"2 ሚሊየን ሰው ይገኛል ብለን እንገምታለን" አቶ ስዩም ተሾመ

‹‹2 ሚሊየን ሰው ይገኛል ብለን እንገምታለን›› አቶ ስዩም ተሾመ

የፎቶው ባለመብት, Seyoum Teshome /Facebook

ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድጋፍ ለመስጠት ያለመ ሰለማዊ ሰልፍ የፊታችን ቅዳሜ 16/2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተሰምቷል።

ከሰልፉ ዋና አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት መምህር እና ጦማሪ አቶ ስዩም ተሾመ ለቢቢሲ እንደገለፁት፣ ሰልፉን ለማካሄድ የሚያበቃው ሂደት 75 በመቶ ያክል ተጠናቋል።

"የሰልፉ ዋና ዓላማ ዲሞክራሲያዊ መብታችን መጠቀም ብሎም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እየወሰዷቸው ላሉ መልካም ጅምሮች ድጋፍን መስጠት ነው፣" ያሉት አቶ ስዩም፤ በቅርቡ ከእስር የተፈቱት ሃብተሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) እና ስንታየሁ ቸኮል ጨምሮ ስድስት ሰዎች በግል ተነሳሽነት ሰልፉን እያስተባበሩ እንደሆነም አረጋግጠውልናል።

የድጋፍ ሰልፉ ዕቅድ ይፋ ከተደረገ በኃላ የተለያዩ ተዛማች ጥያቄዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ መንሸራሸር ይዘዋል።

በገዥው ፓርቲ አባላት መካከል የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ እንዳየለ የአደባባይ ሚስጢር በሆነበት በአሁኑ ሰዓት ከዚህ የድጋፍ ሰልፍ በስተጀርባ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የመጡበት የኦህዴድ ጣልቃ ገብነት የመጀመሪያው ነው።

አቶ ስዩም በበኩላቸው ከዚህ የድጋፍ ሰልፍ ጀርባ አንዳችም የፖለቲካ ፓርቲ ጣልቃ ገብነት እንደሌለ ያስረዳሉ "እኔ የማንም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፣ ከእኔም ጋር በሰልፍ አዘጋጅነት ያሉት ለምሳሌ እነ አቶ ጉደታ ገለልቻ፣ ስንታየሁ ቸኮል እና አበበ ቀስቶ በዚህ ስርዓት ታስረን ለብዙ ጊዜ ስንሰቃይ የነበርን ሰዎች ነን፣"ብለዋል።

ሁለተኛው ጥያቄ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ላይ ቆይታቸው ገና ድፍን 100 ቀን ባልሞላበት ሁኔታ እንዲህ ያለው የድጋፍ ሰልፍ መዛለቂያው ያልታወቀውን የአመራር ብሂል ቀድሞ ማመስገን አይሆንም ወይ? የሚለው ነው።

"እንዲህ ባለ ቀን ስሌት ውስጥ ከመግባት ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያሳዩ ያሉትን መልካም እርምጃ መደገፍ እና ማበረታት አግባብ ነው" ብለው በማመን ሰልፉን እንደጠሩ አቶ ስዩም ያስረዳሉ።

የህወኃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሰሞኑ ያወጣው መግለጫ ለአስተባባሪዎቹ ይሄንን መሳይ የድጋፍ ሰልፍ እንዲያቅዱ እንደ አንድ ምክንያት እንደሆነ የጠቀሱት አስተባባሪው የሰልፉ ዋነኛ ምክንያት ግን "ዲሞክራሲያዊ መብታችንን በተግባር ለማረጋጋጥ መሻት ነው" ብለዋል።

መምህር እና ጦማሪ ስዩም ተሾመ በቅዳሜው ሰልፍ በግምት 2 ሚሊየን እና ከዚያ በላይ ሰው ይሳተፋል ብለው እንደሚያስቡ ለቢቢሲ አክለው ተናግረዋል።