በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞች አሁንም በሳዑዲ እስር ቤት ይገኛሉ

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከሳዑዲ ሲመለሱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ስሜ አይጠቀስ ብሎ አስተያየቱን ለቢቢሲ የሰጠው ግለሰብ ከሁለት አመት በፊት ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲሄድ ነበር ለእስር የተዳረገው። በሳዑዲ ጅዳ ጂዛኔ እስር ቤት ከሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን እስረኞች አንዱ ነው።

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በሳዑዲ ያሉ እስረኞችን ለማስፈታት የመደራደራቸው ዜና ተስፋ ሰጥቶታል። "ዜናው እውን ከሆነ በህይወቴ አዲስ ምዕራፍ ይከፈታል" ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት አርብ ከሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር በኢትዮጵያና ሳዑዲ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙርያ መክረዋል።

ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መሀከልም ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ማስፈታት ይገኝበታል።

በመሪዎቹ ስምምነት መሰረት በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ተለቀው ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሱ ነው።

አስተያየቱን ለቢቢሲ የሰጠው እስረኛ አብረውት እስር ላይ ያሉትን ሰዎች ቁጥር በትክክል ባያውቅም "በግምት ወደ 5,000 የሚሆኑ እስረኞች አሉ" ብሏል።

በእስር ቤቱ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም ስለሚቻል እስረኛውን ያነጋገርነው ወደተንቀሳቃሽ ስልኩ ደውለን ነበር።

"እስከ አሁን ምንም አልተፈረደብኝም" ቢልም እስር ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያውያኑ ከሶስት አመት በላይ መታሰራቸውን ገልጿል።

"ከሁለትና ከሶስት ከአመት በላይ የቆዩ ሰዎች አሉ። ሁኔታው በጣም አስጊና አስፈሪ ነው" ብሏል።

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ወደ ሳዑዲ ያቀኑት የተሻለ ህይወትን በመሻት እንደሆነ ይናገራል። "እዚህ የመጣነው ለእንጀራ ጉዳይ ነው። ለእንጀራ ስንል ተሸውደን እዚህ ገብተናል።" ሲል ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ገልጿል።

"አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሞ ሲታሰር መማር ነው ያለበት እኛ ግን እየተማርን ሳይሆን እየተሰቃየን ነው። መፍትሔ ያስፈልገናል። መፍትሔውንም በደስታ እንቀበላለን" ሲልም ተስፋውን ለቢቢሲ አካፍሏል።

በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት አምባሳደር አቶ ውብሸት ደምሴ በሳዑዲ እስር ቤቶች ከፍተኛ ፍርደኞች የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አሚን አብዱል ቀድር እንደሚናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር ባደረጉት ስምምነት በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ከእስር ተለቀው ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ይገኛሉ።

የተቀሩትም የሚመለሱበትን ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሁለቱ መሪዎች የደረሱበት መግባባት እስረኞቹ እንዲፈቱ ምክንያት ሆኗል ብለዋል። እስካሁን በሁለት ዙር እስረኞች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉን ይናገራሉ።

የሁለቱ የአገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ እንደሆነ የተናገሩት አምባሳደሩ የተጀመረው እስረኞችን የማስፈታት ስራ ጊዜና ትዕግስትን የሚጠይቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

ያነጋገርናቸው በሳዑዲ ጅዛን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞች "ሳዑዲ የሚገኘው የኢትዯጵያ ኤምባሲን እርዳታ ፈልገን በተደጋጋሚ ብንደውልም ምላሽ ተሰጥቶን አያውቅም። አገር እንደሌለን ነው የሚሰማን" ይላሉ።

አምባሳደሩ በበኩላቸው "በሳዑዲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በህግ ጥላ ስር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ክትትል ያደርጋል" ብለዋል።

አምባሳደሩ እንደሚሉት እስረኞቹ የሳዑዲን ህግ ተላልፈው ቢገኙም ምህረት እንዲደረግላቸው በአገር ደረጃ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። "ተገቢውን ምላሽ እየሰጠናቸው ነው። አገራቸው ለዜጎቿ ያላትን ተቆርቋሪነት አሳይተናል" ብለዋል።

እስረኞቹ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጣቸው በመሆናቸው ለማስፈታት መንግስት በጀመረው ሁኔታ በትዕግስት እንደሚቀጥል ተናግረዋል። "የአገሪቱን ህግና ስርዓት በመረዳትና የፍርድ ሂደቶችን በማጣራት በብርቱ ጥንቃቄ መስራትም ያስፈልጋል" ሲሉም አክለዋል።

በተለይም ወደ ሳዑዲ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር መጨመሩ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። አምባሳደሩ እስረኞችን ከማስፈታት ባሻገር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሼክ ሁሴን አሊ አላሙድን ከእስር የማስፈታት ጉዳይም ተነስቶ ነበር።

"በመግባባት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የአገሪቱን ህግና ስርዓት በጠበቀ መልኩ ከሳዑዲ አልጋ ወራሽ ልዑል መሃመድ ኢን ሰልማን ጋር ተወያይተውበታል። ጉዳዩም በቀጣይ እንደሚታይ በሳዑዲ በኩል ማረጋገጫ አግኝተናል" ብለዋል።