በአርሲ የመሬት መንሸራተት የሃያ ሁለት ሰዎችን ህይወት ቀጠፈ

በመሬት መንሸራተቱ የተቀበረችን ላም የአካባቢው ሰዎች ሊያወጡ ሲሞክሩ Image copyright West Arzi Zone Communication Office

በምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ቱሉ ጎላ በተሰኘ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቢሎ በተሰኘ ቦታ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ሃያ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ ሰባት ሰዎች ደግሞ በነፍስ አድን ሰራተኞች ሊተርፉ ችለዋል።

በአደጋው ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፤ ቤቶች ፈርሰዋል ፤ በርካታ የቤት እንስሳት ላይም ጉዳት ደርሷል። ከሞቱት ሰዎች መካከል አስራ አራቱ ዕድሜያቸው ከ 15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት እንደሆኑ ታውቋል።

አደጋው የደረሰበት ስፍራ ከከተማ ወጣ ያለና መሰረተ ልማት ያልተሟላለት በመሆኑ የነፍስ አድን ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው የምዕራብ አርሲ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ፈይሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ፈይሳ አክለውም በህይወት ለተረፉ ሰዎች የህክምና እርዳታ እየተደረገ እንዳለና የዞኑ የኦህዴድ አደራጅ ና የፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊ በሆኑት አቶ ወርቅነህ ሐይሌ የሚመራ ልዑክ የተለያዩ መድሃኒቶችን፣ የህክምና ባለሙያዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ይዘው ወደ ስፍራው መጓዛቸውን ነግረውናል።

በአደጋው አራት ሰዎች እንደጠፉና እነሱን የመፈለግ ስራ እየተሰራ ነው።

Image copyright West Arsi Communucation Bureau

ይሁን እንጂ አደጋው የደረሰበት ቦታ የነፍስ አድኑን ስራ አዳጋች ስላደረገው የሟቾቹን ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

በመንግስት በኩል ሟቾችን የቀብር ስነ ስርዓት ማስፈፀምና ተጎጅዎችን ለቀጣዮቹ ሳምንታት የህክምና እርዳታ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው የሚሉት አቶ ፈይሳ ይህን መሰል አደጋ ከዚህ ቀደም አጋጥሞ እንደማያውቅ ገልፀው ቀድሞ ጥንቃቄ ለመውሰድ ምንም ዓይነት የቅደመ ትንበያ ባለመኖሩ አደጋው ሊከሰት ችሏል ብለዋል።

በተጨማሪም ስፍራው በተራሮች የተከበበ መሆኑን የገለፁት አቶ ፈይሳ በኗሪዎች ላይ ተንዶ ጉዳት ያደረሰው ተራራ የተራቆተ ስለነበረ ነው ብለዋል። በመሆኑም አካባቢን የመጠበቅ ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች