ዚምባብዌ የኮመንዌልዝ አገራትን ለመቀላቀል ጥያቄ አቀረበች

የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ

የፎቶው ባለመብት, ALEXANDER JOE

ዚምባብዌ የኮመንዌልዝ አገራት ማህበርን ከለቀቀች ከ15 ዓመታት በኋላ ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል።

የኮመንዌልዝ ዋና ፀሐፊ ፓትሪሺያ ስኮትላንድ እንደተናገሩት ከዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ከጥቂት ቀናት በፊት ደብዳቤ ደርሷቸዋል።

ነገር ግን ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደሚመለሱ ጨምረው ተናግረዋል።

የረጅም ጊዜ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሮበርት ሙጋቤን የተኩት ምናንጋግዋ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ማጠናከር እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ሲገልፁ ነበር።

በኮመንዌልዝ አገራት ድረ-ገፅ ላይ በወጣው መግለጫም የዚምባብዌ ወደ ኮመን ዌልዝ አገራት መመለስም አገሪቷ ከማህበሩ ካላት ታሪካዊ ዳራና ትስስር አንፃር በቅርቡ እውን እንደሚሆን ነው።

53 አባላት ካሉት ኮመንዌልዝ ሀገራት ዚምባብዌ በአውሮፓውያኑ 2003 የተሰናበተች ሲሆን ይህም ከምርጫ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ነው።

ምንም እንኳን የአገሪቱን አባልነት ለመመለስ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ፕሬዚዳንት ሙጋቤ በእምቢተኝነታቸው ፀንተው ነበር።

የኮመንዌልዝ መግለጫ ጨምሮ እንደሚያትተውም አገሪቱ መሰረታዊ የሚባሉ የዲሞክራሲ መርሆችን ማክበር፣ ሰብዓዊ መብትን ማስጠበቅ፣ ራስን የመግለፅ ነፃነትን ማረጋገጥ ሀገሪቷ ከመቀላቀሏ በፊት ልታሟላው የሚገባው ቅድመ-ሁኔታ እንደሆነ ነው።

የኮመንዌልዝ ታዛቢዎችም የዘንድሮውን ምርጫ እንዲታዘቡ ከዚምባብዌ በኩል ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን ይህ ሂደትም መደበኛ ያልሆነው የግምገማው አካል እንደሚሆን ተገልጿል ።

ሌሎች አባላት ሀገራትም በዚምባብዌ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን አስተያየታቸው እንደሚጠየቅ መግለጫው ጨምሮ ያትታል።