ሞርጋን ፍሪማን በፆታዊ ትንኮሳ ለቀረበባቸው ውንጀላ ይቅርታ ጠየቁ

ሞርጋን ፍሪማን Image copyright PA

ዝነኛው አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ ከስምንት ሴቶች በላይ ፆታዊ ትንኮሳ አድርሶብናል የሚለውን ውንጀላ ተከትሎ ይቅርታ ጠይቀዋል።

"ጎይንግ ኢን ስታይል" የተሰኘው ፊልም ቀረፃ አስተባባሪ የነበረች አንዲት ሴት ለወራት ያህልም ትንኮሳ እንዳደረሰባት ሲኤንኤን በዘገባው አስነብቧል።

የ80 ዓመቱ ዕድሜ ባለፀጋ በተደጋጋሚ ያለፍቃዷ እንደነኩዋት፣ ቀሚሷን ሊገልቡ እንደሞከሩና የውስጥ ልብስም አድርጋ እንደሆነ ይጠይቋት እንደነበር አስታውቃለች።

ሞርጋን ፍሪማን በበኩላቸው "ምቾት ለተነሱና ክብር ለተነፈጉት" ይቅርታን ለግሰዋል።

በመግለጫቸው ጨምረው " የሚያውቀኝ ሰው ሁሉ የሚመሰክረው እኔ አውቄ ሰዎችን ማስቀየምም ሆነ ምቾት እንዲነሱ አላደርግም" ብለዋል።

"ሴቶችን ምቾት መንሳት መቼም ቢሆን አላማየ አይደለም" ብለዋል።

በሆሊውድ ውስጥ በፆታዊ ትንኮሳ ሲወነጀሉ ከሀርቬይ ዌይንስቴይን ቀጥሎ ሞርጋን ፍሪማን ሌላኛው ዝነኛ ሰው ሲሆኑ በተለይም የብዙ ፊልሞች ባለቤት የሆኑት ሀርቬይ ዌይንስተን ያደረሱትን ወሲባዊ ጥቃትም ተከትሎ በዓለም አቀፍ ዘንድ ሚቱ (#Me Too) የሚል ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው።

ይህች የፊልም ቀረፃ አስተባባሪ የፆታዊ ትንኮሳ ደርሶብኛል ብለው ለሲኤኤን ከተናገሩት ከስምንቱ ሴቶች አንዷ ናት።

በወቅቱም አለን አርኪን የተባለው ሌላኛው ተዋናይ ለሞርጋን ፍሪማን "ትንኮሳቸውን እንዲያቆሙ በነገሯቸው ወቅት እንደደነገጡና ምንም ማለት እንዳልቻሉ" ተናግራለች።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ አውሮፓውያኑ 2013 በወጣው "ናው ዩ ሲ ሚ' (Now You See Me) በሚቀረፅበት ወቅት "ሴቶች ጡታችንን እንዲሁም ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻቸችን የሚያጋልጥ ልብስ እሳቸው ባሉበት እንዳንለብስ ሰራተኞቹ ይነግሩን ነበር" ብላለች።

በተቃራኒው ሲኤኤን የስራ ባልደረቦቻቸውን አናግሮ ሞርጋን ፍሪማን ሁልጊዜም ለስራቸው የሚተጉና ባህርያቸውም ባለሙያነትን የተላበሰ እንደሆነ ዘግቧል።