ልዑል ፊሊፕ፡ የኤደንብራው መስፍን ልዑል ፊሊፕ የሕይወት ታሪክ

ልዑል ፊሊፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኤደንብራው መስፍን ልዑል ፊሊፕ ለንግሥቱቱ በነበራቸው ያልተቋረጠ ጠንካራ ድጋፍ የተነሳ ሠፊ አክብሮትን ለማግኘት ችለው ነበር።

ልዑሉ የነበራቸው ሚና በባሕር ኃይል ውስጥ በመሪነት ቦታ ላይ ለቆየ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ሠፊ ዕውቀትን ላዳበረ ሰው ቀርቶ ለሌላ ለማንም ሰው እጅግ አስቸጋሪ ነበር።

ነገር ግን የነበራቸው ጠንካራ ባህሪይ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በውጤታማነት እንዲወጡት ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ ለባለቤታቸው የንግሥትነት ሚና ከሙሉ ልባቸው ድጋፍ አድርገውላቸዋል።

የእንስት ዘውዳዊ ባለማዕረግ ወንድ አጋር እንደመሆናቸው፤ ልዑል ፊሊፕ ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ሚና አልነበራቸውም። ነገር ግን ማንም ከእርሳቸው የበለጠ ለዘውዳዊው አስተዳደር ቅርብና ለንግሥቲቷ አስፈላጊም አልነበረም።

የፎቶው ባለመብት, Royal Collection

የምስሉ መግለጫ,

ፊሊፕ በእናቱ ልዕልት አሊስ እቅፍ ውስጥ

ቀዳሚ ዓመታት

የግሪኩ ልዑል ፊሊፕ የተወለዱት እ.ኤ.አ ሰኔ 10 ቀን 1921 በኮርፉ ደሴት ነው። የልደት የምስክር ወረቀታቸው ላይ የሰፈረው ቀን ግን ግንቦት 28/1921 የሚል ነው። ለዚህም ምክንያቱ በወቅቱ ግሪክ የጎርጎሪዮሳዊያን የቀን አቆጣጠር ቀመር ትከተል ስላልነበረ ነው።

አባታቸው የግሪኩ ልዑል አንድሪው ሲሆኑ እርሳቸውም የሄሌናው ንጉሥ ጆርጅ ቀዳማዊ ትንሽ ልጅ ነበሩ። እናታቸው የባተንበርጓ ልዕልት አሊስ ደግሞ የባተንብርጉ ልዑል ልዊስ የበኩር ልጅ እንዲሁም የበርማው ኧርል ሞንትባተን እህት ነበሩ።

በ1922 መፈንቅለ-መንግሥት ከተካሄደ በኋላ አባታቸው በአብዮታዊው ፍርድ ቤት ከግሪክ ተባርረዋል።

ሁለተኛ የአክስት ልጃቸው በነበሩት ንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ የተላከ የብሪታንያ የጦር መርከብ ከነቤተሰባቸው ወደ ፈረንሳይ ወስዷቸዋል።

ልዑሉም ቀለም መቁጠር የጀመሩት በፈረንሳይ ቢሆንም ተቀዳሚ ትምህርታቸውን የተከታተሉት የሰባት ዓመት ልጅ ሳሉ ከዘመዶቻቸው ጋር ለመኖር በመጡበት እንግሊዝ ነው።

በዚህ ጊዜ እናታቸው ስኪዞፍሬኒያ በሚባለው ከባድ የአዕምሮ ህመም ተጠቅተው የአዕምሮ ህሙማን ማቆያ ውስጥ ገብተው ነበር። ወጣቱ ልዑል ከእናታቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነትም ውስን ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ፊሊፕ (የተቀመጠው) በጎርደንስታውን በአማተር ተዋናይነት

ወታደራዊ ስልጠና

ልዑል ፊሊፕ በወታደራዊው ዘርፍ ለመሳተፍ ወሰኑ። ዘውዳዊውን የአየር ኃይል ለመቀላቀል ፈልገው የነበረ ቢሆንም የእናታቸው ቤተሰብ የባሕር ላይ ታሪክ ስለነበራቸው፤ በእንግሊዝ ደቡባዊ ዳርቻ ባለችው ዳርትሞዝ በሚገኘው በብሪታንያ ዘውዳዊ የባሕር ኃይል ኮሌጅ ውስጥ እጩ መኮነን ሆነው ተመዘገቡ።

እዚያ በነበሩበት ጊዜ ንጉሥ ጆርጅ ስድስተኛ ኮሌጁን በሚጎበኙበት ወቅት ሁለቱን ወጣት ልዕልቶች ኤልሳቤጥን እና ማርጋሬትን እንዲያጅቡ ተወክለው ነበር።

ይህ መገናኘትም በ13 ዓመቷ ልዕልት ኤልሳቤጥ ልቦና ውስጥ የጠለቀ ስሜትን ፈጠረ።

ፊሊፕ ወዲያውኑ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ማስመስከር ቻሉ፤ በ1940 ትምህርታቸውን ከክፍላቸው ቀዳሚ ሆነው ያጠናቀቁ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ወታደራዊ ተሳትፏቸውንም በህንድ ውቅያኖስ አደረጉ።

በ1942 በዘውዳዊው የባሕር ኃይል ውስጥ ካሉት ወጣት መኮንኖች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን፤ ኤችኤምኤስ ዋላስ በምትሰኘው የጦር መርከብ ላይ ያገለግሉ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ፊሊፕ በባሕር ኃይል ውስጥ አገልግለዋል

መታጨት

በዚህ ሁሉ ጊዜ እርሳቸው እና ወጣቷ ልዕልት ኤልሳቤጥ ደብዳቤ ይለዋወጡ ነበር። በበርካታ አጋጣሚዎችም ከዘውዳዊው ቤተሰብ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፉ ይጋበዙም ነበር።

ግንኙነታቸው በሰላሙ ጊዜ ይበልጡን ተጠናክሮ በ1946 የበጋ ወራት ልዑሉ ልጃቸውን ለጋብቻ ይሰጧቸው ዘንድ ለንጉሡ ጥያቄ አቅርበዋል።

ይሁንና መተጫጨታቸው ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ ልዑሉ አዲስ ዜግነት እና የቤተሰብ ስም አስፈልጓቸዋል። የግሪክ ማዕረጋቸውን ትተው የብሪታንያ ዜግነትን ሲቀበሉ የእናታቸውን የአንግሊካን ልማድን የሚከተለውን ሞንትባተን የተሰኘ ስም ወስደዋል።

ጋብቻው በዌስትሚኒስቴር አቤ በ1947 ተከናውኗል።

የፎቶው ባለመብት, PA

የምስሉ መግለጫ,

ልዕልት ኤልሳቤጥ እና ፊሊፕ ሞንትባተን ጋብቻ ፈፀሙ

የተቋረጠው የሥራ መስመር

መስፍኑ ወደ ባሕር ኃይል ሥራቸው ተመልሰው ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ጥንዶቹ እንደማንኛውም የወታደር ቤተሰብ ወደሚኖሩበት ማልታ አቀኑ።

ልጃቸው ልዑል ቻርለስ በ1948 ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ውስጥ ሲወለዱ ልዕልት አን ደግም በ1950 ወደዚህች ዓለም መጥተዋል።

በ1950 ልዑሉ የማንኛውንም የባሕር ኃይል አባል ህልም አሳክተው ኤችኤምኤስ ማግፓይ የተባለችው የጦር መርከብ አዛዥ ሆነዋል።

በ1951 ዘውዳዊውን የባሕር ኃይል ለቀቁ፤ ወደ መደበኛው የባህር ኃይል ሥራም አልተመለሱም።

የሥራ አጋሮቻቸው እንደሚሉት በሥራቸው ብቃት ብቻ የባሕር ኃይል የበላይ አዛዥ (ፈርስት ሲ ሎርድ) መሆን ይቻላቸው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኤልሳቤጥ ንግሥናውን ሲረከቡ ታማኝነታቸውን ከገለፁት መካከል ፊሊፕ ቀዳሚው ነበሩ

የማዘመን ውጥኖች

በ1952 ጥንዶቹ በመጀመሪያ በንጉሡ እና በንግሥቲቱ ታቅዶ የተከናወነውን የጋራ ብልፅግና (ኮመንዌልዝ) አገራት ጉብኝትን አደረጉ።

በወርሃ የካቲት ኬንያ ውስጥ ባለ የመዝናኛ ስፍራ እንዳሉ ነበር ንጉሡ የመሞታቸው ወሬ የተሰማው።

በዚህ ጊዜም ለሚስታቸው ንግሥት የመሆናቸው ዜና የማድረሱ ኃላፊነት በልዑሉ ላይ ወደቀ።

በዓለ ሲመቱ ሲቃረብ በሁሉም ጉዳዮች ከንግሥቲቷ ቀጥሎ ልዑል ፊሊፕ ስልጣን እንደሚኖራቸው የሚያስረግጥ ዘውዳዊ ድንጋጌ ታወጀ። እንዲያም ቢሆን ግን ምንም ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ስልጣን አልነበራቸውም።

የምስሉ መግለጫ,

ፊሊፕ ንግሥቲቱን አጅበው

መራር ቅሬታ

ፊሊፕ የተነቃቃ ማኅበራዊ ሕይወት የነበራቸው ሲሆን በተደጋጋሚ ከአሽብራቂ ባልንጀሮች ጋር ፎቶ ይነሱ ነበር።

የእርሳቸውን የቤተሰብ ስም ሳይሆን ዊንድሰር የተባለውን የራሳቸውን ስም ይዞ ለመቀጠል ንግሥቲቱ መወሰናቸው ልዑሉ ላይ መራር ቅሬታን ፈጥሮ ነበር።

"ስሙን ለልጆቹ ማውረስ የማይፈቀድለት በአገሪቱ ውስጥ ያለው ብቸኛው ወንድ እኔ ነኝ" ሲሉ ለወዳጆቻቸው ምሬታቸውን አሰምተው ነበር።

የልዑል ቻርልስን የህይወት ታሪክ የፃፈው ጆናታን ዲምቢልቢ እንደሚለው፤ በወጣትነታቸው ጊዜ በሰዎች ከአባታቸው ፊት ባጋጠማቸው ነቀፌታ የተነሳ አምርረው አለቀሰዋል። በአባት እና በልጅ መካከል ያለው ግንኙነትም መቼም ቀላል አልነበረም።

የምስሉ መግለጫ,

ፊሊፕ ንግሥቲቱን አጅበው

"ሰናይ ምግባር"

ልዑል ፊሊፕን ከሚያሳስቧቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የታዳጊ ልጆች እጣ ፈንታ ነበር። ይህም በ1956 እጅግ ስኬታማ የሆነው የኤደንብራ መስፍን ሽልማት ለመጀመሩ ምክንያት ሆኗል።

በቀጣይ ዓመታትም የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ እና ላልሆኑ ስድስት ሚሊዮን ያህል ከ15 እስክ 25 ዓመት ያሉ ወጣቶች የቡድን ሥራን፣ የፈጠራ ችሎታን እንዲሁም ተፈጥሮን ማክበርን ለማበረታታት በበርካታ ከቤት ውጪ እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን እንዲፈትኑ አስችለዋል።

ለዱር አራዊት እና ለአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮችም በጋለ ስሜት ይሟገቱ ነበር። በኋላ ላይ የዓለም አቀፍ ፈንድ ለተፈጥሮ ተብሎ ስሙ ለተቀየረው ለዓለም አቀፉ የዱር እንስሳት ፈንድ በከፍተኛ ደረጃ ጉልበታቸውን ያፈሰሱ እና ተፅዕኖም ያሳረፉ ሲሆኑ፤ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት መሆናቸውም የሚያስገርም አልነበረም።

ቃለ መጠይቅ ላደረገላቸው የቢቢሲ ጋዜጠኛ እንዲህ ብለው ነበር "እንደማስበው እኛ ሰዎች ህይወት እና ሞትን -መጥፋት እና መትረፍን - የማምጣት አቅም ካለን፤ በአንዳች ዓይነት ምግባረ ሰናይነት ልንተገብረው ይገባናል። ማጥፋት የሌለብንን ነገር እንዴት እናጠፋለን?"

ቀጥተኛ

ነገሮችን ፍርጥርጥ የማድረግ እና በቀጥታ የመናገር ዝንባሌያቸው አንዳንድ ጊዜ ልዑሉን ችግር ውስጥ ይጥላቸው ነበር።

በዚህም በአንዳንዶች ዘንድ ክፉኛ ቢብጠልጠሉም፤ ሌሎች በራሳቸው የሚሽከረከሩ እና በፖለቲካዊ ትክክለኛነት ያልታሰሩ ሰው ናቸው ይላሉ።

ኋለኛ ዘመን

የዕድሜ መግፋት የህይወታቸውን ፍጥነት ሊቀንሰው አልቻለም።

በህይወታቸው ሁሉ፤ ልዑል ፊሊፕ ለስፖርት ልዩ ፍቅር ነበራቸው። ዓለም አቀፉን የዱር እንስሳት ፈንድ በመደገፍ እና ንግሥቲቱን በውጭ አገር ጉዞ በማጀብ በስፋት መጓዛቸውንም ቀጥለዋል።

ግላዊ የኃይማኖት ጉዞም በ1994 ወደ እየሩሳሌም አድርገው የእናታቸውን የመቃብር ስፍራ ጎብኝተዋል። እናታቸው በጥያቄያቸው መሰረት የተቀበሩት በእየሩሳሌም ነበር።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓን የተሸነፈችበት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል እ.ኤ.አ በ1995 በተከበረበት ወቅት ሌላ ስሜታዊ ዕለትን አሳልፈዋል።

ጃፓን እጇን ስትሰጥ ልዑል ፊሊፕ በቶኪዮ ሰርጥ በብሪታንያ የጦር መርከብ ውስጥ ነበሩ። በክብረ በዓሉ ዕለትም በሩቅ ምሥራቁ ዘመቻ ተሳትፈው ከነበሩ የቀድሞ የጦር መኮንኖች ጋር በመሆን ከንግሥቲቱ ፊት የሰልፍ ትርኢት አሳይተዋል።

ግትርነታቸው በኋለኛ ዘመናቸው በመጠኑ ረገብ ብሏል፤ ይህም የዌልሷ ልዕልት ዳያና ከሞቱ በኋላ ሕዝቡ አንዳንዴ ለዘውዳዊው ቤተሰብ አሉታዊ አስተያየትን ከማዳበሩ የመነጨ ነው።

የዳያና የመጨረሻው የፍቅር አጋር አባት መሃመድ አል ፋይድ የልዕልቲቷ ሞት በሚመረመርበት ወቅት በልዑል ፊሊፕ ትዕዛዝ ነው የተገደለችው እስከ ማለት ደርሰዋል። ይህንን ውንጀላ ግን ልዑሉ ፍርጥም ብለው አጣጥለውታል።

እአአ በ2007 ከልጃቸው ሚስት ጋር ቅራኔ ነበራቸው የሚለውን ውንጀላ ለማጣጣል በመስፍኑ እና በሟቿ ልዕልት መካከል የተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦች ታትመዋል።

ደብዳቤዎቹ እንደሚያሳዩት መስፍኑ ለዳያና ታላቅ ድጋፍን ሲያደርጉ ነበር። ይህ ሃቅም ልዕልቲቷ ይፅፉ በነበረበት ሞቅ ያለ ስሜት የበለጠ ይጠናከራል።

የፎቶው ባለመብት, PA

የምስሉ መግለጫ,

ንግሥቲቱ ባለቤታቸውን የጥንካሬያቸው ምንጭ እንደሆኑ ይገልጿቸዋል

"የማይረባ አቀራረብ"

የኤደንብራው መስፍን ልዑል ፊሊፕ የሥራ ኃላፊነታቸው ሁልጊዜም ሁለተኛ ስፍራን እንዲይዙ ያስገደዳቸው ተፈጥሯዊ መሪ ነበሩ። ተጋፋጭ ባህርያቸውም የተቀመጡበት ቦታ ካለው ስሱነት ጋር ደጋግሞ የሚጋጭባቸው ሰውም ነበሩ።

"የሠራሁት ባለኝ አቅም ሁሉ የላቀውን ነው" ሲሊ በአንድ ወቅት ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ነገሮችን የማከናውንበተን መንገድ ሙሉ በሙሉ በድንገት መለወጠወ አልችልም፣ ፍላጎቶቼንና ለነገሮች ምልሽ የምሰጥበትን መንገድ መቀየር አልችልም። ይህም የእኔ ዘይቤ ነው።"

