ኢትዮጵያ፦አሲድን እንደ መሳሪያ

ኢትዮጵያዊቷ ሞግዚት፣ ሽዌይጋ ሙላህ በሊቢያ ድብደባና ቃጠሎ ደርሶባት፦ መስከረም 2011

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኢትዮጵያዊቷ ሞግዚት፣ ሽዌይጋ ሙላህ በሊቢያ ድብደባና ቃጠሎ ደርሶባት ነበር

የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ደጃፍን የፍትህ ያለህ ብለው ከሚረግጡ ጉዳዮች መካከል 90 በመቶዎቹ የባልና የሚስት ናቸው።

ከእነዚህ መካከል ደግሞ ላቅ ያለውን ድርሻ የሚይዙት የቤት ውስጥ ጥቃቶቸች መሆናቸውን የድርጅቱ ኃላፊ ወ/ሮ ሜሮን አራጋው ይናገራሉ።

በርግጥ የቤት ውስጥ ጥቃት ሰፊ ነው የሚሉት ወ/ሮ ሜሮን የአካል፣ የስነልቦና፣ የኢኮኖሚ መብት ጥሰት፣ የወሲብ ጥቃቶችን ሁሉ እንደሚጨምር ያሰምሩበታል።

ወደ ቢሯቸው የሚመጡትም ሴቶች እነዚህን ሁሉ ጥቃቶች አልፈው የሚመጡ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

አሁን ግን ይላሉ ወ/ሮ ሜሮን የተለመዱትን ጥቃቶች በህግ ፊት አቅርበን ፍትህ ሳናሰጥ አዳዲሰ የምንላቸው ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየበረከቱ መጥተዋል።

ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል የአሲድ ጥቃትና በቡድን ሆኖ ደፈራ ይጠቀሳሉ።

ማስረጃ 1- ዳንግላ

በ2007 ዓም ነው ነገሩ የሆነው። ለ5 ዓመታት በፍቅር ጓደኝነት አብረው ቆዩ። እርሱ በተለያዩ ሱሶች ስለተጠመደ አልተግባቡም፤ ተለያዩ።

አንቺ የኔ ካልሆንሽ መኖር አትችይም በማለት በተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያደርስ እንደቆየ ወ/ሮ ሜሮን ይናገራሉ።

አክለውም እርሷ የምትሰራውና የምታድረው ሆቴል ውስጥ በመሆኑ ጥቃቱን መፈፀም ባሰበ ጊዜ አብራው ከምትሰራው እና ለእርሱ ጓደኛ ከሆነ ግለሰብ ጋር በመተባበር፣ የምትገባበትን የምትወጣበትን ሰአት በመጠበቅ፣ አሲድ አዘጋጅቶ ልትተኛ በተዘጋጀችበት ወቅት በሯን አንኳኩቶ በመግባት አሲድ ፊቷ ላይ ደፍቶባታል ይላሉ።

በወቅቱ በተደረገ ምርመራም መሬት ላይ "በወደቀችበትም ደጋግሞ እንዳርከፈከፈባትና ከቁምሳጥን ውስጥ ልብሷን በማውጣት እሰይ እንኳን እያለ በእርካታ ስሜት እንደደፋበት ለማወቅ ተችሏል" ሲሉ ያስረዳሉ።

እየተንከባለለች ራሷን እስክትስት ድረስ ድርጊቱን በእርካታ ስሜት እንደፈፀማባት የሚናገሩት ወ/ሮ ሜሮን ይህ ግለሰብ በአሁን ሰአት 19 አመት ተፈርዶበታል።

ልጅቷ በጉዳቱ አይኗን መጨፈን አትችልም፤ ጆሮዎቿ በሙሉ ተቆራርጠዋል፤ ከፊቷ እስከ ጡቷ ድረስ የደረሰውን ጉዳት በሀገር ውስጥ ለማከም ከ 20 ጊዜ በላይ ቀዶ ጥገና አድርጋለች።

በአሁኑ ሰአት በውጭ ሀገር ህክምና ለማግኘት ወደዛው አቅንታለች በማለት የደረሰባትን አካላዊ ስቃይ ያስረዳሉ።

እነዚህ ጥቃቶች ድርጅቱ በ23 አመት የስራ ዘመኑ በተደጋጋሚ ያልገጠመው ነገር ግን አሁን በሩን እያንኳኳ ያለ ጉዳይ ነው በማለት የሚያስረዱት ወ/ሮ ሜሮን በዚህ አመት ብቻ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለት ሶስት የአሲድ ጥቃቶች እንደመጡና እነዚህ ጥቃቶች ትኩረት ያሻቸዋል በማለት ሌላ አስረጅ ይጠቅሳሉ።

