"የአርባ ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ጥቅም የሚያስከብር ሥራ ተሰርቷል" የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የፕሬዝዳንት ካጋሜ እና የጠ/ሚኒስትር አብይ ፎቶ በአዲስ አበባ ጎዳና
የምስሉ መግለጫ,

የፕሬዝዳንት ካጋሜ እና የጠ/ሚኒስትር አብይ ፎቶ በአዲስ አበባ ጎዳና

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተለያዩ ሃገራት ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ አርባ ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያንን ጥቅም የማስከበር ሥራ መሰራቱን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ገለፁ።

በተጨማሪም በተለያዩ ሃገራት እስር ቤቶች ውስጥ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ነፃ እንዲወጡ መደረጉን ይህም በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያላሰለሰ ጥረትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ድጋፍ እንደሆነ ቃል አቀባዩ ጨምረው አመልክተዋል።

ቃል አቀባዩ እነዚህ ሁሉ ተግባራት የተከናወኑት በመንግሥት በኩል ካለው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ጥናትን መሰረት አድርጎ መሆኑን አመልክተዋል። ይህም እስረኞችን ከማስለቀቅ ባሻገር በውጪ ሃገር ያሉ ዜጎች ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኙ ጥረት ማድረግን ይጨምራል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያን በመጎብኘት የመጀመያው ይሆናሉ የተባሉት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር የሆኑት ፕሬዝዳንቱ ካጋሜ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቀረበላቸው ግብዣ ነው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቀደም ሲል በተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባል ሆነው ሩዋንዳ ውስጥ መስራታቸው ይታወሳል።

አቶ መለስ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ባሉ የኢትዮጵያ ተልዕኮዎች ውስጥ ተሰማርተው የነበሩ አምባሳደሮችን መጠራትና ወደሌሎች ሃገራት መዘዋወርን በተመለከተ እንደገለፁት፤ በዋናነት ስኬታማ ሥራን ለማከናወንና ክፍት የሆኑ ቦታዎችን ከማሟላት ውጪ ሌላ ምክንያት እንደሌለው ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝትን ተከትሎ ከእስር የተለቀቁ ዜጎች ወደ ሃገራቸው መመለስ ጀምረዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የያዘ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ገልፀዋል።

የምስሉ መግለጫ,

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም