"ልጅ" ማይክል በ30 ዓመቱ ከወላጆቹ ጋር በመኖሩ ክስ ተመሠረተበት

ማይክል ሮቶንዶ ማክሰኞ ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ
የምስሉ መግለጫ,

ማይክል ሮቶንዶ ማክሰኞ ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ

ልጅ በስንት ዓመቱ ከቤት ወጥቶ ራሱን መቻል ይኖርበታል?

በኒውዮርክ በ30 ዓመቱ የወላጆቹን ቤት የሙጥኝ ያለው ጎልማሳ በገዛ ወላጆቹ መከሰሱ ተሰምቷል።

አባትና እናት ልጃቸው ራሱን ችሎ ከቤት እንዲወጣ ያደረጉት ውትወታና ተከታታይ ጥረት ፍሬ አላፈራም። የመጨረሻው አማራጭ ለፍርድ ቤት መክሰስ በመሆኑ ይህንኑ ጨክነው አድርገውታል።

ልጃቸው 30ኛ ዓመቱን ቢደፍንም አሁንም ከወላጆቹ ጋር ነው የሚኖረው።

የፍርድ ቤት መዝገብ እንደሚያስረዳው የ30 ዓመቱ "ልጅ" ማይክል የቤት ኪራይ አይከፍልም። በዚያ ላይ ደግሞ ቀለል ያሉ የቤት ውስጥ ሥራዎችን (እገዛዎችንም) አያደርግም። ወላጆቹ ራሱን ችሎ ቤት እንዲከራይ የድጎማ ገንዘብ ቢሰጡትም በጄ አላለም።

ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ክርስቲና እና አባቱ አቶ ማርክ ሮቶንዶ እንደሚሉት ልጃቸው ቤታቸውን እንዲለቅ አምስት ግልጽ ደብዳቤዎችን በተለያየ ጊዜ ሰጥተውታል።

"ልጅ" ማይክል ግን "ከቤት እንድለቅ በቂ ጊዜ አልተሰጠኝም" ይላል።

ለኦኖንዳጋ አውራጃ ፍርድ ቤት ክስ የመሠረቱት ወላጆቹ ልጃቸውን ከቤት ወጥቶ ራሱን እንዲችል ያደረጉት ሙከራ ውጤት ሊያመጣ ስላልቻለና ሌላ ምን ማድረግ እንደሚቻል ግራ ስለገባቸው ነው ወደ ፍርድ ቤት ያቀኑት ተብሏል።

"እኛ አባትና እናትህ ይህንን የወላጆችህን ቤት በአስቸኳይ እንድትለቅ ወስነናል" ይላል በየካቲት 2 የተጻፈ የመጀመርያው ደብዳቤ።

ማይክል ይህን ደብዳቤ ችላ ካለ በኋላ ወላጆቹ በጠበቃቸው አማካኝነት ለልጃቸው ሌላ መደበኛ ደብዳቤ እንዲደርሰው አድርገዋል።

"ልጄ ሆይ! ከዚህ በኋላ ከዚህ ቤት ተባረሃል" ይላል በየካቲት 13 በእናቱ ፊርማ የወጣ አንድ ደብዳቤ፤ ይህን የማያደርግ ከሆነ ግን በሕግ እንደሚጠየቅ ከሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ጋር።

ወላጆቹ ከዚህ ደብዳቤ በኋላ ለልጃቸው መቋቋሚያ እንዲሆነው በሚል 1100 ዶላር ያበረከቱለት ሲሆን እሱ ግን ገንዘቡን ለመውሰድም ፍላጎት አላሳየም።

በመጋቢት ወር ወላጆቹ ወደ ክፍለ ከተማው ፍርድ ቤት ሄደው ጉዳዩን ያሳወቁ ሲሆን የፍርድ ቤቱ የመዝገብ ቤት ኃላፊዎች ማይክል ልጃቸው በመሆኑ ውሳኔያቸውን ለማስፈጸም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ደብዳቤ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጾላቸዋል።

ደብሊው ኤቢሲ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው "ልጅ" ማይክል የወላጆቹን ክስ "የበቀል ስሜት ያዘለ" በሚል አጣጥሎታል። ፍርድ ቤቱም እንዳይቀበለው አሳስቧል።

ወላጆቹ ግን ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ቀጠሮ ይዘዋል። ይህ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በሚመለከትበት ወቅት "ልጅ" ማይክል 31ኛ ዓመቱን ለመድፈን ይቃረባል።