ጉዞ ከሃገር ባሻገር የዓለም ዜጋ ለመሆን

አላን በጉዞው ካገኛቸው ጓደኞቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Alan Mesfin

አላን መስፍን ከኤርትራውያን ቤተሰብ የተገኘ ቢሆንም እራሱን እንደ የዓለም ዜጋ ነው የሚያየው። የሰው ልጆች የሰሯቸው ድንበሮች ተፈጥሯዊ ስላልሆኑ ተከባብረንና ተዋደን መኖር እንዳለብን ያምናል።

አላን ባለፉት አስር ወራት የአውሮፓና እስያ ሃገራትን እንዲሁም አውስትራልያ ለመጎብኘት ጉዞ ላይ ነው ያለው። ባለፈው ወር ጃፓን ውስጥ ከደቡባዊ የሳታ ሚሳኪ ጫፍ ተነስቶ ወደ ሰሜናዊው የሶያ ሚሳኪ ፅንፍ በእግሩ እየተጓዘ ነው።

ጉዞው እስከ ስድስት ወራት ሊወስድበት እንደሚችል ገምቷል። ጃፓን 25ኛ መዳረሻው ነች።

"ወላጆቼ ይሄን ያክል ርቀት መጓዝን ምን አመጣው እንዲሉ እንዳደረኳቸው አልጠፋኝም። ለእኔ ግን፤ ከአሁን በኋላ ገና ብዙ ይቀራል" ይላል የተቀረውን የጉዞ ዕቅዱን እያስታወሰ።

ባንድ ወቅት፤ አመሻሽ ላይ በጃፓን በረሃዎች ሲጓዝ ተኩላ ገጠመውና ሳይተናኮለው ተርፏል። ምድረ ጃፓን ተኩላና ድብ የሞላበት አገር ነው።

"ቻይና ውስጥ በየሄድክበት የፍተሻ ኬላ ስላለ፤ ፓስፖርት ቪዛና የምትቆይበት ቦታ እንዳለህ የሚያስረግጥ ሰነድ ዋናውንና ቅጂውን ማቅረብ ስላለብህ ስጋት ነበረብኝ። ልክ ሻንጋይ እንደደረስኩ ግን፤ ትልቅ ከተማ ስለሆነ ነው መሰለኝ ያ አሰልቺ ፍተሻ አልጠበቀኝም።"

ሻንጋይ የህዝብ ብዛቷን እና የከተማዋን ትልቅነት የሚመጥን ኢንተርኔትንም ይዛ አልጠበቀችውም።

የጉዞው ዓላማ

የጉዞዬ ዓላማ ብዙ ሀገሮችን ለመድረስ እና ባህላቸውን ለማወቅ ነው። በተለይም ከዚህ በፊት ያልተዋወኳቸውን። ከአውሮፓ ውጭ ስለሚኖሩ ህዝቦች የነበረኝ እውቀት ውስን ነበር። አሁን ግን አንዲት ሀገር ላይ ስደርስና አሻግሬ ሌላኛዋን መዳረሻዬን ሳይ እኩል እየሆነ ነው።

በርግጥ ለመጀመሪያ ግዜ አንዲት ሀገር ላይ ስደርስ ሞቅ ያለ ስሜት ነው የሚሰማኝ። ጎብኚዎች የሚሄዱባቸው ቦታዎች፣ ምግቡ፣ የአካባቢው ባህልና ልምዱ ማራኪ ነው።

እንዲህ ላሉት ነገሮች ፍቅሩ ስላለኝ ነው ጉዞውን የማደርገው። ሌላም ግድ የሚለኝ ነገር አለ፤ ሰው ልጆች ግንኙነት። የአንዲት ዓለም ሰዎች ሳለን አስተሳሰባችን እና ችግሮችንን የምንፈታበት ዘዴ ግን የተለያየ ነው። እነዚህን በቅርበት ስታዘብ ደስ ይለኛል።

ስለዓለም ያለኝ አመለካከት ከሌላው ሰው ለየት ያለ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከእያንዳንዳችን መማር የምንችላቸው በርካታ ነገሮች አሉ። በቀጣይነትም መማር እፈልጋለሁ።

የፎቶው ባለመብት, Alan Mesfin

ጃፓን

ስለ ጃፓን ከተራው ሰው የተሻለ እውቀት ያለኝ ይመስለኝ ነበር። ወንድሜ ወደ ጃፓን ከሄደ ይሄው አስር ዓመቱ ነው። እዚያው ቀርቷል።

በባለቤቱና በቤተሰቦቿ በኩል ከሀገሪቷ ጋር በሚገባ መተዋወቅ ጀመርኩ። ከታሪካዊ ቤተ-መቅደሶቻቸው በተጨማሪ ትዕግስታቸው፣ የፈጠራ አቅማቸው፣ ግብረ-ገብነታቸው የሚያስደምም ነው።

ሻኲ (ቤዝ-ቦል) ሲጫወቱ ማየትም አስደሳች ነው። አንድን ነገር አሻሽለው ለመስራት፣ ለማስጌጥ፣ ደግመው ለመፍጠር የተፈጠሩ ሰዎች መስለው ነው የሚሰሙኝ።

