ሃውዜንን በትውስታ

ንጉስ ኃይለስላሴ

ንጉስ ኃይለስላሴ እባላለሁ፤ በ 1972 ዓ.ም ሀውዜን ውስጥ ነው የተወለድኩት።

ሰኔ 15 ፤ 1980 ዓ.ም ቀኑ ረቡዕ ስለነበር ሰው አገር አማን ነው ብሎ ገበያውን እየከወነ ነበር። የውጊያ አውሮፕላኖች መጡ። ሌላ ግዜ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደብድበው ስለሚመለሱ እንደዚያው መስሎን ነበር።

ያኔ የስምንት ዓመት ህፃን ብሆንም ክስተቱን በደንብ አስታውሰዋለሁ።

አዋቂዎቹ እኛን ወደ ቤት እንድንገባ አደረጉ። ወድያውኑ ድብደባው ጀመረ። እኛ ቤታችን ውስጥ መሸሸግያ ጉድጓድ ስለነበርን እዚያ ተሸሸግን።

ሻይ ቤት ስለነበረን፤ ወላጆቼ ደግሞ እዚያው ቀሩ።

ከሰዓታት ድብደባ በኋላ እናቴ፣ ወንድሜ፣ አክስቶቼና አጎቶቼ ባጠቃላይ 15 የቤተሰባችን አባላት ሬሳ ተቆፍሮ ወጣ።

እኔን ጨምሮ ሌሎች 15 ሰዎች ደግሞ ከተቀበርንበት ተቆፍሮ ወጣን።

ቤታችን ከመሰረቱ ፈራርሷል። ዘመዶቼ ያኔውኑ ወደገጠር ወሰዱኝ። ከዚያ አያቴ ዓዲግራት ይኖሩ ስለነበር፤ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ እሳቸው ጋር ተማርኩ።

እንደገና ወደ ሓውዜን ተመልሼ በላቤ ራሴን አሳደግኩ። በህይወት የተረፉት ወንድሞቼንም ረዳሁ።

ያኔ የሚያስተምረኝም ሰው ስላልነበረ አስረኛ ክፍል ላይ ትምህርት አቁሜ ወደ ስራ ገባሁ።

አሁን ለዲፕሎማ እየተማርኩ ነው፤ ልመረቅ አንድ ዓመት ይቀረኛል።

የሶስት ልጆች አባት ነኝ። ልጆቼ እኔ ላይ የደረሰው እንዲደርስባቸው አልሻም።

ከጭፍጨፋው የተረፉ 5 ወንድሞች አሉኝ። ታናሻችን እናታችን ስትሞት ገና የአንድ ዓመት ህፃን ነበር።

እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ይህን ጭፍጨፋ ያስፈፀሙ ሰዎች በህግ ጥላ ስር ስለነበሩ እንካሳለን ብዬ አስብ ስለነበር ምንም አይሰማኝም ነበር። ምህረት ሲደረግላቸው እንደ ተበዳይ አዝኛለሁ።

ለምን ምህረት ኣደረገላቸው ሳይሆን፡ መንግስት እኛን አለማማከሩ፤ የሚገባንን ድጋፍ አለማግኘታችንም ያሳዝነኛል።

ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባይሰጠንም የሞራል ካሳ ሊሰጠን ይገባ ነበር። አሁንም ድረስ ስነልቦናዊ ጉዳት አለብኝ። አሁንም ድረስ ሌት ተቀን ጉዳቱ ይሰማኛል።

ይህን ስቃይ ለልጆቼም ላወርሳቸው አልፈልግም። ልጆቼን በቀል ማስተማር አልፈልግም። ይህንን ታሪክ በጭራሽ ልነግራቸውም።

ተያያዥ ርዕሶች