"ኤርትራ የምትሰጠው አዲስ መግለጫ የለም" በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር

ካርታ

ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን ከገለጸች ጀምሮ ከኤርትራ መንግሥት በኩል የሚሰጥ ምላሽ ሲጠበቅ ቆይቷል። ሆኖም ፕሬዚዳንቱም ሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት አቶ የማነ ገብረመስቀል ዛሬ በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት ''ላለፉት አስራ ስድስት ዓመታት አቋማችን ግልፅ ነው'' ከማለት ውጪ ምንም አይነት ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም።

ነገር ግን ቢቢሲ የትግርኛው ክፍል በዚህ ጉዳይ ላይ በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑትን አምባሳደር ኤስጢፋኖስ ዛሬ ረፋድ ላይ አነጋግሯቸው ነበር።

የኤትርራ መንግሥት ስለምን መግለጫ ሳይሰጥ ቀረ? በሚል የተጠየቁት አምባሳደሩ "ኢትዮጵያ እንጂ ኤርትራ የምትሰጠው አዲስ መግለጫ የለም" ሲሉ ተናግረዋል።

''የኤርትራ መንግሥት ምላሽ ለረዥም ዓመታት በቀጥታ የተገለጸ ነው'' ያሉት አምባሳደሩ የኤርትራ አቋም ውሳኔው ከተሰጠ ማግስት ጀምሮ አንድና የማይቀየር ነው ብለዋል።

"ከኢትዮጵያና ከሌሎች ጋር ያለን ዝመድና ስትራቴጂካዊ ነው። ታክቲካዊ አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።

''በኢትዮጵያ አንድ አዲስ ክስተት አለ'' ያሉት አምባሳደሩ "ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ በህወሓት የበላይነት ተይዞ ቆይቷል" ሲሉ አብራርተዋል። በሥልጣን ላይ የቆየው ህወሓትም አገሪቱን ለመበታተን ነበር ሲሠራ የቆየው" ሲሉም ተችተዋል።

አሁን ያሉ ሁኔታዎች ግን አገሪቱ ከህወሓት የበላይነት እየወጣች እንዳለ የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮች ይታያሉ ብለዋል አምባሳደሩ።

"አሁን በኢትዮጵያ የሕዝቡ ተቃውሞ የድል አፋፍ ላይ እንደደረሰ ልንገነዝብ እንችላለን" ብለዋል። "በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ፖለቲካዊ ለውጦች ደግሞ ይህንን ያመለክታሉ" ሲሉም አክለዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጰያ ይህንን የማይቀለበስ ውሳኔ መቀበሏ "እንደ አውንታዊ እርምጃ ልናየው ይገባል" ብለዋል።

የሁለቱ ሕዝቦች ከዚህ ውሳኔ ምን ያተርፋሉ በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ''አሁን እየነፈሰ ያለው ጥሩ አየር ሁለቱን ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው አገራት ጭምር ይተርፋል፣ በጎ ተጽዕኖም ይኖረዋል'' ብለዋል።

"የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዘቦች ለጦርነት፣ ለኋላቀርነትና ለድንቁርና አይደለም የተፈጠሩት'' ያሉት አምባሳደሩ ሁለቱ ሕዝቦች በቂ የተፈጥሮ ሀብት መታደላቸውን ገልፀው ''ይህ ሀብት ለሁለቱም ጥቅም ይውል ዘንድ ሰላም ያሻል" ብለዋል።

"ይሄን ስንል ለሕዝብ ግንኙነት የሚውል ወሬ እየነዛን አይደለም። ግንኙነታችን ስትራቴጂክ ነው። ይህ ግንኙነት ትናንት ነበር፣ ዛሬም አለ፣ ነገም ይኖራል" ብለዋል አምባሳደሩ።