ካናዳን በጥበብ ሥራው ያስዋበው ኢትዮጵያዊ

ሲሳይ ከሳለው 'የሰንበት ቀለማት' የተሰኘው የአዳም ረታ መጽሐፍ ሽፋን ጋር Image copyright SISAY SHIMELES
አጭር የምስል መግለጫ ሲሳይ ከሳለው 'የሰንበት ቀለማት' የተሰኘው የአዳም ረታ መጽሐፍ ሽፋን ጋር

ጊዜው በአውሮፓውያኑ 2000 ዓ.ም.፤ ለአራት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብና ዲዛይን የተማረው ሲሳይ ሽመልስ ህይወትን አንድ ብሎ ጀመረ።

ዕድል ፈገግ ያለችለት ሲሳይ በጀርመኗ ሃኖቨር ከተማ በተዘጋጀ ዓውደ ርዕይ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር እንዲሳተፍ ሆነ። ኑሮውንም በጀርመን ተያያዘው፤ በግራፊክስ ዲዛይን ሙያም ተመረቀ ''ከዚህ ወዲህ ነው ሕይወቴ አዲስ መልክ የያዘው'' ይላል ሲሳይ።

ለጥቆም መኖሪያውን ከአውሮፓ ካልጋሪ ወደተሰኘችው የካናዳ ከተማ ቀየረ።

ሥራዎቹ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊነቱን እንዲያንፀባርቁ ብሎም ሕዝቡን እንዲወክሉ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል የሚናገረው ሲሳይ፤ "ፋይዳ ያላቸው' ሥራዎችን መሥራት እመርጣለሁ"ይላል።

በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በ15 ደቂቃ ውስጥ የሰዎችን ፊት በመሳል እራሱንና ሥራውን ያስተዋውቃል።

"ብዙውን ጊዜ ከሥራዬ ይልቅ የቆዳዬን ቀለም ወይም አመጣጤ ላይ የሚያተኩሩ ሰዎች ያጋጥሙኛል" የሚለው ሲሳይ "አንዳንዴ አዝናለሁ ... 'በዚህ እንለካካ?' ያስብለኛል" ሲል ቁጭቱን ይገልፃል።

ከሁሉም በበለጠ ግን እንደ አፍሪካዊነቱ በምዕራቡ ዓለም ማንነቱን የሚገልጹ ሥራዎች ለሕዝብ ማቅረብ በመቻሉ ደስታ እንደሚሰማውም ይናገራል።

«ፋይዳ ያለው ሥዕል». . . ?

የቀሰመውን የግራፊክስ ዲዛይን ትምህርት ሥራ ላይ በማዋል በካልጋሪ ፖሊስ ጣቢያ ግድግዳዎች ላይ ሥራዎቹ በቋሚነት ተሰቅለውለታል።

አብዛኛውን ጊዜ የግራፊክስ ዲዛይን ሲባል የማስታወቂያ ሥራን ተኮር ያደረጉ ሥራዎች የሚቀርብበት ነው የሚለው ሲሳይ፤ የእርሱ ፍላጎት ግን የሥዕሎቹን የጀርባ ማንነት ማጥናት እንደሆነ ያስረዳል።

ለዚህም ነበር የመመረቂያ ሥራውን 'የሕይወት አዕማዶች' በማለት ፍቅር፣ ተስፋ፣ እምነት፣ ትህትና፣ ምህረትና ምስጋና ላይ ያተኮረው።

ከእነዚህም መካከል 'እምነትና ተስፋ የተሰኙት' ሥዕሎቹ ተመርጠው በካልጋሪ ፖሊስ ጣቢያ ለመሰቀል በቅተዋል።

የተገነቡበት መንፈስም አብሮ የመሥራትን፣ በተስፋ አብሮ የማደግን፣ ለአዳዲስ ነገሮችና ለለውጥ መዘጋጀትን እንዲያመላክቱ እሳቤ ውስጥ በማስገባት ነበር።

ሥዕሎቹ ከሌላው ተለይተው የተመረጡበት ምክንያትም "በሃገሪቱ ያለውን የፖሊሱንና የስደተኛውን ሕይወት እንዲያቆራኙ እና የሁለቱን አብሮ የመሥራት ፍላጎት እንዲያነሳሱ ተደርገው በመሠራታቸው" እንደሆነ ይገልፃል።

በተለያዩ ቦታዎች እንደሚሰማው በፖሊሱና በስደተኛው ሕብረተሰብ መካከል ያለው የሃሳብና የድርጊት አለመገጣጣም ብዙ ችግሮችንና ሕፀፆችን እንዳስከተለ ይናገራል።

ለሲሳይ እነዚህ ሥራዎቹ በፖሊስ ጣቢያው መሰቀላቸው ከዚህም ያለፈ ትርጉም አለው።

"እኛም በተሻለ መንገድ እራሳችንን ማሳየት እንችላለን፤ 'በበኩላችን የምናደርገው አስተዋጽዖ አለ' የሚለውን ሀሳብ የሚወክሉ ሥራዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ" ይላል።

ለካልጋሪ ማሕበረሰብ ትርጉም ሰጪ ሥራዎች በመሆናቸው ፋይዳ ያላቸው ሥዕሎች እንደሆኑም ይናገራል።

Image copyright SISAY SHIMELES
አጭር የምስል መግለጫ 'የሕይወት አዕማዶች' ከተሰኘው የሲሳይ ሥራ ከፊሉ

የኩራት ምሳሌ

በካልጋሪ ነዋሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙት ሥራዎቹ "ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ትውልድ እንደ ምሳሌ ሊቀርቡ የሚችሉ እንደሆኑ እምነቴ ነው» ይላል ሲሳይ።

«የመጪውን ትውልድ የሚያነቃቁና የወጣቱን የወደፊት ተስፋ ብሩህ የሚያደርጉ ሥራዎች ናችው» በማለት ያስረዳል። «እስቲ ሥራዎችህን አቅርብልን» የሚሉ ጥሪዎች ከተለያዩ ተቋማት እንደሚደርሱት የሚናገረው ሲሳይ፤ ወጣቶች ሥራዎቹን ሲመለከቱ «የመነሳሳትና የኩራት መንፈስ ሲፈጥር አስተውላለሁ» ይላል።

«እዚህ ሃገር በተለምዶ 'ኢንዲጂነስ አርት' ብለው የሚጠሩትን ዓይነት ሥራ እየሠራሁ ነው፤ አልፎም ሥራዎቼ የማሕበረሰባችንን ማንነት እያንፀባረቁና ለየት ያለ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ይሰማኛል።»

«ይህን በማድረጌ ደግሞ እጅጉን ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ብዙዎች 'ድምፃችን ሆነሃል' ይሉኛል» ይላል የሚሰማውን ኩራት ሲገልፅ።

«በባህላችን 'ምልሶች' ነን፤ ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያውያን እራሳቸውንም ሆነ ችሎታቸውን ገፍተው ሄደው አያቀርቡም፤ ጨምሮም በምንኖርበት ሕብረተሰብ ውስጥ ለውጥ መፍጠር የሚለው ሃሳብ ገዥ አይደለም። በተሰማራንበት በማንኛውም ሙያና ችሎታ ይህን የምናደርግበት ዕድሉም ጠባብ ነው።»

ሆኖም ግን ሲሳይ ከሃገሩ ልጆች በተለየ ይህ ዕድል ለእርሱ በመከፈቱ ይህን ተልዕኮ የመወጣት ግዴታም እንዳለበት ይሰማዋል። በተለይ የሚሠራቸውን ሥዕሎች ለሕዝብ በሚያቀርብበት ጊዜ «አፍሪካዊያንም ይህን መሠራት ይችላሉ» የሚለውን ስሜት በምዕራባውያን ላይ መፍጠር እንደሚፈልግ ይናገራል።

«ከዚያ ባለፈም በውጪው ዓለም የሚወለዱና የሚያድጉ በብዛት ከወላጆቻቸው ወይም ከማንነታቸው ጋር የሚያስተሳስራቸው ሰንሰለት ልል በመሆኑ ሥራዎቼን በመመልከት ''እኛም እንችላለን'' የሚለውን ስሜት እንዲፈጥርባቸው እፈልጋለሁ።»

