የዳቦና የወተት እጥረት በአዲስ አበባ

የዳቦ እጥረት በአዲስ አበባ Image copyright FEDERICO PARRA

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአዲስ አበባ የዳቦ መጋጋሪያና ማከፋፈያ ደጃፎች ረጃጅም ሰልፎችን ሲያስተናግዱ ሰንብተዋል።

በሌላ በኩል የሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ መደብሮችም ከሁለት በላይ የታሸጉ ወተቶችን እንደማይሸጡ የሚደነግጉ ማስታወቂያዎችን ለጥፈው ተስተውለዋል፥

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ችግሩ ባለፈው ሚያዝያ ወር ቢስተዋልም በያዝነው ግንቦት ወር ግን ተቀርፏል ባይ ነው።

በመዲናይቱምና በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎችም የትንሳዔ በዐልን ተከትሎ የሚፈጠረውን ከፍተኛ ፍላጎት ማስተናገድ የሚችል ምርት ማቅረብ ካለመቻሉ ጋር በተያያዘ፤ የወተት እጥረት ማጋጠሙ እንግዳ እንዳልሆነ በአንድ ወተት ማቀነባበር እና ማሰራጨት ስራ ላይ የተሰማራ ኩባንያ ኃላፊ ይናገራሉ።

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኤልያስ በየነ ችግሩን ያባበሰ ሌላ ምክንያትን ጨምረው ያነሳሉ፤ የስንዴ አቅርቦት እጥረት።

የአቅርቦት እጥረቱ ከመንግስት የድጎማ ስንዴ የሚያገኙ ዳቦ መጋገሪያዎችን ከምርታቸው እስከ ግማሽ የሚደርስ ያህሉን እንዲቀንስ ከማስገደዱም በተጨማሪ በእንስሳት መኖ ምርት ላይም ጫና አሳርፏልም ይላሉ።

"ባለፈው ሚያዚያ ወር በመንግስት ድጎማ ከሚቀርቡ የሸቀጦች አንዱ የሆነው የስንዴ ምርት፤ መንግሥት በሚያቀርበው ልክ በተሟላ መልኩ ባለመቅረቡ ችግር ተከስቷል" ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ ኤልያስ እጥረቱ "በተወሰኑ በድጎማ ላይ በተመሰረቱ ፋብሪካዎች ላይ" ጫና ማሳደሩንና ይህም በዳቦ ከገበያ መጥፋት መተርጎሙን ያስረዳሉ።

ዳቦው በሚገኝበት ጊዜ ዋጋው ጨምሮ እና መጠኑ አንሶ እንደሚገኝ አስሩን ክፍላተ ከተማዎቹ ተዟዙሮ ያጠናው የንግድ ቢሮው ግብረ ኃይል እንደደረሰበትም አቶ ኤልያስ ይገልፃሉ።

"መንግስት የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ህይወት ለማቅለል እና የኑሮ ውድነቱን ለማስታገስ የሚያቀርበው የድጎማ ምርት ጊዜን ጠብቆ መድረስ ነበረበት። ከግዥ ጋር ተያይዞ ትንሽ የመዘግየት ሁኔታ ሲከሰት፥ ችግሩ እንደሚፈጠር ይታወቃል" ይላሉ አቶ ኤልያስ።

እርሳቸው የስንዴ አቅርቦት እጥረቱ ከግዥ ስርዓት ጋር እንደሚያያዝ ይናገሩ እንጅ፤ የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አገልገሎት ዋና ዳይሬክቶር የሆኑት አቶ ይገዙ ዳባ ግን የአቅርቦት ችግር ለዳቦ እጥረት ምክንያት ሆኗል በሚለው አስተያየት አይስማሙም።

አቶ ይገዙ መስሪያ ቤታቸው ግዥውን ያከናወነበት አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ጅቡቲ ወደብ ላይ ይገኝ እንደነበርና የስንዴ እጥረት ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ፤ እርሱን በአስቸኳይ ወደአገር ውስጥ ማስገባት ይቻል እንደነበር ይከራከራሉ።

"ችግሩ ቢኖር ኖሮ ይህንን በአስቸኳይ ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ችግሩን በአስቸኳይ ለመፍታት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ነበር። ተገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ አለን" ሲሉ ዳይሬክተሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ተጨማሪ ግዥዎች መኖራቸውን አይደብቁም።

