"አፍሪካዊ አይቶ ለማያቀው ቤተሰቤ ኬንያዊ ማግባቴ ችግር ነበር"

ዡ ጂንግና ሄንሪ በፍቅር የተሳሰሩት ከአስር ዓመታት በፊት ነበር

ቻይናዊቷ ዥሁ ጂንግ ምንም እንኳ ከኬንያዊ ባለቤቷ ጋር ቢፋቀሩም ግንኙነታቸው መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ እንደነበር ትናገራለች።

"ቤተሰቦቼ ስለ አፍሪካ ብዙ አያውቁም ነበር። ኬንያዊ አይተው ስለማያውቁም መጀመሪያ ተጨንቀው ነበር" ትላለች።

ኬንያዊው ሄንሪ ሪቶችም በነገሩ ጭንቀት ገብቶት ነበር።

ጥንዶቹ በፍቅር የወደቁት የመንግሥት ተቀጣሪው ሄንሪ ማንዳሪን ለማጥናት ወደ ቻይና በሄደበት ወቅት ነበር።

ከቤተሰቦቿ ጋር ለመተዋወቅ በደንብ የማንዳሪን ቋንቋ መናገር እስኪችል መጠበቅ ነበረበት።

ዛሬ ከአስር ዓመት በኋላ ጥንዶቹ ሁለት ልጆች አፍርተው በኬንያ መዲና ናይሮቢ ከትመዋል።

ጂንግ አስር ሺህ የሚገመቱ ቻይናዊያን እንደሚኖሩ በሚገመትባት ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የማንዳሪን ቋንቋ ታስተምራለች።

የጂንግና የሄንሪ የግንኙነት ታሪክ ስኬታማ ቢሆንም የቻይናና የኬንያ ግንኙነት ግን ቀላል ሆኖ አያውቅም የሚል እምነት ያላቸው ብዙዎች ናቸው።

ለምሳሌ ናይሮቢን ከኢንዱስትሪ ከተማዋ ቲካ ከሚያገናኘው አዲስ የመንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘ ቻይኖች ከብዙ ኬንያዊያን ሴቶች የመውለዳቸው ነገር "ቲካ ቤቢስ" እየተባለ ይነሳል።

እንደሚባለው ከሆነ የመንገዱ ግንባታ ላይ ይሰሩ የነበሩ ቻይናዊያን ከአካባቢው ሴቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጆችን ወልደዋል።

አንዲት ተማሪ ግንባታው ላይ ይሰራ ከነበረ ቻይናዊ ወልዳ በመጨረሻ ግለሰቡ ማን እንደሆነ እንድትለይ ስትጠየቅ ግንባታው ላይ ተሰማርተው ከነበሩት ቻይናዊያን መካከል መለየት እንዳቃታት ተዘግቦም ነበር።

ሄንሪ በኬንያዊያን ዘንድ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሌላውን አዘውትሮ መጠየቅ ብሎም ከዘመድ ቤት መሰነባበት የተለመደ ቢሆንም፤ በቻይናዊያን በኩል ግን የእዚህ አይነቱ ነገር አለመኖሩን እንደ አንድ ልዩነት ያነሳል።

"ቻይናዊያን ቤተሰብ ሊጠያየቅ ይችላል። ዘመድ ሌላው ዘመድ ቤት የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ሲሆን በተለይም ከቅርብ ዘመድ ውጪ የመቀራረብ ነገርም ብዙ የለም"ይላል።

በኬንያ የቻይና ኩባንያዎች አማካሪ የሆነው ጂንሁዋ ዛሬም በሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት መካከል ችግሮች መኖራቸውን ይናገራል።

"ሁሉም ናቸው ብዬ መደምደም አልፈልግም ግን ኬንያዊያን ነገሮች ላይ ዝግ ይላሉ። ተሰባስቦ መደሰት ይወዳሉ ይህ በቻይናዊያን ዘንድ የለም" ይላል።

"ቻይናዊያን ወደዚህ ሲመጡ የመጨረሻ ግባቸውን አስበው ነው።ረዥም ሰዓት ቅዳሜና እሁድን ሁሉ ሊሰሩ ይችላሉ።ረፍታቸው ውስን ነው።የሚፈልጉት ፕሮጀክቶቻቸው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ ነው።"ይላል።

ጥንዶቹ ጂንግና ሄንሪም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።

ቢሆንም ግን ኬንያዊያን በጥቅሉ አፍሪካዊያን እየተቀየሩ እንደሆነ ይናገራል ሄንሪ።

በሌላ በኩል ብዙ ቻይናዊያን ወደ ኬንያ እየመጡ በመሆናቸው በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው የባህል ልዩነት እየጠበበ እንደሆነ የሚናገሩም አሉ።

በዚህ ረገድ የቻይና መንግስት ድጋፍ የሚያደርግለትና ጂንግ ማንዳሪን የምታስተምርበት ተቋም የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት የተሻለ በማድግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ይታመናል።

በተቋሙ ማንዳሪን የሚማሩ ኬንያዊያን ወደ ፊት ቻይና ሄደው የተሻለ ስራ ስለማግኘት ያልማሉ።ቻይና እንደ አገር ደግሞ ከኬንያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የማጥበቅ ፍላጎት እንዳላት ትገልፃለች።