በእባብ በመነደፍ ሳቢያ በመቶ ሺዎች እንደሚሞቱ ተገለፀ

እባብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም የጤና ድርጅት በእባብ በመነደፍ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎች ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ውሳኔ አስተላላፈ።

በዚህ ምክንያት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፤ ብዙዎችም ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል።

"በእባብ መነደፍ የሚመጡ ውስብስብ የጤና ችግሮች ችላ ከተባሉት የቆላ በሸታዎች መካከል አንዱ ነው" ሲል የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።

ውሳኔውን የተቀበሉት የዓለም የጤና ድርጅት አባል አገራት ችግሩን ለማስወገድ ቀድሞ በመከላከል፣ በመቆጣጠርና ህክምናውን በመስጠት ረገድ ተመሳሳይ የአተገባበር ሒደት ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።

የጤና ጉዳይ ተሟጋች ቡድኖች በበኩላቸው ውሳኔው መተላለፉ ያስደሰታቸው ሲሆን "በዓለም አቀፍ ደረጃ በእባብ በመነደፍ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ እንዲሁም አካል ጉዳትን ለመከላከል ትልቅ ርምጃ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ቅድመ መከላከል ላይ ለመስራት፣ ህክምናውን ለመስጠት፣ እንዲሁም የማገገሚያ ፕሮግራሞችን ለማከናወን የመተግበሪያ ዕቅድ ለማውጣት ሃላፊነቱን ወስዷል።

ይህም ለበርካታ አገራት በተለይም ከሰሃራ በታች ለሚገኙ ድሃ አገራት ርካሽና ውጤታማ የሆነ የእባብ መርዝ ማርከሻ መድሃኒት ተደራሽ ማድረግን የሚያካትት ነው።

በድህነት ምክንያትና በቂ የጤና ተቋማት ባለመኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገቢው ህክምና ሳይደረግላቸው ህይወታቸው አልፏል።

ሌሎች ደግሞ ምንም ዕውቀቱ ወደ ሌላቸው የልምድ ሐኪሞች ጋር በመሄድ ለበለጠ ጉዳት ተዳርገዋል።

አዲሱ መላ ለጤና ባለሙያዎች የእባብ መነደፍን በምን መልኩ ሊያክሙ እንደሚችሉ፤ እንዲሁም ችግሩ በአብዛኛው በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ስልጠና መስጠት ላይ ትኩረት ያደርጋል።

በዓለም በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእባብ ተነድፈው ይሞታሉ። ከእነዚህ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት ከአፍሪካ አገራት ናቸው።

በእባብ በመነደፋቸው ምክንያት ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን አጥተዋል፤ ሌሎች የአካል ጉዳቶችም አጋጥመዋቸዋል። ይህም የጤና አገልግሎት ፍላጎቱን ከፍ እንዲል አድርጎታል።