"የኢትዮጵያ ህዝብ ከኤርትራ ጋር ሰላም እንዲኖር መፈለጉ አዲስ ነገር አይደለም" ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ

የፎቶው ባለመብት, MoI Eritrea

ኢትዮጵያ የአልጀርስ ስምምነት መቀበሏን ተከትሎ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አንድ የልዑካን ቡድን ወደ አዲስአበባ እንደሚልኩ ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት ዛሬ በኤርትራ ቴሌቪዥን የሰማዕታት ቀንን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ሲሆን ጉዳዩን በቀጥታና በጥልቀት ለማወቅና ቀጣይ የስራ እቅድ ለማውጣት እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል።

"የሁለቱ ህዝቦችና ሀገራት ተደጋጋፊነት፣ የሁለትዮሽ ጥቅም እና እድገት ከሁለት ትውልዶች በላይ የተደከመበት እና የተሰዋንለት ዓላማም ስለሆነ ቀዳሚነት ሰጥተን የምንሰራው ስራ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ "ለይስሙላና ለህዝብ ግንኙነት ስራ ሳይሆን የህዝቡን ፍላጎት ለሟሟላት ነው" ብለዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

"የኢትዮጵያ ህዝብ ከኤርትራ ጋር ሰላም እንዲኖር መፈለጉ አዲስ ነገር አይደለም" ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝብ ለአምሳ ዓመታት ያህል ዓለም አቀፍ አጀንዳን ለማስፈፀም እንደተሰቃየ ገልፀው ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ታግለው ነፃ ለመውጣትና አዲስ ምዕራፍ ሊጀምሩ ቢሽቱም ሊሳካ አልቻለም እንዳልቻለም ገልፀዋል።

"ይህ ጥሩ ጅማሮ ሳይሳካ መስመሩን የሳተ ዓለም ዓቀፍ ፖሊሲ ምክንያት የህይወት መጥፋት፣ መስዋዕትነት አስከፍሎናል። በጣም ፈታኝ ነው"ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በቅርብ ጊዜ በቀጠናው በተለይም በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ሂደቶች አስፈላጊ የሆነ ምልከታ ያስፈልገዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በተለይም የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ እንደተጎዱና በተለይም ህወሐት ከሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ጋር ተያይዞ ህዝቡ ገፈት ቀማሽ እንደሆነ አስምረውበታል።

ከሁለቱ ኃገራት መቃቃር ጋር ተያይዞም የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ማሻከሩ እንዲሁም የሁለቱ ኃገራት ህዝቦችና መዋዕለ-ሀብት በቀጠናው ላይ ሊያመጡት የሚችለውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ኪሳራ አምጥቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በዚህም ኢትዮጵያን ተወቃሽ አድርገዋል።

"በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የደረሰውን ግፍም ህዝቡ በቃኝ በማለቱ ኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ ጎዳና ላይ ናት። ይህ መጨረሻው ምንድን ነው? እንዴትስ ይሳካል? የሚሉት ጥያቄዎች አንገብጋቢ ጥያቄዎች ስለሆኑ መመለስ አለባቸው" ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ከኤርትራውያን ጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም መኖር እንደሚፈልግ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ "የኢትዮጵያ ህዝብ ከኤርትራ ጋር ሰላም እንዲኖር መፈለጉ አዲስ ነገር አይደለም" በማለት ተናግረዋል።

ኤርትራ ፖሊሲ ስታረቅ የሀገሪቱንና የአለም እውነታ ከግምት ውስጥ እንደሚያስገቡ ጠቅሰው አጎራባች ሀገሮችን ባጠቃላይና በዋነኛነት ኢትዮጵያን ከግምት እንደሚያስገቡም ገልፀዋል።