ቁስሌን በገዛ እጄ እያከምኩ ሽቅብ ወጣሁ

የአፈራ አለሙ የምርቃት ፎቶ Image copyright አፈራ

"የሰው ልጅ ለመነሳት መውደቅ አለበት ባልልም፤ በመደናቀፍ ውስጥ የሚያልፍበት ብርቱ ስቃይ ግን ጠንካራ ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ" ይላል አፈራ ዓለሙ ታሪኩን ሲጀምርልን።

አፋራ አላማጣ ነው የተወለደው፤ በተወለደበት ቦታ ለማደግና ለመማር ግን አልታደለም። ተፈጥሮ ባስከተለችው ጦስ ከቀየው የተፈናቀለው በለጋ እድሜው ነበር።

ለትምህርት ከነበረው ፍቅርና ታላቅ ህልም በመነሳት፤ በ 15 ዓመት ዕድሜው "ሀ" ብሎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ እውቀት መገብየቱን ተያያዘው።

"መጀመርያ ለእኔ ቀላል አልነበረም። ምክንያቱም ሁሉም አብረውኝ ይማሩ የነበሩት በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ ስለነበሩ እንደተለየ ነገር ይመለከቱኝና መሳቂያም ያደርጉኝ ነበር። ሆኖም ሁኔታው ትምህርቴን በደንብ እንድከታተል አበረታኝ እንጂ አልጎዳኝም። በርትቼ በመማር ትምህርቴን ጨርሼ በጂኦግራፊ ለመመረቅ በቃሁ" ይላል የህይወት ገድሉን ሲዘክር።

ከዚያም በትውልድ ቀየው ቦርቆ እናዳያድግ ያደረገውን ድርቅ መታገል የዘወትር ህልምና ራዕዩ ሆነ። ስደት ምን ያህል እንደሚያም እና ማንነትን እንደሚያሳጣ ካለፈው ህይወቱ ''ትልቅ ትምህርትን ቀስሜያለሁ'' የሚለው አፈራ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን የመርዳት ጥልቅ ፍላጎት አደረበት።

ይህን ለማሳካትም ሱዳን ከሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመሆን የአቅሙን ያህል አበርክቷል። የግል ኑሮውንም ጎን ለጎን በማስኬድ አንዲት እንግሊዛዊት በሀገሩ ባህል መሰረት አግብቶ የአንድ ልጅ አባት ለመሆን በቅቷል።

Image copyright አፈራ

ተስፋ አለመቁረጥና የነገውን ማየት

የአፈራ ጥረት በዚህ አላቆመም። አሁን ላለበት ደረጃ ያበቃችውን ያችን የገጠር ትምህርት ቤት አልረሳትም። አስፈላጊ የቁሳቁስና የገንዘብ እርዳታ እየሰጠ፤ የትምህርት ጥማት እያላቸው እንደእሱ ትምህርት ለማግኘት ያልቻሉትን ህፃናት ለመደገፍ የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ትምህርት ቤቷም በአሁኑ ጊዜ "አፈራ አለሙ" ተብላ እንደምትጠራና ወደፊትም የሚያስፈልጋትን ሁሉ በማድረግ ለእድገቷ እንደሚጥር በኩራት ይናገራል።

መጨረሻው

"ተደናቀፍኩኝ እንጂ ወድቄ አልቀረሁም" የሚለው አፈራ ቁስሌን በገዛ እጄ እያከምኩ ሽቅብ ወጣሁ ይላል። ''ገና ወደ ላይ ለመምጠቅ ነው ጥረቴ።'' ነገር ግን ይህን ሲያደርግ ብዙ ገንዘብ ኖሮት ሳይሆን ዋናው ተነሳሽነቱ እንደሆነ ይናገራል። ''አንዱን ጫፍ እንደያዝኩኝ ህልሜንና ዕቅዴን መግታት እንደሌለብኝ ተፍትኜ ከህይወት ተምሬአለሁ።''

አሁን ላይ ሆኜ ስመለከተው፤ በዚያን ጊዜ ከተራራ በላይ ገዝፈው ያስደነገጡኝ ፈተናዎች፤ እዚህ ግባ የማይባሉ እንደሆኑ እታዘባለሁ። ለግዜው ሸፈኑኝ እንጂ አልደቆሱኝም፤ አደከሙኝ እንጂ መቃብር አላወረዱኝም። አሁን ከበላያቸው ስለሆንኩ አልፌያቸው ስለሄድኩ ታሪክ ሆነው ቀርተዋል።"