የቼልሲ እግር ኳስ ቡድን ባለቤት አብራሞቪች እስራኤላዊ ዜግነት ለማግኘት ብቁ ናቸው

ሮማን አብራሞቪች Image copyright AFP

ሩሲያዊው አይሁድ ቢሊየነርና የቼልሲ እግር ኳስ ቡድን ባለቤት ሮማን አብራሞቪች፣ እስራኤላዊ ዜግነት ለማግኘት ብቁ መሆናቸው ስለተረጋገጠ ወደ ቴላቪቭ አቅንተዋል።

የእስራኤል ኢሚግሬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት ለቢቢሲ እንደተናገረው ባለፈው ሳምንት አብራሞቪች ሞስኮ በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ለጥያቄ ቀርበው ነበር፤ በዚህም ምክንያት ወደ እንግሊዝ ለመብረር የሚያስችላቸው ቪዛ ዘግይቷል ብለዋል።

የእርሳቸው ቃል አቀባይ ግን በእስራኤል ዜግነት በማግኘታቸው ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የ51 ዓመቱ አብራሞቪች በእስራኤል እጅግ በጣም ሐብታሙ ግለሰብ ይሆናሉ ማለት ነው።

ወደ እንግሊዝ መግባት የሚያስችላቸው የኢንቬስተር ቪዛ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጊዜው ያለፈበት ሲሆን የእንግሊዝ መንግስት ኃላፊዎች ግን በግለሰብ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈለጉም።

አብራሞቪች በዌምብሌ የተካሄደውንና ቼልሲ ማንችስተር ዩናይትድን ያሸነፈበትን የኤፍ ኤ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ሳይታደሙ ቀርተዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን አብራሞቪች በአለም ላይ የሚገኙ አይሁዳውያን ወደ እስራኤል ሲመለሱ የሚሰጣቸውን የተመላሽ መታወቂያ እንደተሰጣቸው ዘግበዋል።

ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል የሀገር ውስጥ ሚኒስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው አብራሞቪች ሰኞ እለት እስራኤል መግባታቸውን እንዳረጋገጡለት ዘግቧል።

አብራሞቪች ወደ እስራኤል በተደጋጋሚ የሚመላለሱ ሲሆን በ2015 በቴል አቪቭ ሆቴል ገዝተው ወደ መኖሪያነት ቀይረውታል።

የእስራኤል ፓስፖርት የያዙ ተጓዦች ያለቪዛ ወደ እንግሊዝ ገብተው ለአጭር ቀናት መቆየት ይችላሉ።

አብራሞቪች 11 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሀብት እንዳላቸው የፎርብስ ዘገባ ያሳያል።

ሮማን አብራሞቪች ማነው?

  • ከሩሲያ ትልልቅ ሃብታሞች አንዱ ሲሆኑ፤ የቼልሲ እግር ኳስ ክለብን በ2003 ገዝተዋል።
  • ከቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት ውድቀት በኋል በአስራ ዘጠኝ ዘጠናዎቹ የነዳጅ ንግድ ከመጀመራቸው በፊት አሻንጉሊቶችን ይሸጡ ነበር።
  • የቀድሞው የራሺያ ፕሬዝዳንት ቦሪስ የልሲን ወዳጅ የነበረውና የናጠጠው ሃብታም የቦሪስ ቤሬዞቭኪይ የስራ አጋር ነበሩ።
  • አብራሞቪች እና ጓደኛው ከክሬምሊን ጋር የነበራቸውን ቁርኝት በመጠቀም የመንግስት ድርጅቶችን በርካሽ ዋጋ መግዛታቸውን ብዙዎች ይተቻሉ።
  • አብራሞቪች የሩሲያዋ ቾኮትካ ግዛት አስተዳዳሪም ሆነው ሰርተዋል።
  • ከአሁኑ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው።