የግሪንፊል ማማ እሳትና የሐበሾች ምስክርነት

የግሪንፊል ማማ እየነደደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለንደን በሚገኘው ግሬንፌል ታወር ሕንፃ ሰባተኛ ፎቅ ላይ ባለ ቤት ውስጥ የተነሳ እሳት ለአደጋ ሰራተኞችና ለነዋሪዎች እድል ሳይሰጥ ሙሉውን ህንጻ እሳት ወረሰው።

በአደጋው የደነገጡ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የወጡ ሰዎች ሁኔታዉን በተረበሸ መንፈስ ይመለከቱት ጀመር።

የእሳት አደጋ ሰራተኞች የአቅማቸውን ያህል ቢጥሩም እሳቱ ግን ህንፃውን ሙሉ በሙሉ ከመበላት አልታደጉትም። ማዳን የቻሉትም 65 ሰዎችን ብቻ ነው።

ህንፃው ጠቁሮ የከሰል ክምር መሰለ።

ይሄንን ክስተት በመገናኛ ብዙሃን የተከታተሉት ከአደጋዉ የተረፉ፣ ጎረቤቶችና የለንደን ከተማ ነዋሪዎች የዚህ ክስተት ልዩ ትዝታ አላቸው።

አብረዉ ሲጫወቱ አምሽተዉ በነጋታው እንዲገናኙ በቀጠሮ የተለያዩት ጓደኛሞች፣ የረመዳንን ጾም አንድ ላይ አፍጥረዉ "ደህና እደሩ" ተባብለዉ የተለያዩ ቤተሰቦች በተኙበት እስከወዲያኛው አንቀላፉ።

"እንደዚህ አይነት አደጋ አይቼ አላውቅ፤ ያንን ሳይ ደግሞ ህንጻው ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ስለማውቅ ደንግጬ ቀረሁኝ" ሲል የገጠመውን ድንጋጤ ይገልጻል አሚር ዮሃንስ ።

ሞገስ ብርሃነ በህንጻዉ አቅራቢያ ከጓደኛዉ ጋር ለአንድ ዓመት ያህል ኖሯል"ወደ ሰማይ ይንቀለቀል የነበረውን እሳት ቴሌቪዥን ላይ ሳይ ይህ ቃጠሎ የአሜሪካ መንትያ ህንጻዎች ላይ ያጋጠመው ነው በማለት ነበር ያሰብኩት" ይላል ሁኔታውን ወደ ኋላ ተመልሶ ሲያስታውስ።

በአንድ በእሳት በሚነድ ህንጻ ስር ሆነህ በቅርብ የምታውቃቸውን ሰዎች፣ ጓደኞችና ዘመድ ሞት ከማየት የከፋ ነገር የለም የምትለዋ ደግሞ ፌሩዝ አህመድ ናት። በተጨማሪም "ህንጻዉ ላይ በቅርብ የምናውቃቸዉ ሰዎች ስለሞቱ እስካሁን ከህሊናችን አልወጣም" ትላለች።

ፌሩዝ ልጇና እናቷ የሆነውን ሁሉ በአቅራቢያው ከሚገኝ ህንፃ በመሆን ተመልክተዋል።

የግሪንፌል አደጋ ሁሌም በአእምሯችን ውስጥ ተሰንቅሮ አለ ስትል የምትናገረው ፌሩዝ ልጇና እናቷ ግን በአንድ ቃል "ይሄንን አጋጣሚ ማውራት አንፈልግም" በማለት ያንን ጥቁር ቀን ዳግም ማንሳት እንደማይፈልጉ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Facebook/Behailu Kebede

የምስሉ መግለጫ,

በኃይሉ ከበደ በአደጋው በጣም የተረበሸ ሲሆን አሁን ህይወቱን ዳግም ለመገንባት እየጣረ ነው

የእውነት አፋላጊው ሸንጎ

በግሪንፊል ማማ ላይ ይኖሩ የነበረውና እሳቱ ከእርሱ ቤት እንደተነሳ ይጠረጠር የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው በጠበቃው በኩል እንደተገለጸው "ምንም የፈጸሙት ስህተት የለም"

የእውነት አፋላጊው ሸንጎ በአቶ በኃይሉ ከበደ ዙርያ ያሉ እውነታዎችን ከጠበቃው አዳምጧል።

ጠበቃ ራጂቭ ሜኑን እንዳሉት ደንበኛቸው በኃይሉ ከበደ አደጋው በደረሰ ጊዜ ስልክ መደወሉን፣ ጎረቤቶቹን ስለሁኔታው እንዲያውቁ ማድረጉን ተናግረዋል። ይህን ሁሉ ያደረገው ጭሱን በተመለከተበት ቅጽበት ነበር።

ስልኩን ብቻ ይዞ በባዶ እግሩ አፓርትመንቱን መልቀቁን፤ ከዚያ በኋላም እሳቱ ወደ ጎረቤት ሲዛመት ተስፋ በመቁረጥ ስሜት በድንጋጤ ይመለከት እንደነበር አብራርተዋል።

ጠበቃ ሜነን ጨምረው እንዳሉት "እሳቱ ድንገተኛ ነው። ደንበኛዬም ኃላፊነቱን የሚወስደብት ምንም አግባብ የለም።"

"አቶ በኃይሉ ከበደ በእርግጥ መልካም ሰው ነው። ምንም ያጠፋው ነገር የለም" ብለዋል ጠበቃው።

ያም ሆኖ እሳቱ በተነሳ ማግስት አቶ በኃይሉ ከበደ ጥፋቱን በሌላ ማላከኩና እሳቱ የተነሳው ግን የእርሱ ፍሪጅ ከፈነዳ በኋላ እንደነበር አንዳንድ ጋዜጦች ሳያረጋግጡ ጽፈዋል።

ከዚያም በሻገር አቶ ኃይሉ ባለሞያ ከመጥራት ይልቅ አንዳንድ የቤት ውስጥ ኤሌክትሪክ ሥራዎችን በራሳቸው ለመስራት ሞክረዋል በሚል ሲተቹ ነበር። ሆኖም ይህንን አቶ በኃይሉ አስተባብለዋል። ፖሊስ ስለ አቶ በኃይሉ ደህንነት በመስጋቱም ለፍርድ ቤት መስካሪዎች የሚደረገው ጥበቃ በሚደረግበት መርሀግብር እንዲታቀፉም ሐሳብ ተሰጥቷል።

የጥፋተኝነት ስሜት

25 ዓመታትን በማማው የኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ በኃይሉ እሳቱ ወደ ሌሎች ሲዛመት ጎረቤቶቹን ለመርዳት ፍላጎት እንደነበረው አጣሪ ኮሚሽኑ አዳምጧል።

"ነገር ግን ምን ማድረግ ይችል ነበር?" ይላሉ ጠበቃው።

ያን ምሽት አቶ በኃይሉ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ቀጥታ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ቃላቸውን መስጠታቸው ታውቋል።

ጠበቃው ደጋግመው እንደሚሉት አቶ በኃይሉ ለፖሊስ መረጃ በመስጠት የተባበሩ ሰው እንጂ የወንጀል ተጠርጣሪ ተደርገው መታሰብ የለባቸውም።

የደህንነት ጉዳይ

በዚህ የእሳት አደጋ ምክንያት በግሪንፌል ታወር ላይ እስከ አሁን ያልተመለሰው"የደህንነት" ጥያቄ አለ።

በ1974 (እአአ) የተገነባውና በ 2016 በ8.6 ሚልዮን ፓውንድ እድሳት ተደርጎለታል የተባለዉ ህንጻ ለምን የደህንነት መጠበቂያዎቹ በአግባቡ በቦታቸው እንዳልነበሩና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች በመገናኛ ብዙሃን ላይ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ሆኖው ነበር።

የአካባቢው አስተዳዳሪ ህንጻው በታደሰበት ወቅት አውቶማቲክ ተቆጣጣሪ እንዳልተገጠመለት ተናግረው ነበር።

"ባለ 17 ፎቅ ተመሳሳይ ህንጻ ውስጥ ስለምኖር ከግሪንፌል ታወር አደጋ በኋላ ሰስጋት ውስጥ ነው የምኖሮው" የሚለዉ ሞገስ በዚህ በሰለጠነ አገር እንዲህ አይነት ቸልተኝነት ማየቱ እንደማይዋጥለት ይናገራል።

"ለሁሉም ሰው የምንኖርባቸዉ ህንጻዎች ጥንካሬ ስለሌላቸዉ እንጠንቀቅ እላለሁ።"

የግሪንፌል ታወር ፍጻሜ በእንግሊዝ አገር ፖለቲካ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል። ለዚህ አደጋ ቀድሞ መደረግ የነበረበት ጥንቃቄ አለመደረጉን የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራዉን እየሰራ ነዉ። ይሁን እንጂ ከዚህ ህንጻ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ቋሚ መጠለያ ስላላገኙ አስተዳደሩ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ላይ ናቸው።