብርዱ በጣም ነው የሚያስርበው።

የምስሉ መግለጫ,

ሕጻን ዩኑስ እና ሕጻን መሐመድ ከአባታቸው በክሪ ኑሪ ጋር ሶላት በመስገድ ላይ፣ ፍራንክፈርት

"ማድቤት ገብቼ ሳንቡሳ የምሠራው እኔ ነኝ" በክሪ

ሾርባ፣ ሳንቡሳ፣ የሞሮኮ ምግቦችን ሁሉ ልቅም አድርጌ አበስላለሁ። ከባለቤቴ ይልቅ ማድቤት ገብቼ የምሠራው እኔ ነኝ። እዚህ ጀርመን እንደኛ ቤተሰብ ያለው ቤቱ ያፈጥራል። ላጤ የሆነ ደግሞ መስጊድ ሄዶ በነፃ ማፍጠር ይችላል። እዚህ ፍራንክፈርት ብዙ መስጊዶች ነው ያሉት። ሞሼ ይባላሉ። መስጊድ ማለት ነው በጀርመንኛ።

"ሀበሾች ግን መስጊድ የለንም"

ጀርመን ብዙ መስጊድ ቢኖርም ሀበሾች ግን መስጊድ የለንም። እዚህ መስጊዶች በአገሮች ነው የሚሰየሙት። የሞሮኮ፣ የቱርክ፣ የአፍጋን፣ የግብፅ፣ የፓኪስታን መስጊዶች አሉ። ለእኔ የሚቀርበኝ የሞሮኮዎቹ 'አቡበከር ሞሼ' የሚባለው መስጊድ ነው።

ሀበሻ የሚበዛበት መስጊድ ግን 'ዶቼ-ሞሼ' የሚባለው ነው። እኛ ሀበሾች የራሳችን መስጊድ ስለሌለን ዶቼ-ሞሼ ነው የምንሰግደው።

ረመዳን ደስ ይላል። የተጠፋፋን ጓደኛሞች የምንገናኝበት ወር ነው። ከኤርትራዊያን ጋር በወር አንዴ ተገናኝተን አብረን እናፈጥራለን።

"የፉርኖ ዱቄት እንጀራ"

እንጀራን ኢትዮጵያ የምናውቀው በጤፍ ነው። እዚህ በገብስና በፉርኖ ዱቄት ነው የሚሠራው። ኢትዮጵያ ሾርባ መሥሪያ ትክክለኛ የገብስ ቅንጬ አለ። እዚህ ግን ከአጃ ነው የምናዘጋጀው።

ሳምቡሳውም፣ ሾርባውም ሁሉም አለ። ግን ኦሪጅናሉን የኢትዮጵያውን አታገኝም። ጣዕሙስ ካልከኝ በአጭሩ እንደ አገርቤት አይጣፍጥም።

"ጀርመን…ቶሎ ቶሎ የሚሰገድባቸው መስጊዶች"

ከ'ኢፍጣር' በኋላ የሚኖረወን ሰዓት በጣም የተጠጋጋ ስለሆነ ቶሎ አፍጥረን፣ ቶሎ ተራዊህ ሰግደን፣ ቶሎ 'ሱሁር' በልተን ፆሙን መጀመር አለብን።

ጀርመን ቶሎ ቶሎ የሚሰገድባቸው መስጊዶች አሉ። ቀስ ተብሎም የሚሰገድባቸው አሉ። ቀጠሮ ያለበት ሰው ምናምን በፍጥነት በመስገድ ወደሚታወቁት ቱርኮች መስጊድ ሄዶ ይሰግዳል።

የምስሉ መግለጫ,

የበክሪና የሱረያ ብላቴና መሐመድ በክሪ፣ በፍራንክፈርት

"ለሙከራ አብረውን የሚፆሙ ጀርመኖች አሉ"

