የኢጣሊያ ፕሬዝዳንት እንዲከሰሱ ተጠየቀ

ፕሬዝዳንት ሰርጊዮ ማታሬላ, May 27 2018
የምስሉ መግለጫ,

ፕሬዝዳንት ሰርጊዮ ማታሬላ ከፋይናንስ ሚኒስትሩ በስተቀር የቀረቡትን እጩዎች በአጠቃላይ ተቀብያለሁ ብለዋል

የጣሊያን ትልቁ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ለፋይናንስ ሚኒስትርነት ያቀረቧቸው ግለሰብ በፕሬዝዳንቱ ደምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ውድቅ ካደረጉ በኋላ እንዲከሰሱ ጥሪ አቀረቡ።

ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የፋይቭ ስታር ፓርቲ መሪው ሉኢጊ ዲ ማዮ እንዳሉት ፕሬዝዳንት ሰርጊዮ ማታሬላ "ተቋማዊ ቀውስ አምጥተዋል" ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

እሁድ እለት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ለመመስረት የተደረገውን ጥረት ፕሬዝዳንቱ የአውሮፓ ሕብረትን የማይደግፈውን እጩ ፓውሎ ሳቮናን ውድቅ አድርገዋል።

ፋይቭ ስታር ከቀኝ ክንፉ ሊግ ጋር መንግስት ለመመስረት ጥረት እያደረገ ነው።

ጣሊያን ባለፈው መጋቢት በተካሄደው ምርጫው የትኛውም ፓርቲ አብላጫ ድምፅ ስላላገኘ መንግስት ሳትመሰርት ቆይታለች።

የምስሉ መግለጫ,

ሉዊጊ ዲ ማዮ ጣሊያን ተቋማዊ ቀውስ ገጥሟታል ብሏል

ኮንቴ አሁን የወረዱ ሲሆን ፕሬዝዳንት ማታሬላ ከቀድሞው የአይ ኤም ኤፍ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ጋር የተፈጠረውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ይሸፍናሉ በማለት እየተነጋገሩ እንደሆነ መረጃዎች አሉ።

ነገር ግን ሮም የሚገኘው የቢቢሲው ጀምስ ሬይኖልድስ እንደሚለው እንዲህ አይነት ንግግሮች የመሳካት እድላቸው አናሳ ነው እናም ሌላ ምርጫ ሊጠራ ይችላል ብሏል።

አሁን በፕሬዝዳንቱ እና በፓርቲዎቹ መካከል ጣሊያን በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ባላት ቦታ ላይ እሰጥ አገባ መኖሩንም አልሸሸገም።

ዲ ማዮ ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ይውረዱ ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት ሕገ መንግስቱን ጠቅሰው ነው። ይህ የሕገ መንግስት አንቀፅ ደግሞ በአብላጫ ድምፅ ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ማውረድ እንደሚቻል ይደነግጋል።

የሕዝብ እንደራሴዎቹ የሚሰጡት ድምፅ ይውረዱ የሚለውን የሚደግፍ ከሆነ የሐገሪቱ ሕገመንግስታዊ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ብያኔ ይሰጣል።

ዲ ማዮ "ይህ ተቋማዊ ቀውስን የሕዝብ እንደራሴዎቹ እንዲመለከቱት እፈልጋለሁ።...." ብለዋል።

"ከዚህ ምሽት በኋላ ባለን ተቋማትና በሀገሪቱ ህግ መተማመን ከባድ ሆኗል" በማለት አዲስ ምርጫ እንዲደረግ የጠየቀው ደግሞ የሊጉ መሪ ማቲዮ ሳልቫኒ ነው።

ለ11 ሳምንት የዘለቀውን የፖለቲካ ቅርቃር መፍትሔ ለመስጠት በማሰብ ለፖለቲካው አዲስ የሆኑት ሚስተር ኮንቴ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በእጩነት ቀረቡ።

እርሳቸውም ለፕሬዝዳንቱ የካቢኔ አባሎቻቸውን ለማቅረብ በሄዱበት ፕሬዝዳንቱ ፓኦሎ ሳቮናን አውሮፓ ህብረት ላይ ያለውን ጠንካራ ተቃውሞ በመጥቀስ ከፋይናንስ ሚኒስትርነት እጩነት ውድቅ አደረጉ።

"በፓርላማው አብላጫ ድምፅ ካለው መካከል ከመንግስት ፕሮግራም ጋር የሚሄድ ጠንካራ አቋም ያለው ሰው ከአውሮፓ ሕብረት መውጣትን የማይደግፍ እንዲያመጡ ጠየኩ " ሲሉ ተናግረዋል፣ ማታሬላ።

አክለውም ኮንቴ የትኛውንም የመፍትሔ ሃሳብ በመቃወም ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን በቃኝ ማለታቸው ገልፀዋል።

በጣሊያን ሕግ ፕሬዝዳንቱ የካቢኔ አባላቶችን ምርጫ ውድቅ ማድረግ የሚችል ቢሆንም ውሳኔ ው ግን አጨቃጫቂ ነው።