"ያም ሆነ ይህ የስንዴ ችግርን በአስቸኳይ ለመፍታት ከዚህ በፊት አራት መቶ ሺህ ሜትሪክ ቶን ገዝተን ነበር፤ ከዚህ በተጨማሪ ሁለት መቶ ሺህ ሜትሪክ ቶን (ሁለት ሚሊየን ኩንታል) በአስቸኳይ እንዲገባ ፕሮሚሲንግ ከሚባል ድርጅት ጋር ውል ተፈራርመናል" ይላሉ አቶ ይገዙ።

የፊታችን አርብ በሚከፈት ሌላ ጨረታ የሁለት መቶ ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሚፈለገውን ምርት ስርጭት ተግባራዊ ከማድረግም በዘለለ ከዱቄት እና ዳቦ አምራቾች ጋር ውይይት አድርጌያለሁ ይላል።

የስርጭት ችግር፣ የዳቦ እጥረቱን ዘለግ ላለ ጊዜ እንዲቆይ ሳያደርገው እንዳልቀረ የሚገምቱት አቶ ኤልያስ፤ "አጋጣሚውን ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት" ተጠቅመውበታል የተባሉ አምራቾች እና ነጋዴዎች መደብሮች መታሸጋቸውን ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል መንግሥት ስንዴ ከውጭ እየገዛ ድጎማ ያስፈልጋቸዋል በሚል በርካሽ ዋጋ ማቅረቡ የአገር ውስጥ ምርታማነትን አያበረታታም ሲሉ የሚከራከሩት በጉዳዩ ላይ ጥናት ያካሄዱት የምጣኔ ኃብት ባለሞያው ዶክተር ደምስ ጫንያለው ናቸው።

በተፈጥሯዊ የአየር ሁኔታ ምክንያቶች በአገር ውስጥ ምርት ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ መሸፈን የማይቻልበት አጋጣሚ ሲፈጠር፤ የአገሪቱን የምግብ ዋስትናን ለማስጠበቅ ከውጭ ሃገራት ግዥን መፈፀሙ የሚጠበቅ ብሎም የሚወደስ ተግባር መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር ጫንያለው፥፤ ለዚህም ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት አንስቶ ኤል ኒኖ የሚል ስያሜ በተሰጠው ተፈጥሯዊ የአየር መዛባት ምክንያት የተከታታይ ወቅቶች የዝናብ እጥረት ባጋጠመበት ወቅት የተወሰደውን መንግስታዊ የግዥ እርምጃ በአብነት ያነሳሉ።

ሆኖም ይህ ነው የተባለ መሰል የምርታማነት ችግር በሌለበት ጊዜ ሁሉ ስንዴን ከውጭ የማስገባት እንቅስቃሴ እንደፖሊሲ የሚያዝ መሆን የለበትም ባይ ናቸው።

"መደጎምም ካለበት ከእኛው ገበሬዎች ነው መገዛት ያለበት" ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ ከውጭ በሚገዙ ምርቶች ዘንድ የአስፈላጊነት ቅደም ተከተል እንዲፈጥር አድርጎታል።

ስንዴ እንደሌሎች ስኳርን እንደመሳሰሉ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ሁሉ ቅድሚያን ማግኘቱ የሚጠበቅ መሆኑን የምጣኔ ኃብት ባለሞያው ዶክተር ደምስ ይገልፃሉ።

ስንዴን ከውጭ ከመግዛት ጋር በተያያዘ አሁን በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ደንቃራ ፈጥሮ እንደሁ የተጠየቁት የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ኃላፊው አቶ ይገዙ በአሉታ ይመልሳሉ።

"ምክንያቱም ስንዴውን በምንገዛበት ወቅት የስድስት ወር የዱቤ አገልግሎት አለ። ገንዘቡን የምንከፍለው ስንዴው ከገባ ከስድስት ወር በኋላ ነው። ስንዴው ከገባ በኋላ ክፍያ ላይ የሚያጋጥም ነገር ካለ ያኔ የሚታይ ነው የሚሆነው። " ብለዋል።