በኢሳትና ኦ ኤም ኤን ላይ የተከፈቱ ክሶች ተቋረጡ

ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) Image copyright MARCO LONGARI

''ሕገ- መንግሥቱና ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማስወገድ ሙከራ አድርጋችኃል'' በሚል የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ ከፍቶባቸው የነበሩት አቶ ብርሃኑ ነጋና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሃመድ ክስ እንዲቋረጥ መደረጉ ተሰምቷል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ሀገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ክሳቸው እንዲዘጋ የተወሰነላቸው ታዋቂ ግለሰቦች የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና የለውጥ አራማጅ እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሃመድ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ በተቋም ደረጃ " ግለሰቦቹ የሚያስተላልፉትን ጥሪ በመቀበል፣ የሽብር ቡድን ድጋፍ በማድረግ፣ በዋና ወንጀል ላይ ተካፋይ በመሆን የሽብር ተግባር ወንጀል" ተከሰው የነበሩት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን( ኢሳት) እና የአሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦ ኤም ኤን) ክሳቸው እንዲቋረጥ መወሰኑም ተሰምቷል።

ውሳኔው ከተሰማ በኋላ ቢቢሲ ያናገራቸው የኢሳት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አበበ ገላው ወትሮም በተቋማቸው ላይ የቀረበው ክስ በሀሰት ላይ የተመሰረተ መሆኑነ ጠቅሰው የክስ ማቋረጥ እርምጃውን ግን በአዎንታ እንደሚመለከቱት ገልፀዋል ።

«የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን እና ራዲዮ የኢትዮጵያዊ ህዝብ የነፃነት ልሳን እንጂ የአሸባሪ ድምፅ አይደለም ፣በውስጡ ያሉ ጋዜጠኞችም በመናገራቸውና በመፃፋቸው ምክንያት ለስደት እና ለመከራ የተዳረጉ ጋዜጠኞች ናቸው፣» ያሉት አቶ አበበ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገሪቱን 'በመጠኑም' ቢሆን የመቀየር አቅጣጫ ማሳየታቸው በመልካምነት እንደሚወሰድ ጠቅሰዋል።

ሆኖም የአሁኑ ርምጃ የቴሌቭዥን እና ራዲዮ ጣቢያቸው የሚታወቅበትን በመንግሥት ላይ የሰላ ትችት ማቅረብን ከመሰሉ የቀደሙ መታወቂያዎቹ እንዲያፈገፍግ እንደማያደርገው አስገንዝበዋል።

«የህዝባችን እና የቄሮ ትግሎች በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዳስፈቱ ሁሉ፣ ዛሬ በእኔም ሆነ በኦ ኤም ኤን ላይ የቀረበውን ክስ ለማዘጋት ችለዋል፣» በማለት አድናቆታቸውን ያስቀደሙት የኦ ኤም ኤን ዋና ስራ አስኪያጅ ጃዋር መሃመድ በበኩላቸው' ከሃይል ይልቅ መደራደር ይቻላል!' በሚል ብቅ ያሉ አዲስ አመራሮችን አመስግነዋል።

ከአሁኑ እርምጃ በተጨማሪ 'አፋኝ ናቸው' እየተባሉ የሚጠቀሱ የፀረ ሽብር እና የፕሬስ አዋጆችን የመሰሉ ህግጋት በተመሳሳይ በአዲስ ከተተኩ በኢትዮጵያ ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ብዙሃነትን የሚያጠናክር እርምጃ ተደርጎ እንደሚታሰብ አስረድተዋል።