"ወሎዬው" መንዙማ

አንድ አማኝ በመስጊድ ውስጥ ቁርዓን በመቅራት ላይ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

መንዙማ የትም ሊኖር ይችላል። ግብፅም የመንም፣ 'ሻምም'

መንዙማ የትም ሊዜም ይችላል፤ ታጃኪስታንም፣ ኡዝቤኪስታንም፣ ፓኪስታንም

እንደ ወሎ የሚኾን ግን…እንጃ!

የወሎ መንዙማ ቱባ ነው። ኦርጋኒክ!

አልተቀየጠ፣ 'አልተከተፈ'፣ 'አልተነጀሰ'። ደግሞም እንደ ዘመነኛ ነሺዳ በ'ኪቦርድ' ቅመም አላበደ…።

ለዚህ ምሥክር መጥራት አያሻም። የሼኽ መሐመድ አወል ሐምዛን እንጉርጉሮ መስማት በቂ ነው።

'በጆሮ በኩል ዘልቆ፣ አእምሮን አሳብሮ ወደ ልብ የሚፈስ የድምፅ ፈውስ…።' ይለዋል ወጣቱ ገጣሚ ያሲን መንሱር።

የመንዙማው ማማ

በዚህ ዘመን ህልቆ መሳፍርት መንዙመኞች አሉ። ሼኽ መሐመድ አወል ሐምዛ ግን ከማማው ላይ ናቸው።

ከወሎ የፈለቁት ሼኹ ለመገናኛ ብዙኃን ቃል መስጠት እምብዛም ምቾት አይሰጣቸውም። ለቢቢሲ ጥሪም እንዲያ ነው ያሉት።

ኾኖም ታሪካቸውን የዘገቡ ሰነዶች የኚህ ሰው የሕይወት መስመር እንደ መንዙማቸው ልስሉስ እንዳልነበረ ያትታሉ።

ደቡብ ወሎ የተወለዱት ሼኹ ገና ድሮ ወደ ሸዋ ገብተው ኑሮ ለማደራጀት ከፍ ዝቅ ብለዋል።

የሚያምር የአረብኛ የእጅ ጽሕፈት አጣጣል ስለነበራቸው የሃይማኖት ድርሳናትን በእጅ ከትበው በመስጂዶች ቅጥር ማዞር ጀማምረውም ነበር ይባላል።

ወዳጆቻቸው እንደነገሩን በአዲሳ'ባ የመን ኮሚኒቲ በመምህርነት እስኪቀጠሩ ድረስ የወሎ ምድርና ተፈጥሮ አድልተው ያደሏቸውን መረዋ ድምጽ በመጠቀም በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ መንዙማን ያዜሙ ነበር።

አንዳንድ መድረኮች ላይ ታዲያ የሼኩ ተስረቅራቂ ድምጽ ለነብዩ ውዳሴ ከሚደረድሩ ጥልቅ መልዕክቶች ጋር ተዳምረው ታዳሚዎችን ስሜታዊ ያደርጓቸው ነበር ይባላል።

"የእሱ እንጉርጉሮ እንደሁ ያው ታውቀዋለህ…ልብ ያሸፍታል…አንዳንድ ሼኾች ድምጽ አውጥተው በስሜት ያለቅሱ እንደነበር አስታውሳለሁ" ይላሉ ቆየት ካሉ ወዳጆቻቸው አንዱ ለቢቢሲ ትዝታቸውን ሲያጋሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመንዙማ ፍቅር የወደቀው ደርግ

መንዙመኛው ሼክ መሐመድ አወል ድሮ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጥረው ነበር አሉ። መንዙማቸውም እንደዋዛ ሬዲዮ ሞገድ ውስጥ ገብቶ ነበር አሉ፤ እንደ ማጀቢያም እንደማዋዣም።

ታዲያ ከዕለታት ባንዱ ልበ-ደንዳናዎቹ ደርጎች በሰውየው አንጀት አርስ እንጉርጉሮ ልባቸው ረሰረሰ።

ከደርጎቹ በአንዱ ላይ ክፉ አሳብ በልቡ አደረ። እንዲህም አለ፣ 'ይሄ ሰውዬ በነካ እጁ ስለ አብዮቱ ለምን አያዜምልንም?'

ሼኪው ተጠሩ። "ድምጽዎ ግሩም ኾኖ አግኝተነዋል፤ እስቲ ስለአብዮታችን አንድ ሁለት ይበሉ…።"

ያን ጊዜ "ያ አላህ! አንተው መጀን!" ብለው ከአገር ሾልከው የወጡ ከስንትና ስንት ዘመን ኋላ የሐበሻን ምድር ተመልሰው የረገጡ። 10 ዓመት? 20 ዓመት? እንጃ ብቻ!

በዚህ ሁሉ ዘመን ታዲያ እኚህ እንደ ጨረቃ የደመቁ መንዙመኛ የት ከረሙ? ስንል የጠየቅናቸው ወዳጆቻቸው ከፊሎቹ "መሐመድ አወል ሐምዛ ሳኡዲ ነው የኖረው ሲሉ፣ ገሚሶቹ ደግሞ 'የለም! እዚህ ጎረቤት 'ሚስር'፣ አልአዝሃር ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ሲይንበለብለው ነበር' ብለውናል።

የቱ ነው ትክክል ብሎ ለመጠየቅ እንኳ ሰውየው ሩቅ ናቸው። ያ ጥኡሙ ድምጻቸው መንዙማን ለማዜም ካልሆነ በቀር አይሰማም። እ…ሩቅ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

መንዙማ- የልብ ወጌሻ

መንዙማ አልፎ አልፎ መዝናኛ ነው፤ አንዳንዴ የጸሎት ማዳረሻ ነው፤ ብዙዉን ጊዜ የማኅበረሰብን ሰንኮፍ ማሳያም ነው፤ አንዳንዴ የአገር ፍቅር መግለጫም ነው።

ብዙዎቹ የመንዙማ ሥንኞች የሥነ-ምግባር ተምሳሌት ተደርገው የሚታሰቡትን ነብዩ ሙሐመድን ያወድሳሉ። አፈንጋጮችን ይገስጻሉ፣ ባሕል ከላሾችን ይኮረኩማሉ።

አቶ ተመስገን ፈንታው መቀለ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሥነ-ጽሑፍና ፎክሎርን ለ12 ዓመታት አስተምረዋል። በመንዙማ ዙርያ የተሠሩ በርከት ያሉ ጥናታዊ ወረቀቶችን አማክረዋል። የአጋጣሚ ነገር-ትውልዳቸውም ወልዲያ ነው።

'ሴት አያቴ በመንዙማ ነው ያሳደገችኝ' ይላሉ' ክርስቲያን መሆናቸው መንዙማን ከማጣጣም እንዳላቦዘናቸው ሲያስረዱ።

"ወሎ ውስጥ መንዙማ ባሕል ነው። የየትኛውንም ዕምነት ተከታይ ሁን መንዙማን ትሰማለህ፤ በአንድም ሆነ በሌላ…"

የወሎ ባሕል ወትሮም ሃይማኖትን ፍዝ ያደርጋል።

"አያቴ መንዙማን "የእስልምና" ብላ አይደለም የምትረዳው። እሷ የምታውቀው የወሎዬ መሆኑን ነው። መንዙማ ለእሷ ከአምላክ ጋር መገናኛ፣ መታረቂያ፣ መለማመኛ፣ ስሜቷን መተንፈሻ ነው። ይላሉ።

መምህር ተመስገን ይኸው የልጅነት ተጽእኖ ይሁን አይሁን ባያውቁትም አሁንም ድረስ ጥሞናና መመሰጥ ሲያምራቸው ከላፕቶፓቸው ኪስ ያኖሯቸውን እንጉርጉሮዎች ያዘወትራሉ።

"አቦ ሌላ ዓለም ነው ይዞኝ የሚሄድ!"

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

መንዙማና 'ፍልስምና'

'ፍልስምና' እስልምናና ፍልስፍናን ያቀፈ ሽብልቅ ቃል መሆኑ ላይ ከተግባባን በመንዙማ ውስጥ ፍልስፍና እንደጉድ እንደሚነሳና እንደሚወሳ ልናወጋ እንችላለን።

በመንዙማ ዓለማዊም ኾኑ ዘላለማዊ መጠይቆች በቅኔ ተለውሰው ይዜሙበታል። በግልባጩም የፈጣሪን መኖር የሚጠራጠሩ ኢ-አማንያን ከብርቱ አማኒያን ተሞክሮ እየተጨለፈ በምክር ይረቱበታል።

ለነገሩ በመንዙማ ስንኞች ፍልስምና ብቻ አይደለም የሚነሳው፤ ምን የማይነሳ አለና!? ፖለቲካ፣ ግብረ-ገብነት፣ መንፈሳዊነት፣ አርበኝነት…ኢትዮጵያዊነት...

