"ትጥቅ ትግል ወደ ዴሞክራሲ አያመራም" አቶ ሌንጮ ለታ

አቶ ሌንጮ ለታና አባ ዱላ ገመዳ

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አምስት አባላትን የያዘ ልኡካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ ዛሬ ገብቷል።

የቀድሞ የኦነግ አመራርና የኦዴግ ሊቀ-መንበር አቶ ሌንጮ ለታ ከመንግሥት ጋር ለመወያየት ሙከራ ሲያደርጉ ስድስት ዓመታት እንደፈጀባቸው ተናግረው አሁን ያለውን ለውጥ ተከትሎ ጥሪ ሲደረግላቸው መምጣታቸውን በቦሌ አየር ማረፊያ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አብሮ ለመስራት መወሰናቸውንም ተከትሎ መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው ከግንቦት 7 ጋር ያላቸው ስምምነት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ኦዴግ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ፖርቲ መሆኑን አፅንኦት በመስጠት የተናገሩ ሲሆን ታጣቂ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

"እኛ በሰላማዊ መንገድ የምንንቀሳቀስ ኃይል ነን። አንዳንድ ስለ ትጥቅ ትግል ከሚያወሩ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አለን። ይህ ደግሞ ለአገር እንዲበጅ ለማለት ነው። እንደ ድልድይ እናገለግል ይሆን ወይ ብለን በማሰብ ነው እንጂ ትጥቅ ትግልን ለማበረታታት አይደለም" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጥቷል ብለው የሚያምኑት አቶ ሌንጮ የትጥቅ ትግል አስገዳጅ የሆነበት ሁኔታ እንደሌለ ጠቀሰዋል።

"ትጥቅ ትግል ወደ ዴሞክራሲ አያመራም፤ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገራት ታሪክ ዴሞክራሲን አመንጭቶ አያውቅም" ያሉት አቶ ሌንጮ እርሳቸውም ትጥቅ ትግል ውስጥ እንደነበሩና ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳልመጣ ገልፀዋል።

"ዴሞክራሲን እፈልጋለሁ የሚል ማንኛውም ኃይል በሰላማዊ መንገድ መታገሉን ቢቀበል ይሻላል፤ ሁኔታው አስገድዶኝ ነው ሊል ይችላል፤ ሁኔታው እየተቀየረና እየተሻሻለ ከመምጣቱ አንፃር ትጥቅ ትግል አስፈላጊ እንዳልሆነ መረዳት አለባቸው።" ብለዋል።

ፓርቲውም ሆነ መስራቾቹ ለዓመታት መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ከማድረጋቸው አንፃር የወደፊቱን የፖለቲካ አቅጣጫ ለመቀየስ እንዲሁም ተሳትፏቸው ምን መልክ እንደሚኖረው ለማወቅ ጥናት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"አገሪቱ በኢኮኖሚም፣ በፖለቲካው ሆነ በማህበረሰቡ በአፋጣኝ ሁኔታ እየተቀየረች ነው። ካጠናን በኋላ ነው ወደ ስራ ዕቅድ ማውጣት የምንሸጋገረው" ብለዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ከመንግሥት ጋር የደረሱባቸው የድርድር ነጥቦች ይኖሩ ይሆን ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም ያደረጉት ድርድር አመጣጣቸው ብቻ ላይ እንዳተኮረ ገልፀዋል።

ወደ አገሪቷም ለመመለስ መፈታት የነበረባቸው ችግሮች እንደነበሩም ጨምረው ተናግረዋል።

" ሰፋፊና አነታራኪ የፖለቲካ ጉዳዮች አልተነሱም፤ እነሱን እዚህ አንስተን እንወያይባቸዋለን " ብለዋል

ከመንግሥት ጋር ጠለቅ ያለ የፖለቲካ ውይይት ለማካሄድ እንደሚያስቡ የተናገሩት አቶ ሌንጮ የፖለቲካ አቅጣጫቸውንም ለመቀየስ ያለውንም ለውጥ ደካማና ጠንካራ ጎኑን መፈተሽ ከቀዳሚ ስራዎቻቸው መካከል እንደሆነ ተናግረዋል።

"ያለውን ለውጥ ደካማና ጠንካራ ጎን ከፈተሽን በኋላ እንዲሁም ከመንግሥት ጋር ውይይት ካደረግን በኋላ እኛ አስተዋፅኦ የምናደርገው በምን መልክ ነው የሚለው ላይ እንወስናለን" ብለዋል።

ከመጡ በኋላስ አቀባበል ይጠብቁ እንደሆነ ለተጠየቁት ጥያቄ "እኛ ከሀገር ከወጣን አንድ ትውልድ ተወልዷል። አያውቀንም አቀባበል እንጠብቃለን ብየ አላስብም" ብለዋል።

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርን (ኦነግ) ጨምሮ ግንቦት ሰባት፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና ሌሎች ፓርቲዎች በኢፌዴሪ መንግስት አሸባሪ ተብለው መፈረጃቸው የሚታወስ ነው።

የግንባሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሌንጮ ለታ እና አንዳንድ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የአመራር አባላት የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር አባላት እንደነበሩ ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች