የተጠበቀውን ያህል የቤንሻንጉል ተፈናቃዮች አልተመለሱም

ተፈናቀዮች

ባለፈው ጥቅምት ወር በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማንነት ላይ ያነጣጠር ጥቃት በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ከደረሰ በኋላ የተፈናቀሉ ዜጎች እንዲመለሱ ጥሪ ቢቀርብም የተመላሾች ቁጥር የተጠበቀውን ያህል አልሆነም።

ተመላሾች በአንፃሩ ቃል የተገባውን ያህል ማቋቋሚያ አላገኘንም ይላሉ። ትናንት በተቀሰቀሰ አዲስ ግጭት የሰዎች ህይወት አልፏል።

"ወደዚህ የመጣሁት ያለኝን ንብረት ጥዬ ነው። በምን ተቋቁሜ ለመስራት ነው ወደዚያ የምመለሰው?" ስትል ጥሩ ፈንታየሁ ትጠይቃለች። ጥያቄው የጥሩ ብቻ አይደለም። በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችም ጭምር እንጂ።

ጥሩ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ተፈናቅለው ባህር ዳር ከተማ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ከተጠለሉ ከመቶ ሰላሳ የሚልቁ ግለሰቦች አንዷ ናት።

የመኖሪያ ቀየዋን ጥላ ከተፈናቀለች ወራት ተቆጥሯል፤ በባህር ዳር የምግብ ዋስትና ግቢ ከዚያም በተለያዩ አብያተ ክርስትያናት ቅፅር ውስጥ መጠለያዋን አድርጋለች።

የሀያ አምስት ዓመቷ ጥሩ የሁለት ልጆች እናት ስትሆን የአምስት ዓመት ልጇን ከዘመድ አስጠግታ ያለፉትን ሁለት ወራት በቤተ ክርስትያኑ ውስጥ ኖራለች።

የካማሼ ዞን ተፈናቃዮች አሁንም ስጋት ላይ እንደሆኑ ገለፁ

"የክልሉን መንግሥት በእግዚአብሔር ስም ጠይቁልን..."

ተፈናቃዮች ወደ ቀደመ መኖሪያቸው እንዲመለሱ የቀረበው ጥሪ ጥሩን ያሳመናት አይመስልም። "ተመልሼ ሄጄ የምሰራው የለም። መንግሥት መጠለያና መቋቋሚያ ሰጥቶን እራሳችንን እንድናስተዳድር እጠብቃለሁ" ስትል ትናገራለች።

አስተያየቷን ሌላኛው ተፈናቃይ አቶ አዕምሮ ተገኘም ይጋሩታል።

ያለፉትን ሰባት ዓመታት በኖሩበት በካማሼ ዞን የሎጂ ጋንፎይ ወረዳ ግብርናን እና የልብስ ስፌት ሥራን አጣምረው በመስራት ይተዳደሩ ነበር።

ባለፈው ጥቅምት ብሄር ተኮር ጥቃት ሲሰነዘር "ተደብድቤ፥ በህክምናና በፀበል ነው የዳንኩት፤ የተመታሁት እጄ አሁንም በቅጡ አይሰራም" ይላሉ።

የስፌት መኪናቸው መቃጠሉ እንዲሁም ከብቶቻቸውን ጥለው መምጣታቸው ወደነበሩበት መመለስን አዳጋች እንዳደረገባቸው ይናገራሉ።

ቢቢሲ መፈናቀል በተከሰተበት የበሎጂ ጋንፎይ ወረዳ ተገኝቶ መረዳት እንደቻለው የተመላሾቹ ቁጥር ከስድሳ አይዘልም፤ ከእነዚህም መካከል አርባ አምስት ያህሉ ብቻ ከአራት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ እርቃ ከምትገኘው የባህር ዳር ከተማ የተመለሱ ሲሆን አስራ አምስት አባዎራዎች ደግሞ ተጠልለውባት ከነበረችው የወረዳው መዲና ሶጌ ከተማ የተመለሱ መሆናቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፀጋየ ተሰማ ገልፀውልናል።

"በእኛ ክልል እና በአማራ ክልል ባለስልጣናት የተቋቋመ ኮሚቴ አለ፤ 'ኮሚቴውም ተፈናቃዮቹን ለመመለስ በመስራት ላይ ይገኛል" ሲሉ አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሕዝብ ጋር በተደረገ ውይይት ፀጥታ መሪ የስጋት ምንጭ መሆኑን መረዳታቸውን የሚያስረዱት አቶ ፀጋየ በስፍራው በቂ የሆነ ፀጥታ አስከባሪ ኃይል መስፈሩንም ጨምረው ገልፀዋል።