ይህን ለማሳካት ደግሞ እስካሁን የሠራቸውና ለሕዝብ ያቀረባቸው ሥዕሎች ጥርጊያ መንገድ እንደሆኑ የሚሰማው ሲሳይ፤ ወደ ፊት ለመጪው ትውልድ «የተለያዩ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶቻችንን ማስተማርን ከግምት ውስጥ ያስገባ በሥነ-ጥበብ የተደገፈ «እራስን የማወቅ ትምህርታዊ ጉዞ» እንደሚያቅድ ይናገራል።

Image copyright SISAY SHIMELES
አጭር የምስል መግለጫ በካልጋሪ ከተማ መንገዶቸ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በቋሚነት የቀረቡት የሲሳይ ሥራዎች

በቀለማት የተዋቡ መንገዶች

ከዚህ ቀደም ሥራዎቹን በተለያዩ ቦታዎች ለዕይታ የሚያቀርብ በመሆኑ እራሴን 'ስቱድዮ አርቲስት' ከሚባሉት ነው የምፈርጅው የሚለው ሲሳይ፤ አሁን የተሰማራበት ዘርፍ ያልተለመደ እንደሆነ ያስረዳል።

የካልጋሪ ከተማ አስተዳደር ለሕዝብ ዕይታ ለሚቀርቡ የጥበብ ሥራዎች ባለው ትኩረት ምክንያት የከተማው ነዋሪዎች እራሳቸውን የሚገልጹበትና ችሎታቸውን የሚያዳብሩበትም ሆነ የሚያንፀባርቁበት ዕድል ሰፊ ነው። ሲሳይ እነዚህን ዕድሎች ከተጠቀሟቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ለሁለት ዓመታት 'የተቀባች ከተማ' በተሰኘ ሃሳብ የተለያዩ ሠዓሊዎችን ባዋቀረ የከተማው ተነሳሽነት ከሌሎች ሠዓሊዎች ጋር ተመርጦ በከተማው ማስዋብ ሥራ ላይ ተሳትፏል።

የካልጋሪን ከተማ ከሚያስውቡት ሥራዎቹ መካከል የምስራቅ አፍሪካ ውዳሴ በሚል ርዕስ ዙሪያ 'የነፃነት ክብረ በዓል' የተሰኘ ቁመቱ 3 ሜትር በ 5 ሜትር የሆነ ሥራው 'ኢንተርናሽናል' በተሰኘው ጎዳና ላይ በቋሚነት ተሰቅሏል።

ከዚያ ውጪ የተለያዩ የከተማው ማስታወቂያዎች፤ በመብራት ዘንጎች እንዲሁም የመብራትና የስልክ ጋኖች ወይም መቁጠሪያዎችን በማስዋብ ሥራ ላይ እንደተሳተፈም ይናገራል። እነዚህም ሥራዎቹ ከሕዝቡ ጋር በይበልጥ እንዲተዋወቅ ያደረጉት መሆኑን ይገልፃል። የሲሳይ ስልት ደግሞ ለየት ያለ ነው። የምዕራቡን የሥዕል ዘይቤ ከአፍሪካ ወይም ከኢትዮጵያ ጋር በማደባለቅ የእራሱን ዱካ በከተማው ላይ እንዳስቀመጠ ይሰማዋል።

በተጨማሪም ይህን የመሳሰሉ ዕድሎች በመከፈታቸው «ለሕዝቤና እኔን ለሚመስሉ ሌሎች ድምፅ እንደሰጠሁ ያህል ነው የሚሰማኝ» የሚለው ሲሳይ፤ ማንነቱንና አመጣጡን ከማንፀባረቅ ወደ ኋላ እንደማይል ይናገራል። ይህ ሁሉ ስኬት ግን በቀላሉም ሆነ ያለፈተና አይመጣምና አልፎ አልፎ የሥዕሎቹ ፈጣሪ እርሱ መሆኑን የሚያውቁ ሰዎች በቆዳው ቀለምም ሆነ በአፍሪካዊነቱ እንደሚገረሙ ይነግረናል።

«ቆዳዬ ይለቅ አይለቅ ለማየት እሰከመንካት የደረሱ መደበኛ የሆኑ ሰዎች አጋጥመውኛል» ቢልም ሙያውን የሚረዱት ደግሞ ለሥራው፣ ለችሎታውና ለብቃቱ ታላቅ አክብሮት እንዳላቸውና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሥራውን እንዲያቀርብም ሆነ እንዲያስተምር እንደሚጋበዝ ይናገራል።