በስልክ ማብራሪያ የሰጡን ኡስታዝ አብዱልአዚዝ መሐመድ የነጃሺ መስጂድ ኢማምና የጁምዓ ሶላት ዲስኩረኛ (ኻጢብ) ናቸው።

መንዙማ በኢትዮጵያ የኢስላም ታሪክና ፖለቲካ ውስጥ የነበረውን ቦታ ሦስት የመንዙማ ሊቃውንትን በስም በመጥቀስ ይተነትናሉ።

በዘመናዊ የኢስላም ታሪክ ውስጥ ሰሜን ወሎ፣ ራያ ውስጥ ጀማሉዲን ያአኒ የተባሉ ሐበሻ ከአጼ ዮሐንስ ጋር ለሦስት ዓመታት ተፋልመዋል። በመጨረሻ አጼው በርትተው ሲመጡባቸው ድል መነሳታቸው እርግጥ ሆነ። ያን ጊዜ ያዜሙት መንዙማ ዛሬም ድረስ ይወሳል።

"ዘይኑ ነቢ ዘይኑ ነቢዬ" የሚል አዝማች ያለው ሲሆን የመንዙማው ጭብጥ ደግሞ የአጼውን ጭካኔ ማጉላት ነው።

እንዲያውም የአጼ ዮሐንስን ጦርነት አርማጌዶን ሲሉት፤ በምጽአት ቀን (ቂያማ) ይመጣል የሚባለው ሰው ጋር ያመሳስሏቸዋል። ይህ ሰው በኢስላም "ደጃል" በመባል ይታወቃል።

አጼው እኔ ላይ ያለ ጊዜው የመጣ ደጃል ሆነብኝ ሲሉም አዚመዋል።

በተመሳሳይ በየጁ ግዛት ይኖሩ የነበሩና አሕመድ ዳኒ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ አባት በወቅቱ የነበረው አገረ ገዢ በጣም ቅር እንዳሰኛቸው፣ ዘመኑም እንዳልተመቻቸው ለመግለጽ የሚያንጎራጎሩበት መንዙማ ዛሬም ድረስ ይዜማል።

ርዕሱ "ሑዝቢየዲ ያረሱላላህ" የሚል ሲሆን "ከይህ ወዲህ ምድር ላይ መቆየት አልሻም፤ በቃኝ" የሚል መልዕክትን የያዘ ነው።

ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መንዙመኞች ደግሞ ሼክ ጫሊ ጎልተው ይወሳሉ። በይዘትም፣ በቋንቋ ልቀትም፣ በቁጥርም፣ በዓይነትም እንደርሳቸው መንዙማን የቀመረ የለም ይባላል።

እርሳቸው ታዲያ ከወራሪው ጣሊያን የተፋለሙ ጀግና ነበሩ። ከመንፈሳዊ መንዙማም በላይ ስለ አገር ፍቅር ያዜሙ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ጣሊያን ወልዲያ፣ ሃራ አካባቢ አባብሎና አግባብቶ ካስጠራቸው በኋላ ተኮሰባቸው፤ በተአምር ተረፉ።

እርሳቸውም በመንዙማቸው እንጉርጉሮን አዚመዋል።

'በአገራችን መኖር አትችሉም አሉን፤ ሻምና ሩም ሂዱ አሉን፤ ምን ጉድ ነው ይሄ' የሚሉ ፖለቲካዊ ዜማዎችን አዚመዋል። እንደ ኡስታዝ አብዱልአዚዝ ገለፃ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

መንዙማና ሥነ-ቃል

እያንዳንዱ መንዙማ ይነስም ይብዛ ታሪክ ተሸክሟል። የመንዙማ ስንኞች ቢያንስ ቀደምት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንዴት እንደኖሩ የመተረክ አቅም አላቸው።

አሁን ያሉቱ መንዙመኞች ግን ቀደምት ግጥሞችን በአዲስ ቅላጼ የማዜም ነገር ካልሆነ እምብዛምም አዲስነት አይታይባቸውም።

በመንዙማ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዕውቀትም ተስፋፍቷል።

ማንበብና መጻፍ ሩቅም ብርቅም በነበረበት በያ ዘመን መንዙማ የእስልምና ትምህርት መሠረታዊያንን ለገጠሩ ማኅበረሰብ ለማድረስ አስችሏል ይላሉ ኡስታዝ አብዱልአዚዝ።

