በቱኒዚያ የ48 ስደተኞች ሕይወት አለፈ

በቱኒዚያ የ48 ስደተኞች ሕይወት አለፈ Image copyright EPA

ስደተⶉቹን የጫነቸው ጀልባ በምሥራቅ ጠረፍ ቱኒዚያ ተገልብጣ ነው በትንሹ 48 ስደተኞች የሞቱት። እጅግ ቢበዛ 90 ሰዎችን መጫን የምትችለዋ ጀልባ 180 የሚሆኑ ስደተኞችን አሳፍራ ነበር። ከነዚህም ውስጥ አንድ መቶ የሚሆኑት ቱኒዚያዊያን ወጣቶች ነበሩ።

ሌሎች 67 ስደተኞች ደግሞ የጠረፍ ጠባቂዎች ከሞት ታድገዋቸዋል።

ቱኒዚያ አሁን አሁን አማራጭ የስደተኞች ማቋረጫ እየሆነች ነው። ይህም የሆነው በሊቢያ በስደተኛ አስተላላፊዎች ላይ ዘመቻ በመከፈቱ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

አደጋው እንዴት እንደደረሰ የተናገረ አንድ ከሞት ያመለጠ ስደተኛ እንደሚለው የጀልባዋ ሾፌር የጠረፍ ጠባቂዎችን ሲያይ በመስጠም ላይ የነበረችዋን ጀልባ ጥሎ በመጥፋቱ ነው አደጋው የደረሰው።

ዋእል ፈርጃኒ የተባለ ሌላ ስደተኛ እንደተናገረው ደግሞ ጀልባዋ ውስጥ ውሀ መግባት በመጀመሩ ነው አደጋው የደረሰው። "ማምለጥ የቻሉት አመለጡ፤ ሌሎች ግን እዚያ መስጠም ጀመሩ" ብሏል። መጀመርያ አሳ አጥማጆች ከዚያም የባሕር ኃይል አባላት እንደደረሱላቸውም ጨምሮ ተናግሯል።

ሥራ አጥ ቱኒዚያዊያን እና ሌሎች አፍሪካዊያን ሜዲቴሪያንን ለማቋረጥ መናኛ ጀልባዎችን በመጠቀም ከቱኒዚያ ሲሲሊ ድረስ እጅግ አደገኛ ጉዞን ያደርጋሉ።

ይህ የሞት ዜና የተሰማው የኢጣሊያ አዲሱ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ማቲዮ ሳልቪኒ ሲሲሊን በሚጎበኝበት ወቅት ነበር። ሚኒስትሩ "ሲሲሊ የአውሮፓ የስደተኞች ቋት መሆኗ ሊያበቃ ይገባል" ብለዋል።