ፌስ ቡክ በፓፓዋ ኒው ጊኒ ለአንድ ወር ሊታገድ ነው

የፌስቡክ መስራችና ኃላፊ ማርክ ዙከርበርግ Image copyright Getty Images

ፓፓዋ ኒው ጊኒ ሐሰተኛ የፌስ ቡክ ገጾችን ለመለየት እና ድረገፁ በሀገሪቱ ላይ ያለውን ተፅእኖ ለመለየት በሚል ፌስ ቡክን ለአንድ ወር ልታግድ ነው።

የሀገሪቱ ኮሙኑኬሽን ሚኒስትር፣ ሳም ባዚል እንዳሉት ወሲብ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንና ሀሰተኘኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ይለያሉ።

አክለውም ከፌስ ቡክ ጋር የሚስተካከል ማህበራዊ ድርአምባ ሊከፍቱ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

በፓፓዋ ኒው ጊኒ ከአጠቃላይ ሕዝቡ 10 እጅ የሚሆነው ብቻ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቢሆንም ሐገሪቱ ግን በድረገፅ የሚሰራጩ መረጃዎች ላይ የሚወጡ ህጎችን በማውጣት ቀዳሚ ነች።

መንግስት በአንድ ወር የእቀባ ጊዜ ውስጥ ፌስ ቡክ እንዴት ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ የሚመረምር ሲሆን የ2016ቱን የሀገሪቱ የሳይበር ወንጀል ሕግ የተላለፉት ላይ ክስ ይመሰርታል።

የኮሙኑኬሽን ሚኒስትሩ ባዚል በሀገር ውስጥ ለሚንቀሳቀስ አንድ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉት "ጊዜውን ከሐሰተኛ አካውንቶች ጀርባ ማን እንዳለ መረጃ ለመሰብሰብ እንጠቀምበታለን፤ ወሲብ ነክ ምስሎችን የሚለጥፉ እና ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ተጠቃሚዎችን እንለይበታለን""

በአለም አቀፍ ደረጃ ለሚንቀሳቀሱ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች "ሐሰተኛ ዜናዎች" ዋነኛ እንቅፋት ሆነውባቸዋል፤ ተጠቃሚዎቻችን መረጃው ስህተት ሲሆን አላስጠነቀቁም በሚልም ይተቻሉ።

"ለሀገራችን ዜጎች በእውነተኛ ማንነታቸው የሚጠቀሙበት አዲስ ማህበራዊ ድር አምባ እንከፍታን" ብለዋል ባዚል።

"አስፈላጊ ከሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ሰብስበን ለህዝባችን የበለጠ ተስማሚ የሆነ በሀገረ ውስጥ ሆነ በውጭ የሚሰራ እንዲፈጥሩ እናደርጋለን"ብለዋል።

ፌስ ቡክ ከካምብሪጅ አናሊቲካ ጋር በተያያዘ ምርመራ የተደረገበት ሲሆን ሐሰተኛ ዜናዎችን እንዳይሰራጩ ለመከላከል ያደረገው ጥረት የለም በሚል ትችት እንደቀረበበት ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች