ከሚሊዮን ብር በላይ ያወደመችው ተማሪ ክስ ቀረበባት

ተማሪዋ የባንክ ደብተር ውስጥ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በስህተት ገቢ ተደርጓል
አጭር የምስል መግለጫ ተማሪዋ የባንክ ደብተር ውስጥ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በስህተት ገቢ ተደርጓል

ተማሪ ደግሞ ይህን ያህል ገንዘብ ከየት ሊያመጣ ይችላል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

ይህቺ ተማሪ ቦርሳ ውስጥ የገባው ሲሳይ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ነው። ለዚያም በአንድ ቀን።

ሲቦንጊሊ ማኒ የ28 ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ናት። ለዚያም የአካውንቲንግ ተማሪ። በስህተት የባንክ ደብተሯ ውስጥ ከገባው 1.1 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 63ሺ ዶላሩን እንዳልነበረ አድርጋ አውድማዋለች። እጇ ውስጥ ከገባው 30 ሚሊዮን ብር ውስጥ ያጠፋቸው ገንዘብ ወደኛ ሲመነዘር ከ2 ሚሊዮን ብር አይበልጥም።

በዋልተር ሲሱሉ ዩኒቨርስቲ የአካውንቲንግ ተማሪ ወደሆነችው ሲቦንጊሊ ማኒ ይህ ሁሉ አዱኛ እንዴት በአንድ ጊዜ ሊገባ እንደቻለ የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃንን እያነጋገረ ነው።

አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆና ክስ የተመሠረተባት ሲቦንጊኒ የድሀ ድሀ ተማሪዎች የሚረዱበት ማኅበር ውስጥ በወር 110 ዶላር የገንዘብ ድጎማ እየተደረገላት ነበር የምትማረው ተብሏል።

የዕድል ጉዳይ ሆኖ ግን ከዕለታት በአንዱ የባንክ ደብተሯ ውስጥ 30 ሚሊዮን ብር ገባላት። ማመን አልቻለችም። ወዲያውኑ 63 ሺህ ዶላሩን መንዝራ ለፈንጠዚያና ውድ ጌጣ ጌጦችን ለመግዛት አውላዋለች።

ትናንት ፍርድ ቤት ቀርባ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣት በኋላ ለሐምሌ 2 ተቀጥራለች ተብሏል።

ደቡብ አፍሪካውያን በትዊተር ገጻቸው እልፍ ሐሳቦችን እየተለዋወጡ ሲሆን በርካቶች "እሰይ ደግ አረግሽ! አበጀሽ!" እያሏት ነው።