ለፌስቡክ ሱሰኞች የተገነባው አስፋልት ተመረቀ

ለተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች የሚያገለግለው አስፋልት Image copyright The Paper
አጭር የምስል መግለጫ የብስክሌት ጋላቢዎችና የእግረኞች መንገድ ብቻ በቂ አይደለም፤ ለፌስ ቡክ ሱሰኞችም መንገድ ተገንብቷል

ለዐይነ ሥውራን ምቹ አስፋልት ተሠርቶ ያውቃል። ለብስክሌት ጋላቢዎችም ጎዳና ተዘርግቶ ያውቃል። በስልክ ሱስ ለናወዙ ተብሎ ግን አስፋልት ሲሠራ ይህ የመጀመርያው ነው ተብሏል።

በብዙ ዘመነኛ ከተሞች ወጣቶች ሞባይሎቻቸው ላይ አቀርቅረው ስለሚራመዱ ከስልክ እንጨት ጋር ይላተማሉ። ለመኪና አደጋም የተጋለጡ አሉ።

ሰሜን ቻይና የምትገኝ አንዲት ከተማ ለእነዚህ ሱሰኞቿ መላ ዘይዳለች። ለእነርሱ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ጎዳናን አስመረቅላች።

ያንታ ጎዳና የሚባለውና ዢያን በምትባለው በዚች ትንሽ ከተማ የሚገኘው ይህ ጥርጊያ ዓለምን ለረሱና በሞባይል ሱስ ለናወዙ ብቻ የሚሆን ነው ተብሏል።

አስፋልቱ ቀይ፣ አረንጓዴና ሰማያዊ ቀለም ተቀብቷል። ወርዱ 80 ሴንቲ ሜትር ቁመቱ ደግሞ 100 ሜትር እንደሚሰፋም ተመልክቷል። ከተራ የእግረኛ መንገድ የሚለየው የተንቀሳቃሽ ስልክ ምልክትም በአስፋልቱ ላይ ታትሞበታል።

የአካባቢው ተወላጆች በዚህ ጎዳና መሠራት እጅግ ተደስተዋል ተብሏል።

በታዋቂው የቻይና ወይቦ ብሎግ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ ዜጎች መሐል የአዲሱ ትውልድ ከስልክ ጋር ያለው ቁርኝት በድሮ የቻይና ዳይናስቲ ለኦፒየም ከነበረው ሱስ ጋር የሚመሳሰል ነው ይላል።

ሌላ አስተየየት ሰጪ በበኩሉ እነዚህ ሱሰኞች አሁንም ቢሆን እርስበርስ መላተማቸው አይቀርም ሲል የአዲሱ አስፋልት መገንባት ከመላተም እንደማያድናቸው ጠቁሟል።