እዚህ በሥራ ቀልድ የለም። ረመዳን ነው ብለህ ሥራ መቅረት አትችልም። ኾኖም የዓመት እረፍትህን፣ (እዚህ "ኡርላፕ"/Urlaub/ ይሉታል) ረመዳን ላይ እንዲሆን አድርገህ ትሞላና ፆም ላይ ትንሽ ታርፋለህ፡፡

የእኛ መፆም ጀርመኖችን በጣም ነው የሚገርማቸው። በተለይ ውሀ አለመጠጣታችን በጣም ይገርማቸዋል። እንሞክረው ብለው አብረውን የሚፆሙም አሉ። በተለይም በውፍረት የሚቸገሩ "ይሄ ነገር አሪፍ ሳይሆን አይቀርም" ብለው አብረውን ይፆማሉ።

"የአገሬ አዛን ይናፍቀኛል"

ኮልፌ ነበር ሰፈ። ኮልፌ ተራራማ አካባቢ ነው። ፀሐይ ስትወጣም ስትገባም ማየት ትችላለህ። ፍራንክፈርት ግን ፀሐይ ስትገባም ሆነ ስትወጣ አይተናት አናውቅም።

እዚህ አገር መስጊዶች ቢኖሩም ድምፅ ማሰማት አይችሉም። በጣም ክልክል ነው። ኮሽታ ከተሰማ ነዋሪዎች ቅሬታ ያሰማሉ። ዐዛን የሚሰማው መስጊዱ ውስጥ ላለ ሰው ብቻ ነው። ነዋሪዎችን መረበሽ አትችልም። ምንድነው መሰለህ የሚደረገው መስጊዶች ካላንደር ይሰጡሃል። ስንት ሰዓት እንደሚሰገድ፣ ስንት ሰዓት እንደሚፈጠር። ሰዓቷን አይተህ ትሄዳለህ እንጂ ዐዛን የሚባል ነገር የለም። ለዚህ ነው የአገሬ ዐዛን ይናፍቀኛል የምልህ…

"የአንዋር መስጊድ ግርግር አይረሳኝም"

የበክሪ ባለቤት ሱረያ ዲኖ በበኩሏ ጀርመን ረዥም ሰዓት ብፆምም እንደ ኢትዮጵያ ግን አይርበኝም ትላለች። ምክንያቱን ስታስረዳ "እዚህ በሥራ ተወጥሬ ስለምቆይ ሰዓቱ አይታወቀኝም።"

"...አገር ቤት እኮ 'ፍጡር ሰዓት አይደርስም እንዴ?፣ አዛን አይልም እንዴ?' እያልክ ደጅ ደጁን ታያለህ፤ እዚህ ግን 'ወይኔ ጉዴ ፍጡር ሰዓት ደረሰብኝ!' ብለህ ነው የምትሯሯጠው።"

ሱረያ ከኢትዮጵያ ረመዳን ጋር ተያይዞ የምትናፍቀው የመስጊድ ግርግር ነው። "…መርካቶ አንዋር መስጊድ ታክሲው፣ ሳምቡሳው፣ ቴምሩ፣ ግርግሩ በጣም ያምራል፤ ወሩን ሙሉ ኢድ ነው የሚመስለው። ሆኖም እኔ መሳለሚያ ቢላል መስጊድ ነበር የማዘወትረው።" ትላለች የፍራንክፈርቷ ሱረያ ዲኖ።

የቢላል ዐዛን ናፋቂ ሀበሾች

በኢስላም ታሪክ የመጀመርያውን ዐዛን (የሶላት ጥሪ) ያሰማው ሰው ደምፀ-መረዋው ቢላል-አል-ሀበሺ ነበር። የዚያ ዘመን ስደተኛ!?

ይኸው ከ1ሺህ 439 ዓመታት በኋላም እንደ ቢላል የተሰደዱ፣ የእርሱን ዐዛን በአገራቸው መስማት የናፈቁ ሀበሾች ዛሬም እልፍ ናቸው። ተዘርተዋል፤ እንደ ከዋክብት፤ እንደ እንጀራ ዐይኖች። እንጀራ ፍለጋ…እስከ አርክቲክ…እስከ ሰሜን ዋልታ…