የመንዙማ ንሸጣ

የመንዙማ ግጥሞች ጥልቀትና ከፍታ በታላቅ መነቃቃትና ጥሞና ውስጥ መጻፋቸው ነው።

የመንዙማ ደራሲ ድንገት ''ዋሪዳ'' መጣብኝ ካለ ቅኔ ሊዘርፍ ነው ማለት ነው። ንሸጣ ውስጥ ገብቻለሁ እንደማለትም ነው። ድሮ ድሮ በግብታዊነት የሚጻፉ፣ በዘፈቀደ የሚሰደሩ ስንኞች አልነበሩም። አሁን አሁን ካልሆነ።

ንፁህ አማርኛን ብቻ የሚጠቀሙ መንዙማዎች የሉም ባይባልም በርካታ አይደሉም። የሚበዙቱ አረብኛን ከወሎ አማርኛ ጋር ያዳቀሉት ናቸው። ለምን?

የወሎ አማርኛ ወትሮም አንዲያ ያደርገዋል።

"ከአረብኛ ጋር የመጎናጎን ባሕሪው ዘመን የተሻገረ ነው። የወሎ ሕዝብ ችግር መጣብኝ ከማለት "ሙሲባ መጣብኝ" ነው የሚለው። ሙሲባ አረብኛ ነው" ይላሉ ኡስታዝ አብዱልአዚዝ።

ይህ ቋንቋን የማዳቀሉ ነገር መንዙማው ላይም ተጋብቶበታል ይላሉ ኡስታዙ። ቢያንስ በሁለት ምክንያት…

በኢትዮጵያ የኢስላም ታሪክ የወሎዎች ሚና መጉላቱ አንዱ ነው። ቁርዓን፣ ፊቂህ (ኢስላማዊ ሕግጋት ) የቅዱስ መጻሕፍት ትርጉም (ታፍሲር)፣ አረብኛ ቋንቋ እና የአብነት ትምህርት ቤቶች (ማድራሳ) ከወሎና ሀይቅ አካባቢ ነው የመነጩት።

ዛሬም ድረስ የበርካታ መዝጊዶች አሰጋጆችና ሊቃውንት (ሙፍቲሆች) የወሎ ልጆች ናቸው።

መንዙማም መንፈሳዊው ሕይወትን የመግለጫ አንድ የጥበብ አምድ መሆኑ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ይልቅ በዚያ አካባቢ እንዲጎመራ የተመቻቸ መስክ ሳያገኝ አልቀረም። ይላሉ ኡስታዙ።

የአረብኛ ቃላት በመንዙማው እንዲህ በአያሌው መነስነስ ሌላው ምክንያት ደግሞ፤ አንድም የሃይማኖቱ አንኳር ቃላት በአረብኛ መወከላቸው የፈጠረው ሀቅ ሲሆን፣ አንድም ደግሞ የገጣሚዎቹ የቋንቋ ልኅቀት ማሳያ የይለፍ ወረቀት (poetic license) መሆኑ ነው።

ሳኡዲን ያስደመመው የሐበሻ መንዙማ

የነጃሸዒ መስጂድ ኢማም ኡስታዝ አብዱልአዚዝ ናቸው ይህን ግርድፍ ታሪክ የነገሩን።

የቀድሞው የሳኡዲ ዋናው ሙፍቲህ እጅግ የተከበሩት ሼክ ኢብኒባዝ -አሁን በሕይወት የሉም-ነፍስ ይማር (ይርሃመሁላህ) አንድ ቀን ምን አሉ?

'እስቲ የናንተ ሐበሾች ጻፉት የሚባለውን መንዙማ አምጡልኝ!' በዝና ብቻ ነበር አሉ የሐበሻን መንዙማ የሚያውቁት።

ቀረበላቸው። ግጥሞቹን ሰምተው ግን ለማመን ተቸገሩ።

"እንዴት እኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋችን አረብኛ የሆንነው ሰዎች ያልቻልነውን በግጥም መራቀቅ እናንተ ቻላችሁበት?" ብለው መደነቃቸው ይነገራል።

ሼኸ ኢብኑባዝን ወሎ ነበር ማምጣት...የቅኔ አገር...የደረሶች ማንኩሳ...የመንዙማ ቀዬ...የ'መሳኪን' ሼኮች ማደሪያ...