የክልል እንሁን ጥያቄ እዚህም እዚያም?

የኢትዮጵያ ካርታ Image copyright Wikimap

ባለፈው ሳምንት በሃዋሳ፣በወላይታ ሶዶና በወልቂጤ በተፈጠሩ ግጭቶች ከአስር ሰዎች በላይ ህይወታቸውን ሲያጡ በርካቶች ላይም የአካል ጉዳት ደርሷል።ንብረት ወድሟል፤ብዙዎችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ጠዋት ሃዋሳ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በወላይታ ሶዶ በመገኘት ከአካባቢዎቹ ኗሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቶቹ ህብረተሰቡን ይወክሉ ዘንድ የተለያዩ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በአካባቢዎቹ በተደረጉት ውይይቶች በእያንዳንዳቸው ከ800 በላይ ተሳታፊዎች እንደተገኙ ይገመታል።

ከሲዳማ ህዝብ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ከተነሱ ጉዳዮች ለዓመታት ሲነሳ የቆየው የሲዳማ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄና በሲዳማ ዘመን መለወጫ ጫምባላላ ዋዜማ በተፈጠረው ግጭት የተሳተፉ ተጠያቂ ይሁኑ የሚሉት ዋነኞቹ እንደነበሩ የሲዳማ ዞን የባህልና ቱሪዝም ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግጭቱ እጃቸው ያለ መጠየቃቸው አይቀሬ እንደሆነ ሲያረጋግጡ በክልል እንደራጅ ለሚለው ጥያቄ ግን አስቡበት ተወያዩበት ማለታቸውን ሃላፊው ይናገራሉ።

ጥያቄው ህገመንግስታዊ በመሆኑ ህገመንግስታዊ ምላሽ የሚያገኝ እንደሆነ ነገር ግን ዋናው የሲዳማ ህዝብ በጉዳዩ ላይ በስፋት ከታች እስከላይ ሊወያይበት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት መስጠታቸውን አቶ ጃጎ ተናግረዋል።

እንደ ሃላፊው አገላለፅ ከግጭቱ ጀርባ ሲዳማዎች ሌሎችም ሊኖሩበት ይችላሉ።ይህ ደግሞ በሂደት የሚገለፅ ሲሆን በማጣራት ሂደቱ የበኩሉን ለማድረግም ህዝቡ ዝግጁ ነው።

በደቡብ ክልል ሶስት ከተሞች በተፈጠሩ ግጭቶች 15 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

በተመሳሳይ በወላይታ ሶዶ በተደረገው ውይይትም ከግጭቱ ጀርባ ያሉ በህግ ይጠየቁ እንዲሁም በክልል እንደራጅ ጥያቄ መነሳቱን በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ህግ መምህር አቶ ተከተል ላቤና ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሲዳማ ብሄር የክልልነት ጥያቄ እያነሳ መሆኑ ክልሉ በአንድ ላይ መኖር አይችልም የሚል እሳቤ እንዲያዝ ማድረጉን እንዲሁም ኦሞቲኩ የክልሉ ህዝብ በብዙ መልኩ ኢፍትሃዊነትን የያስተናገደ መሆኑን በመግለፅ የክልል እንሁን ጥያቄው መቅረቡን አቶ ተከተል ያስረዳሉ።

"ጋሞ ጎፋን ፣ ወላይታ ዞን፣ዳውሮና ኮንታ አካባቢን አካቶ ኦሞቲክ ክልል እንዲፈጠር እንፈልጋለን በሚል ነው ጥያቄው የቀረበው" ይላሉ አቶ ተከተል።

ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግስት ራሱ በብዙ መልኩ ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ሃሳቦች መሰንዘራቸውን የሚናገሩት አቶ ተከተል በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንም ቢሆን የመንግስት ሃላፊዎችን ጨምሮ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ማስረገጣቸው እንዳስደሰታቸው ይገልፃሉ።

እንደ አካባቢው ተወላጅና እንደ ምሁርም ክልል መሆን መፍትሄ ይሆናል ወይ?የሚል ጥያቄም አቅርበንላቸው ነበር።

ችግሩ ውስብስብ ከመሆኑ አንፃር ክልል መሆን መፍትሄ ይሆናል አይሆንም የሚለውን ለመመለስ ጥናት ያስፈልጋል ይላሉ።ቢሆንም ግን የክልል እንሁን ጥያቄ በቂ መሰረት ያለው እንደሆነ ያምናሉ። ምክንያቱም ጥያቄው ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲሁም የፖለቲካ ውክልና አለመኖር የወለደው መሆኑን ያስረዳሉ።

በክልል መደራጀቱ ለማእከላዊው መንግስት መቅረብ ማስቻሉ የጥያቄው አዎንታዊ ገፅታ ቢሆንም ፍትሃዊነትን ማስፈን ከተቻለ ግን አሁን ባለው አደረጃጀትም መቀጠል እንደሚቻል ያምናሉ።

ተያያዥ ርዕሶች