የኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ የጠ/ሚሩን ጥያቄ ይቀበለው ይሆን?

አርማ Image copyright ferrantraite

የኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ (ESFNA) ዘንድሮ በሚያዘጋጀው 35ኛ ዓመታዊ የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ንግግር እንዲያደርጉ ስለመጠየቁ አስታወቀ።

የፌዴሬሽኑ ሊቀ-መንበር አቶ አብይ ኑርልኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በፌስቲቫሉ ላይ ንግግር ያደርጉ ዘንድ ጥያቄ የቀረበው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ነው።

''ይሄ ጥያቄ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ብቻ የሚወሰን ጉዳይ ስላልሆነ ወደ ቦርድ አባላት አስተላልፈናል። የቦርዱ አባላትም ሰኞ ከሰዓት በኋላ ስብሰባ ተጠርተዋል'' ያሉት ሊቀ-መንበሩ፤ አጠቃላይ የቦርድ አባላት ተሰብስበው ደብዳቤውን ከመረመሩ በኋላ ውሳኔ ላይ እንደሚደረስ አረጋግጠዋል።

የስፖርት ፌዴሬሽኑ እና የኢትዮጵያ መንግሥት በዓመታት ውስጥ የነበራቸው ግንኙነት መልካም የሚባል አልነበረም። በመንግሥት በኩል የስፖርት ፌስቲቫሉን የተቃዋሚዎች መድረክ እንደሆነ ሲተች፤ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ መንግሥት ህልወናዬን ለማፍረስ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ነበር ሲል ይከሳል።

የአሁኑ ጥያቄ በቀደመው አቋም ላይ ለውጥ መኖሩን ያሳይ ይሆን?

የፌዴሬሽኑ ሊቀመንበር አብይ ኑርልኝ በእሳቸው ወገን ለውጥ እንደማይኖር ያስረግጣሉ፣

''ድርጅታችንን የሚደግፉት ወገኖች በውጭ የሚኖሩ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ደስተኛ ያልሆኑ ናቸው። በጋራ በአንዲት ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እንዳይጓደል፣ መድሎ እንዳይኖር፣ ሙስና እንደይበዛ እና በሌሎች ጉዳዮች ድምጻችንን ስናሰማ ነበር። ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እየተደገፍን ነው የቆየነው። ይህ (ደብዳቤው) ዓላማችንን አይቀየርውም'' ብለዋል።

ውሳኔውን ደጋፊዎቻቸውን በማያስቀይም መልኩ፣ ድርጅታቸውን ወደ ስህተት በማይከት ሁኔታ ለማስተላለፍ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ጉዳዩ ከተሰማ በኃላ ፌዴሬሽኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቲቫሉ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ መፍቀድ ''አለበት!'' ''የለበትም!'' የሚል ሙግት በተለያዩ መድረኮች አይሏል።

ትደግ ቦንሳ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግሥት በሚቃወሙ ሰልፎች እና ዘመቻዎች ላይ ባላት ተሳትፎ ትታወቃለች። ፌዴሬሽኑ 'ጥያቄውን መቀበል የለበትም' በሚልም ትሟገታለች። ምክንያቷ ደግሞ መንግሥት ይሄን መድረክ በአሜሪካ ህግ መወሰኛ በኩል የቀረበበትን ጫና ለማርገብ እንደመሳሪያነት ይጠቀምበታል የሚል ነው።

''ኤች አር 128 የተሰኘው ባለስልጣናት እስከአሁን ላደረሱት ጥፋት በፍርድ ቤት ፍረዳቸውን እንዲያገኙ፣ ብሎም እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ የተዘረፈው ገንዘብ ተመላሽ እንዲሆን የሚጠይቀው የውሳኔ ሃሳብ ለሴኔት አልፏል'' የምትለው ትደግ፤ ለዶ/ር አብይ የአሁኑን መድረክ መስጠት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታውን በመጠቀም በውሳኔው ላይ የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ መንግሥታቸውን የሚጎዳ ውሳኔ እንዳያስተላልፍ ለማድረግ ፖለቲካዊ ጥቅም መሰብሰቢያ እንደሚያደርጉት በመጥቀስ ትሟገታለች።

''ዶ/ር አብይ ይሄንን መድረክ አገኙ ማለት ለአስተዳደራቸው እውቅና እና ህጋዊነትን መስጠት፣ ለዓመታት የቀረቡ ጥያቄዎችን እንደመለሱ ማስቆጠር ነው'' በማለት።

የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ግን ዶ/ር አብይ ንግግር እንዲያደርጉ ቢፈቀድ መልካም እንደሆነ ይናገራሉ።

''በ35 ዓመት ውስጥ አንድም የሀገሪቱ መሪ ይሄንን ተቋም (ፌዴሬሽኑ) ዕውቀና ሰጥቶት 'ኃይል ናችሁ!' ብሎ ተቀብሎት አያውቅም። እንዲህ እንደ ኃይል ሲታሰብ 'አዎ ጠንከራ ኢትዮጵያዊ ኃይል ነን' ብሎ ለማስተናገድ ራስን ክፍት ማድረግ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ'' ይላሉ።

የሰሜን አሜሪካ ዓመታዊ የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫል ዘንድሮ ከሰኔ 24-30 ድረስ በዳላስ ከተማ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።