በሳንፍራንሲስኮ የመጀመሪያዋ ጥቁር ከንቲባ በጠባብ ድምፅ አሸነፈች

ለንደን ብሪድ በከተማው ማዘጋጃ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለንደን ብሪድ፣ በሳንፍራሲስኮ የመጀመሪያዋ ጥቁር ከንቲባ ሆነች።

በዚህች ከተማ አፍሪካዊ አሜሪካውያን ቁጥራቸው በጣም አናሳ ነው።

አያቷ በድህነት ያሳደጓት ለንደን ብሪድ ለከንቲባነት ለመብቃት በርካታ ኣውጣ ውረዶችን አልፋለች፤ ትልቅም ስኬት ነው ተብሎላታል።

የ 43 ዓመቷ ብሪድ በጠባብ የድምፅ ብልጫ በማለፏና ባገኘችው የምርጫ ውጤት ደስተኛ እንደሆነች ገልፃለች።

በአሜሪካ ከሚገኙ 15 ትላልቅ ከተሞች ብሪድ ብቸኛዋ ሴት ከንቲባ ነች።

ሳንፍራንሲስኮ ቤት አልባ ምንዱባኖች የበዙባት፣ ከድሃ አገራት ጎዳናዎች ጋር የሚስተካከሉ በቆሻሻ የተሞሉ አውራ ጎዳናዎች ያሉባት፣ የቤት ዋጋ ውድነት የሰራተኛውን ክፍል በኑሮ ውድነት ፈትሮ የያዘባት ከተማ ነች።

አዲሷ ተመራጭ ከንቲባ ከዚህ በፊት ከተማዋን ያስተዳድሩ የነበሩት ኢድ ሊ ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ ተጠባባቂ በመሆን ለአጭር ጊዜ ሰርተዋል፤ ከዛ በኋላ ነው ለቦታው ራሳቸውን በእጩነት ያቀረቡት።

ምርጫው ከተደረገ ሳምንት ያለፈው ሲሆን ውጤቱ የዘገየው ተወዳዳሪዎች ያገኙት የድምፅ ልዩነት ጠባብ በመሆኑ የከተማው የምርጫ ቦርድ በሺዎች የሚቆጠሩ የምርጫ ድምፆችን በድጋሚ ለመቁጠር በመገደዱ ነው።

የከተማዋ የመጀመሪያ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ከንቲባ የነበሩትና ለምርጫው የተወዳደሩት ማርክ ሌኖ ከ ለንደን ብሪድ ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘው የተሸነፉበትን የምርጫ ውጤት ተቀብለውታል።

ሳንፍራንሲስኮን በ1978 ሴት ከንቲባ አስተዳድረዋት የሚያውቁ ሲሆን እኚህ ሴት በአሁን ሰአት የካሊፎርኒያ ሴናተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።