ጋና የእግር ኳስ ማሕበሯን በተነች

ኪዌሲ ኒያንታኪ የተሰኙት የማሕበሩ ፕሬዝደንት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጋና እግር ኳስ ማሕበር ፕሬዝደንት የሆኑ ግለሰብ በአንድ ዘጋቢ ፊልም ላይ ጠርቃ ያለ ጥሬ ገንዘብ ሲቀበሉ በመታየታቸው ምክንያት ነው ጋና ማሕበሩን ለመበተን የተገደደችው።

ኪዌሲ ኒያንታኪ የተባሉ የማሕበሩ ፕሬዝደንት 65 ሺህ ዶላር ወይም 1.8 ሚሊዮን ብር ገደማ ገንዘብ ሲቀበል በመቅረፀ ምስል ከተያዙ በኋላ ነው ጫናው የበረታው።

የመርማሪ ፊልሙ አዘጋጅ የሆነ ሰው በጋና የእግር ኳስ ላይ 'ኢንቨስት' ማድረግ የሚፈልግ መስሎ ፕሬዝደንቱ ጋር ከሄደ በኋላ ነው ይህን ድርጊት መመዝገብ የቻለው።

የስፖርት ሚኒስትሩ አይዛክ አሲያማ ማሕበሩ ወዲያኑ እንዲፈርስ መደረጉን ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

አወዛጋቢው ጋናዊ የምርመራ ጋዜጠኛ አናስ አረማያው አናስ ያቀናበረው መርማሪ ፊልም እግር ኳስ አፍሪካ ውስጥ ያለበት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ያሳያል ሲሉ በርካቶች አስተያየት በመስጠት ላይ ናቸው።

'ስግብግብነት እና ሙስና ባህል ሲሆኑ' በሚል የሰየመው መርማሪ ፊልም ለጋና ባለሥልጣናት ከተሰጠ በኋላ ሕዝብ በተሰበሰበበት ነው ዕለተ ረቡዕ ለእይታ የቀረበው።

የጋና መረጃ ሚኒስትር መንግሥት ማሕበሩን ያለ ምንም ቅድመ ውሳኔ ለማፍረስ እንደወሰነ አሳውቀዋል፤ አዲስ ማሕበር መመሥረት እና መሰል እርምጃዎች እንደሚከተሉ ጥቆማ በመስጠት።

ማሕበሩ ጉዳዩን ለማጣራት የሚከናወን የትኛውም ዓይነት ምርመራ የተሳካ እንዲሆን ትብብር እንደሚያደርግ አሳውቋል።

ኪዌሲ ከጋና እግር ኳስ ማሕበር ኃላፊነታቸው ባለፈ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፈዴሬሽን ምክትል ፕሬዝደንት ናቸው።

ማሕበሩን መምራት ከጀመሩ ወዲህ «ሙስናን ለመወጋት የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም» ሲሉ ደጋግመው ይናገሩ ነበሩ።

ነገር ግን መርማሪ ፊልሙ ላይ 65 ሺህ ጥሬ ዶላር ወደ ቦርሳቸው ሲያስገቡ ታይተዋል።

የበርካቶችን አፍ በአግራሞት ያስከደነው ይህ መርማሪ ዘጋቢ ፊልም ኬንያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ባሉት አገራት ከመቶ በላይ የሚሆኑ የእግር ኳስ ሃላፊዎች ከጨዋታ በፊት ገንዘብ ሲቀበሉም ያሳያል።

በሩስያው የዓለም ዋንጫ በረዳት ዳኝነት እንዲያገለግሉ የታጩ አንድ ኬንያዊ አርቢትር 600 ዶላር ሲቀበሉ በፊልሙ ላይ በመታየታቸው ምክንያት ራሳቸውን ከዓለም ዋንጫ ግዳጅ አግልለዋል።