የአማራ ክልልን ወክለው ተፈናቃዮችን የመመለስ እና የማቋቋማው ሥራን ሲያስተባብሩ ያገኛናቸው በቤንሻንጉል ክልል የብዐዴን ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ኃይሉ የፀጥታ ችግሮችን ከመቅረፍ በዘለለ ተመላሾቹ ወደቀደመ መተዳደሪያቸው እስኪመለሱ ድጋፍ የመቸር አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ ተመልሰው ለሄዱ ሰዎች የቤት ውስጥ ቁሳ ቁስ እየተከፋፈለ ይገኛል፤ የእርሻ ወቅት በመሆኑ ጸረ አረምና መርጫ ተገዝቷል፤ የሳርና እንጨት ቤት የተቃጠለባቸው ሰዎች ተለይተው በክልሉ ድጋፍ ቤት ይሰራላቸዋል።

ይሁንና ወደ ቤንሻንጉል ተመለሱ የሚለውን ጥሪ ያልተቀበሉ 136 አባዎራዎች እስካሁንም በባህር ዳር ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴዴራል ተጠልለው እየኖሩ ሲሆን፥ በአማራ ክልል ልዩ ልዩ ወረዳዎች ወደሚገኙ ዘመዶቻቸው የሄዱ ተፈናቃዮች መኖራቸውንም አረጋግጠናል።

ለተፈናቃዮቹ የሚደረገውን ድጋፍ፥ ከሶጌ ከተማ አስራ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው የበለው ዴዴሳ ቀበሌ ሄድን እውነታውን ለመመልከት ያደረግነው ጥረት የዞኑ ባለስልጣናትን ይሁንታ ሳያገኝ ቀርቷል።

ለሰዓታትን እንድንቆይ በተገደድንበት የወረዳው አስተዳደር ፅህፈት ቤት ውስጥ ውጥረት የነገሰበት ስብሰባ በእሁድ ቀን ሲከናወን ያስተዋልን ሲሆን፥ ከአስተዳደራዊ ችግሮች ጋር በተያያዘ በዞኑ በቅርቡ ሹም ሽር ሊኖር እንደሚችል የፅህፈት ቤቱ ሰራተኞች ግምታቸውን አካፍለውናል።

በካምሽ ዞን በጉምዝና በአማራ እንዲሁም በኦሮሞ ተወላጆች መካከል ለዓመታት የዘለቀ መሬት ተከራይቶ በማረስና ምርትን በመካፈል ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነት እንዳለ ነዋሪዎችም የአጥቢያው ባለስልጣናትም ያስረዳሉ።

ይሁንና የስራ ቅራኔዎች እንዲሁም ግለሰባዊ ግጭቶች የብሄር መልክ የሚይዙባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት እንዳልሆኑም ይመሰክራሉ።

ከወር በፊት ከባህር ዳር ወደ ቤንሻንጉል የተመለሰውና በስልክ ያነጋገርነው አርሶ አደር ግን ቃል የተገባውን ያህል ማቋቋሚያ አለማግኘቱን ወደ ግብርናው ለመመለስ አለመቻሉንም ገልጾልናል።

ባህር ዳር ሳለ "ወንድሞቻችንን፣ እህቶቻችንንና ንብረታችንን ወዳጣንበት ቦታ አንመለስም" ቢሉም ነገሮች እንደሚመለሱ ቃል ተገብቶላቸው ነበር። "ሙሉ ቀለብ ይሰጣችኃል። ቤት ይሰራላችኋል። ለወደመባችሁ ንብረት ካሳ ይሰጣችኋል ተብለን ነበር" ይላል።

ወደ ቤንሻንጉል ሲመለስ ግን የጠበቀውን እንዳላገኘ ይናገራል። ሰፊ ቤተሰብ ላለው ሰው ከማይበቃ ስንዴ፣ ድስትና ጄሪካን ያለፈ የተሰጣቸው ባለመኖሩ ያማርራል።

"ቤት ያላችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ ተባለ። ቤት የሌለን በረንዳ ላይ ዝናብ እየመታን፣ ረሀብ እየተጫወተብን ነው" ሲል የጠበቀውን ስላላገኘ እሮሮውን ያሰማል።

በሌላ በኩል በዚያው በቤንሻንጉል ክልል ማንዱራ ወረዳ ትናንትና በጉሙዝ በተቀሰቀሰ ግጭት ሰዎች መሞታቸውን ከወረዳው አስተዳዳሪ አቶ መልኬ ማረጋግጥ ችለናል።

አስተዳዳሪው ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