ይህንንም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በልዑሉ 90ኛ ዓመት የልደት በዓል ዋዜማ ላይ ባደረጉት ንግግር መስክረውላቸው።

"ምንጊዜም ነገሮችን የሚከውኑት በቀለል ነገር ግን የራሳቸው በሆነ ልዩ መንገድ ነው። ለብሪታኒያ ሕዝብ ለማይማርክ የማይረባ አቀራረብን ቦታ የላቸውም" ብለው ነበር።

ከሕዝባዊው እንቅስቃሴ መራቅ

ለበርካታ አስርት ዓመታት ንግሥቲቱን ሲያግዙና በራሳቸውና በሌሎች ድርጅቶች በሚካሄዱ የበጎ አድራጎት ዝግጅቶች ላይ ሲታደሙ የቆዩት ፊሊፕ ከዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ገለል ያሉት ከአራት ዓመታት በፊት ነበር።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1952 ጀምሮ ባሉት ጊዜያት 22,219 የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ብቻቸውን እንደተሳተፉ የባኪንግሃም ቤተመንግሥት ገልጿል።

ለዚህም የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በዘመናቸው ላበረከቱት "ድንቅ የሕዝብ አገልግሎት" ምስጋናቸውን አቀውርበውላቸዋል።

ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ በትዳር ውስጥ የቆዩት ፊሊፕ፤ በዳሌያቸው ላይ ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና የተደረገላቸው ቢሆንም በዊንድሰር ቤተ መንግሥት ውስጥ ንጉሣዊ ሠረገላቸውን እያሽከረከሩ ከመዘዋወር አልተቆጠቡም ነበር።

ልዑሉ ከሁለት ዓመት በፊት እራሳቸው በሚያሽከረክሩበት ጊዜ ካጋጠማቸው ከባድ የመኪና አደጋ የተረፉ ሲሆን፤ በሌላኛው መኪና ውስጥ የነበሩ ሁለት ሴቶች በአደጋው የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው ነበር። ይህንንም ተከትሎ ፊሊፕ በገዛ ፈቃዳቸው የመንጃ ፈቃዳቸውን መልሰዋል።

በኮሮናቫይረስ ወቅትም በጥር ወር 2021 (እአአ) ፊሊፕና ንግሥቲቱ ባለቤታቸው የወረርሽኙን መከላከያ ክትባት የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለበትን ጊዜ ባሳለፉበት የዊንድሰር ቤተመንግሥት ሐኪም አማካይነት ተከትበዋል።

ፊሊፕ ንጉሣዊ ሥልጣናቸውን ለብሪታንያውያን ህይወት ከፍተኛ አበርክቶ ለማድረግ በመጠቀምና ዘውዳዊው ሥርዓት በኅብረተሰቡ ዘንድ በዘመናት ሂደት እየተለወጠ ከመጣው አመለካከት ጋር እንዲጣጣም በማድረጉ ረገድም ስኬታማ ነበሩ።

ከሁሉም ስኬቶቻቸው የሚልቀው ለንግሥቲቷ በረጅም የንግሥና ዘመናቸው ድጋፋቸውን ያበረከቱበት ወጥነት እና ጥንካሬ እንደሆነ ይነገራል።

የጥንዶቹን የጋብቻ የወርቅ እዮቤልዩ ለማክበር በተሰናዳ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ንግሥቲቷ በብሪታንያ ታሪክ ለረጅም ዘመን ላገለገሉት ባለቤታቸው እንዲህ በማለት ውዳሴ አቅርበውላቸዋል፡

"ሙገሳን በቀላሉ የማይቀበል ሰው ነው። ነገር ግን በቀላሉ ጥንካሬዬ ሆኖ እነዚህን ዓመታት ሁሉ ዘልቋል። እኔም፣ ጠቅላላው ቤተሰቡም እንዲሁም ይህች እና ሌሎች አገራትም እርሱ ሊጠይቀው ከሚችለው እኛም ልናውቀው ከምንችለው በላይ ባለዕዳዎቹ ነን።"

የፎቶው ባለመብት, PA