በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝና ኦሮምኛ ቋንቋዎች ጥናት ፍላጎት ጨምሯል

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
የምስሉ መግለጫ,

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

የግዕዝና ኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት መስጠት የጀመረው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከጠበቀው የላቀ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ማግኘቱ ተገልጿል።

በሁለተኛ ዲግሪ ለአስራ አራት ተማሪዎች መስጠት በጀመረው የግዕዝ ቋንቋና ሥነ-ፅሁፍ ትምህርት፤ የኢትዮጵያን ጥንታዊና መካከለኛው ዘመን የተደበቀ የዕውቀት ጥሪት የመፈልቀቅ፤ የጥናት በርም የመክፈት ግብ እንዳለው ተመልክቷል።

ፍላጎት ላላቸው የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች መሰጠት የጀመረው የኦሮምኛ ቋንቋ ስልጠናም በርካቶችን እንደሳበ ተገልጿል። ቋንቋው በመደበኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜ፤ በመጀመሪያ ዲግሪ በሚቀጥለው ዓመት መሰጠት ይጀምራል።

የዩኒቨርሲቲው የሥነ-ሰብ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ዳዊት አሞኘ ለቢቢሲ እንደገለፁት የግዕዝ ቋንቋና ሥነ-ፅሁፍ በሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ተገቢውን ግምገማ ያለፈው ከወራት በፊት ሲሆን አሁን በተያዘው ሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ጸድቆ ወደተግባር ተገብቷል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በልዩ ልዩ የትምህርት ዘርፎች የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙና መሠረታዊ የግዕዝ ዕውቀት ያላቸው አርባ ዕጩ ተማሪዎች ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቋንቋው ለመስራት ቢመዘገቡም፤ ከዩኒቨርሲቲው የአቅም ውስንነት አንጻር ሲሶውን ብቻ ተቀብሎ ማስተማር ጀምሯል።

"የትምህርት ክፍሉ ዋነኛ ዓላማ በጥንታዊና በመካከለኛው የኢትዮጵያ የስልጣኔ ዘመን የነበሩ ብዙም የማይታወቁ የህክምና፣ የትምህርት፣ የፍልስፍና፣ የባህል፣ የሥነ-ልቦና፣ የእምነት እንዲህም የአስተዳደር ዕውቀቶችን መዳሰስና ለጥናት በር መክፈት ነው" ሲሉ ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በበቂ ሁኔታ የግዕዝ መምህራን አለማግኘት ቀዳሚው ፈተናቸው መሆኑን የሚያስረዱት ዶክተር ዳዊት "ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራን ነው" ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ኦሮምኛ ማስተማር የጀመረው በአጫጭር ስልጠና መልክ ሲሆን፤ የተማሪዎቹ የቋንቋ ብቃት ታይቶ የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል ተብሏል።

የመጀመሪያውን ስልጠና የሚወስዱ ተማሪዎች ቁጥር ሃምሳ ገደማ ሲሆን መማር የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር መብዛት ግን ተጨማሪና ተከታታይ ስልጠናዎች እንዲኖሩ እንደሚያስገድድ ዶክተር ዳዊት ይናገራሉ።

ዩኒቨርሲቲው በሚቀጥለው ዓመት በኦሮምኛ ቋንቋ መደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት መስጠት የሚጀምር ሲሆን አሁን የከፈተው ኢ-መደበኛ የስልጠና መርሃ ግብር የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ላይ ያተኮረ ነው።

"ለስልጠናው ጥሪ ስናቀርብ በርካታ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ አስተዳደሪዎች፣ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች ፍላጎት አሳይተው መማር ጀምረዋል" ይላሉ ኃላፊው።

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኦሮምኛ ቋንቋ በዲግሪ ደረጃ ሊያስተምር እንደተሰናዳ ከተዘገበበት ጊዜ አንስቶ፤ የቋንቋ ትምህርት በግዕዝ ሆሄያት ይሰጥ ዘንድ ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖች ነበሩ።

ይህን መሰሉ እርምጃ ተማሪዎቹን ከጠቅላላ የቋንቋው ተናጋሪ ማህበረሰብ የሚነጥል መሆኑን በማውሳት እንደማይቀበሉት ዶክተር ዳዊት ይገልፃሉ።

"ለውጥ የሚያስፈልግ ከሆነ የቋንቋው ባለቤቶች ከተናጋሪው ህብረተሰብ ጋር መክረው ካልለወጡት በስተቀር፤ በአንድ ቋንቋ ውስጥ ሁለት የተለያየ የአፃፃፍ ስርዓት የለም" ይላሉ።