አሜሪካዊው በሞተ እባብ ተነደፈ

አሜሪካዊው በሞተ እባብ ተነደፈ

መኖሪያውን ቴክሳስ ግዛት ያደረገ አንድ ግለሰብ 25 ያክል የእባብ መርዝ መከላከያ መድሃኒት እንዲወስድ ግድ ሆኖበታል። ይህም የሆነው ቀጥቀጦ እና ቆራርጦ የጣለውን እባብ ከመኖሪያ ቤቱ እያራቀ ሳለ በሞተው እባብ ጭንቅላት በመነደፉ ነው።

የተነዳፊው ባለቤት ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስትናገር ባለቤቷ የአትክልት እርሻውን በማሰማመር ላይ ሳለ ነበር 1.25 ሜትር ርዝማኔ ያለውን እባብ የተመለከተው።

ከዚያም መከላከያውን መዥለጥ በማድረግ እባቡን እንዳልነበር ካታትፎ ይጥለዋል። ለጥቆም የተቆራረጠውን የእባቡን አካል ይዞ በመውጣት ላይ ሳለ የእባቡ ጭንቅላት የነደፈው።

ወዲያውም ሰውየውን ይንዘፈዘፍ ያዘ። ይህን የተመለከትችው ባለቤቱ ደርሳ አምቡላንስ ትጠራለች። የአካባቢው የጤና ባለሙያዎችም የእባብ መርዝ ማርከሻ ካለበት ሥፍራ በሄሊኮፕተር በመውሰድ ሕይወቱን ሊያተርፉት ችለዋል።

ግለሰቡ ኩላሊቱ አካባቢ ከሚሰማው የሕመም ሰሜት በቀር አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተነገሯል።

በሕክምና መስጫው ያሉ አንዲት ባለሙያ አንዳንድ የእባብ ዝርያዎች ጭንቅላታቸው ቢቆረጥ እንኳ ለሰዓታት ሳያሸልቡ ሊቆዩ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ በእባብ መነደፍ ከአንገብጋቢ የጤና እክሎች መካከል መመደቡን አሳውቆ እንደነበር አይዘነጋም።