ማስረጃ 2- አዲግራት

በዚሁ በ2010 ዓ.ም የሆነ ነው። በአዲግራት ልጅ አብረው የወለዱና ባለመግባባት ምክንያት ትዳራቸውን በስምምነት ያፈረሱ ግለሰቦች ናቸው።

ባል ከሐገር ውጭ ሲኖር እርሷ ደግሞ ኑሮዋን እዛው አዲግራት አድርጋለች።

አንድ ቀን ድንገት በሯ ይንኳኳል፤ ስትከፍት የቀድሞ የትዳር አጋሯ ነው፤ በእጁ አሲድ ይዟል።

እንደመጣ እንኳን አልሰማችም ድንገት በበሯ ተከስቶ አሲድ ፊቷ ላይ ደፍቶ ተሰወረ።

ይህች ሴት ፊቷ ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል።

ሁለት አይኖቿ ጠፍተዋል ጆሮዎቿ አፍንጫዋም እንደተቆራረጠ ወይዘሮ ሜሮን ይናገራሉ።

አዲግራት ሆስፒታል ብትገባም ለ40 ቀናት ህክምና ሳታገኝ በበርካታ ሴቶች ማህበራት ጥረት በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተልካ ህክምና እያገኘች ትገኛለች፤ እስካሁን ድረስ ተጠርጣሪው አልተያዘም በማለት ግለሰቧ ያለችበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Meron Aragaw

የምስሉ መግለጫ,

ወ/ሮ ሜሮን አራጋው፣ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዳይሬክተር

ማስረጃ 3- አዲስ አበባ- ቦሌ ቡልቡላ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የሆነች የ24 ዓመት ወጣት ትዳር መስርታ አንድ ልጅ ወልዳለች። ከትዳር አጋሯ ጋር ባለመስማማቷም በፍቺ ተጠናቀቀ።

ንብረት ክፍፍል ላይ ደርሰው ባለበትም ወቅት የልጃቸውን ሰነድ ልስጥሽ ብሎ ይጠራታል።

ተገናኝተው በመኪናው አብረው እየተጓዙ እያለ ጫካ ያለበት ሰዋራ አካባቢ ሲደርሱ መኪናውን ተበላሸ በማለት ያቆመዋል።

ከዛ ፊቷ ላይ አሲድ ይደፋባታል፤ ይህች ወጣት ግማሽ ፊቷ ነው የተቃጠለው።

ግለሰቡ ተይዞ ህግ ፊት ሲቀርብ የተጠየቀው በአካል ጉዳት ስለሆነ የተፈረደበት 5 አመት ብቻ ነው በማለት ህጉ ላይ ስላለው ክፍተት ክፍተት ወ/ሮ ሜሮን ይናገራሉ።

ድርብርብ ፈተናዎች

የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ስለሚሰራ ሴቶቹ ጥቃት ደረሶባቸው የፍትህ ያለህ ሲሉ ስነልቦናቸው ተጎድቶ፣ አካላቸው ጎድሎ መታከሚያ ቤሳ ቤስቲን ሳይኖራቸው ስለሚመጡ ፈተና ውስጥ ይወድቃል።

እነዚህን ሴቶች ወደ ቀድሞው ጥንካሬያቸው ለመመለስ፣ ጤናቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ እጅ አጥሮት እንደተቸገረም ድርጅቱ ገልጿል።

ቢያንስ እነዚህ ሴቶች አደጋ የደረሰባቸው ሴቶችን በማቆያ ቤት ውስጥ ለማድረግ የቀድሞ አቅሙ በበጎ አድራጎት ህጉ ምክንያት ስለተነጠቀ ፈተናውን እንዳከበደበት ይናገራሉ።

ለዚህም ማስረጃ አድርገው የሚጠቅሱት በቅርቡ ከወደ ሐረር የቢሯቸው ደጃፍ የደረሰውን ጉዳይ በማንሳት ነው።

በሰው ቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ትሰራ የነበረች የ13 ዓመት ህፃን የአስገድዶ መድፈር እና ማስረጃ ለማጥፋት ከወገብ በታች ተቃጥላ ነበር ወደ ቢሯቸው የመጣችው።

ቃጠሎዋ ከፍተኛ እንደሆነ የሚገልፁት ወ/ሮ ሜሮን እስከ አጥንቷ ድረስ የዘለቀ መሆኑን የየካተት 12 ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች መግለፃቸውን ይናገራሉ።