ከደግነታቸው፣ ከዋህነታቸውና ከጋስነታቸው ውጪ ስለምን ላውራ? በተለይ ብቻዬን በማደርገው በዚህ ጉዞ ላይ ሁኜ የማስባቸው እና የማብላላቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ሰዎች ፈገግ ሲሉልኝ፣ ጎንበስ ብለው ሰላምታ ሲያቀርቡልኝ አያለሁ።

ጭው ባለው መንገድ ላይ ድጋፍ ቢሆነኝ ብለው የሚጠጣ ይሰጡኛ፣ ልጆች እጃቸውን ያውለበልቡልኛል፣ በእንግሊዘኛ ሊያዋሩኝም ይሞክራሉ። መቼም በጃፓን የውጭ ሰዎችን እምብዛም አያዩም። ልክ ቦሲኒያ፣ ህንድ እና ላኦስ ውስጥ እንደሚገኙት ገጠሮች ጥቁሮችን ማግኘት ከባድ ነው!!!

ለዚህም ነው ጃፓንኛ ለመማር የተነሳሳሁት። ከቋንቋ ጋር የሆነ ትስስር አለኝ፤ ጉጉት ይሁን ታታሪ ሁኜ ልሁን አይገባኝም። አዲስ ቋንቋ መማር ግን ደስ ይለኛል። መንገዴ ላይ ከሚገጥሙኝ ልጆች ጋር ሰላምታ መለዋወጥ ደስ ይላል!

የፎቶው ባለመብት, Alan Mesfin

ማሰላሰል

አንድ መደበቅ እማልፈልገው ነገር ትግርኛ አልችልም። ግን ትንሽ ትንሽ እሰማለሁ። ቤተሰቦቼ እንግሊዘኛ እያስተማሩ ነው ያሳደጉኝ። ምክንያት ነበራቸው 'ቋንቋችን የት ይሄድብናል' ብለው ይሆናል። ለወደፊቱ ግን ትግርኛ የመማር እቅድ አለኝ።

ለመሆኑ ዋናው ባህሌ የትኛው ነው? ማንነቴስ? ቤተሰቦቼ ኤርትራውያን ስለሆኑ እኔም ኤርትራዊ እሆናለሁ ማለት ነው? እዚያ ስለተወለድኩ ጀርመናዊ ነኝ? እንግሊዝ ስላደግኩ እንግሊዛዊ ነኝ?

እራሴን ከብሔረተኝነት እና ከሀገር ፍቅር ጋር ማስተሳሰር አልችልም፤ አይሆንልኝም። ያንን መንገድ ከተከተልኩኝ የት እንደሚያደርሰኝ ደግሞ አውቀዋለሁ። መጨረሻው 'እኔና እናንተ' የሚለው ነው። ምንጫችንን እያሰብን ብንኮራ ነውር አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ማንም ሰው በስረ መሰረቱ ሊኮራ እንጂ ሊያፍር አይገባውም።

በሌላው በኩል ደግሞ፤ እራሴን የዓለም ልጅ ብየ መጥራት ይከብደኛል። የዓለም ልጅ ነኝ ስል ደስ የሚል ነገር አለው። በውስጤ ጠንካራ ማንነት ወይም ስሜት ግን አይፈጥርልኝም።

እራሴን የዓለም ልጅ ነኝ ብዬ ስጠራ አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ የማልገደብ ያህል ነው የሚሰማኝ፤ ልክ እንደ አንድ ኮብላይ፤ ዝንተ-ዓለሙን ፍለጋ ላይ እንደሚኖር። እና እንዴት ነው እራሴን የዓለም ልጅ ብዬ የምጠራው?

ስለዚህ ለራሴ ስም መስጠት አልፈቅድም! ሰዎች "ከየት ነህ?" ብለው ሲጠይቁኝ አመነታለሁ።

መልሱ ካለሁበት ሁኔታ ጋር ነው የሚሄደው፤ ከኤርትራዊ መሰረቴ፣ ከጀርመናዊ ትውልዴ እና ከእንግሊዛዊ እድገቴ ጋር። በሄድኩበት ቦታ ሁሉ አዲስ ማንነት እጨምርበታለሁ። ስፔናዊ የሥራ ልምድ፣ አዲስ ጃፓናዊ ማንነትን የመሳሰሉትን ያካትታል።

በእኔ ህይወት ውስጥ የተለያዩ ልምዶች ተፅዕኖ አላቸው። የእናትና የአባቴ ልምድ ካልሆነ በስተቀር ስለኤርትራ ልምድ የለኝም።

ስለእራሴ የጀመርኩትን ወግ ላጠናቅላችሁ፤ ከረጅሙ የጃፓን ጉዞ ሦስቱን ወር አገባድጃለሁ። 1700 ኪሎ ሜትሮችን ለ400 ሰዓታት ተጉዣለሁ።

አሁን ኒጋታ የሚባል አካባቢ ሙራካሚ ሲቲ ላይ ደርሻለሁ። ከፊቴ 1300 ኪሎ ሜትር እየጠበቀኝ ነው። ብዙ ለማሰብና ለማሰላሰል እድሉን አገኛለሁ ማለት።