ይህች ታዳጊ የካቲት 12 ሆስፒታል ተኝታ የፍትህም የህክምናም አገልግሎትም እየተከታተለች ቢሆንም የህክምና ወጪዋን ለመሸፈን አቅም እግር ተወርች አስሯቸው ደግ ልብ ያላቸው ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ለማሰባሰብ የባንክ ሒሳብ በእናቷ ስም እንደከፈቱ ተናግረዋል።

ወ/ሮ ሜሮን አክለውም ይህ ማህበር ከ2001 ዓም ጀምሮ የበጎ አድራጎት ህግ በመታወጁ እና በዚህም መሰረት 90 በመቶ ገቢውን ከሀገር ውስጥ መሰብሰብ መቻል ስላለበት በርካታ የህዝብ ማስተማር ስራዎቹ ተቀዛቀቅዘዋል ይላሉ።

እንደቀድሞው በተከታታይነት ማህበረሰቡን ስለ ፆታ እኩልነት ለማስተማር ስልጠና ለመስጠት ተግዳሮት እንደሆነባቸው ያስረዳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሴቶች ዙሪያ በጎ የሆነ እና በአዲስ አቅጣጫ ትኩረት የሚሰጥ አመላካች ንግግሮችን እንዲሁም መልእክቶችን ሲያስተላልፉ ቆይተዋል የሚሉት ወ/ሮ ሜሮን ይህንን ተከትለው የእርሳቸው ማህበር ከሌሎች አቻ ማህበራት ጋር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

"ይህንን ተከትሎ የእርሳቸውንም ጥረት ለመደገፍ የሲቪክ ማህበረሰቡ ድርሻም ስላለው በተለይ ሴቶች ላይ የምንሰራ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ተሰባስበን ወዲያውኑ እርሳቸው ወደስልጣን እንደመጡ ውይይቶችን አድርገናል።" ይላሉ።

በውይይታቸውም በፖሊሲ ደረጃ፣ በህግ አፈፃፀም እንዲሁም በመዋቅር ደረጃ የሴቶች መብት መከበር፣ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል የመንግስት ትኩረት ምን መሆን አለበት የሚለውን ሰፊና ጥልቅ ውይይት በማድረግ የመፍትሄ ሃሳቦችን እንዳሰባሰቡ ይናገራሉ።

ይህንንም የመፍትሄ ሃሳባቸውን ይዘው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመነጋገር ደብዳቤ አስገብተው ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነ ተናግረዋል።

ማህበሩ በተናጠል ደግሞ በቅርቡ ቀዳማይ እመቤት በሴቶችና በህፃናት ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር አብረው ለመስራት ደስተኛ እንደሆኑ መግለጫ ስለሰጡ እርሳቸውንም ለመነጋገር ቀጠሮ እንዲያዝላቸው ደብዳቤ ማስገባታቸውን ጠቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, EWLA

የማህበሩ ታሪክ

የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሰራ ያለ መንግስታዊ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ተቋም ነው።

ይህ ድርጅት ከተመሰረተ 23 ዓመታት የሞላው ሲሆን በእነዚህ አመታት በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሲሰራ ቆይቷል።

አንደኛው ነፃ የህግ አገልግሎት ለሴቶች ብቻ መስጠት ሲሆን ሁለተኛው የህዝብ ማስተማርና የአቅም ማጎልበት ስልጠና መስጠት ነው።

ሶስተኛው የጥናትና ምርምር ስራ ነው። የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በዚህ ዘርፍ ህጎች እንዲለወጡ እና እንዲሻሻሉ የሚሉት ወ/ሮ ሜሮን በዚህም የቤተሰብ ህጉ እና የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ይጠቀሳል በማለት ያብራራሉ።

ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በነፃ የህግ አገልግሎቱ ከ 200 ሺህ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፣ በህዝብ ማስተማርና በአቅም ማጎልበት ስራዎቹ ደግሞ 80 ሺህ ሰዎችን በቀጥታ በማግኘት ስለሴቶች መብቶች ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ በተለያዩ ህትመቶችና ሬዲዮን ፕሮግራሞች በሌሎች መንገዶች ደግሞ 10 ሚሊየን ሰዎችን በመድረስ ውጤታማ ስራ ሰርቷል በማለት ይናገራሉ።

ማህበሩ በአሁን ሰአት 260 በጎ ፈቃደኞች ያሉት ሲሆን በአዲስ አበባ፣ በአዳማ ፣ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ ሃዋሳ፣ አሶሳ እና በ53 ገጠር ቀበሌዎች ነፃ የህግ ድጋፍ ይሰጣል።