በሰኔ 16 ቅዳሜ ሰልፍ ላይ የታየው ክፍተት ምን ነበር?

በአዲስ አበባው የድጋፍ ሰልፍ ላይ

የፎቶው ባለመብት, YONAS TADESSE

ቅዳሜ ሰኔ 16 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለመደገፍ በተጠራው ሰልፍ ሚሊየኖች ተገኙ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በዚህ ሰልፍ ላይም የቦንብ ፍንዳታ ደረሰ።

ትናንት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘይኑ ጀማል በቅዳሜው ሰልፍ ላይ የታየው የደህንነት ክፍተት ሆን ተብሎ በፖሊስ ቸልተኝነት የተፈጠረ መሆን አለመሆኑም ይጣራል፤ በእለቱ በመድረኩና በህዝቡ መካከል ያለው ርቀት መስፋት ሲገባው መቀራረቡም እንደ ክፍተት ተወስዶ ተገምግሟል ብለዋል።።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎ የተፈጸመውን ጥቃት ማክሸፍ አለመቻሉ በእለቱ የተስተዋለ ክፍተት ነው ብለዋል።

የሆነው ምን ነበር?

ኢቲቪ እያስተላለፈ በነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድጋፍ ቀጥታ ስርጭቱ ላይ እንደታየው ጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ነው የፍንዳታ ድምጽ የተሰማው። ቀጥሎም መድረኩ አካባቢ የነበሩ ግለሰቦች ሲሯሯጡ ተስተውሏል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአደጋው በኋላ ''ኢትዮጵያውያን በፍቅር ተደምረው ፍቅር እንዲዘንብ ያደረጉበት ዕለት ቢሆንም የአገራችንን ሰላም የማይፈልጉ አካላት በተጠና እና በታቀደ መልኩ ሙያቸውን ታግዘው ይህን ደማቅ ስነ-ስርዓት ለማደፍረስ የሰው ህይወት ለመቅጠፍ እና ደም ለማፍሰስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል" ብለዋል።

የድጋፍ ሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጉደታ ገላልቻ በበኩላቸው " ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመሆን በቅንጅት ስንሰራ ነበር አሁን የተፈጠረው ግን ከደህንነት አካላት በኩል ክፍተት መኖሩን አሳይቶናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አደጋው ከደረሰ ከጥቂት ሰአት በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ለኢቲቪ በሰጡት መግለጫ " የጸጥታ ሃይሎች ብዙ ተግባር አከናውነናል ይሁን እንጂ ጥቃት አድራሾቹ ከፍተኛ ዝግጅት አድርገው ስለነበር ጥቃቱ ሊፈፀም ችሏል" ብለዋል።

ከዚህ ቃለምልልስ በኋላ ግን እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ዘጠኝ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፌደራል ፖሊስ አባላት ከስራቸው መባረራቸውን እንዲሁም በስራቸው ላይ ክፍተት በማሳየታቸው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ ተዘግቧል።

በዛኑ ዕለትም ፖሊስ 6 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልፆ ነበር፡፡

ከትናንት ጀምሮ የምረመራው ሂደት በውጭ አገር መርማሪዎች ሊደገፍ እንደሆነ ታውቋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ዘይኑ ጀማል ለቢቢሲ እንዳስታወቁትም ፖሊስ ከአደጋው ጀርባ ያሉ ግለሰቦችን ለመለየት የሚያደረገው ክትትል ቀጥሏል። ከኤፍቢአይ ጋርም በጥምረት መስራት ጀምሯል፤ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥርም 28 ደረሷል ብለዋል፡፡

አቶ ቢተው በላይ የቀድሞ ታጋይና የኢህአዴግ ምክር ቤት አባል ናቸው። በደቡብ ክልልም ከፀጥታና ደህንነት ጋር በተያያዘ ሲሰሩ ነበር።

እርሳቸው ቅዳሜ እለት ስለተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ዝግጅት ከአንዳንድ ሰዎች ጠይቀዋል። ከንግግራቸው እንደተረዱትም "አዘጋጆቹ ከፀጥታ አካላት ጋር በሚጠበቀው መንገድ ተቀናጅተው የገቡበት አይመስልም።"

አቶ ቢተው ስለዝግጅቱ ከመንግስት አካላት ጠይቆ መረዳት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው አንዳንድ ቦታዎች የፍተሻ መላላት እንደነበር ቀድመው በስፍራው ገብተው ያደሩም እንደነበሩ መነገሩ ሌላው የፀጥታው ጉዳይ መላላቱን ማሳያ ነው።

ይህንን ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም ከውጭ ሆኖ ለሚመለከተው ግለሰብ የተቀናጀ ነገር እንዳልነበር ያሳያል ይላሉ። እንዲህ አይነት ትልቅ ህዝባዊ ስብሰባዎች ሲዘጋጁ በየደረጃው ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር ከመነሻው ጀምሮ በጋራ በመሆን ማቀድ ያስፈልግ እንደነበር ያስታውሳሉ። "እንዲህ አይነት በራስ ተነሳሽነት የሚደረግ ህዝባዊ ሰልፍ ሲደረግ ፍላጎት የሌላቸው ደግሞ በዓሉን ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን ነገር ለመከላከል ዝግጅት ወሳኝ ነው" ይላሉ።

ምንም እንኳ ከመንግስት ውጭ የተዘጋጀ ሰልፍ ቢሆንም ከመንግስት አካል ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ችግር ቢከሰት እንኳ እንዴት መፍታት እንደሚቻል መታቀድ ነበረበት ይላሉ አቶ ቢተው። በአቶ ቢተው ሃሳብ እነዚህ አካላት ከመነሻው ጀምሮ አለመገናኘታቸው ክፍተቱን ፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል ይችላል።

ለአቶ ቢተው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚደረገው ጥበቃ ምን ይመስል እንደነበር ለመናገር በስፍራው የነበረ ሰው የሚታዘበው እና አስተያየት ቢሰጥበት የተሻለ እንደሚሆን ገልፀው ነገር ግን ጥበቃው በስፍራው ላይ ቀድሞ በመገኘት መጠናከር ይኖርበት እንደነበር ይገባኛል በማለት አስተያየታቸውን ያጠናቅቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ላይ የሚካሄደው ምርመራ ተጀምሯል በማለት ለቢቢሲ የተናገሩት።የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘይኑ ጀማል የምርመራውን ሂደት አስመልክቶ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በምርመራ ሂደቱ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ የተውጣጡና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን አስረድተዋል።

ምርመራው የድርጊቱን ፈጻሚ? የድርጊቱን ኢላማ? በድርጊቱ ውስጥ የፖሊስ ተሳትፎ መኖር አለመኖሩን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለመ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽነሩ በጥቃቱ ላይ የፖሊስ ተሳትፎ ስለመኖሩ የሚጣራ ነው የሚሆነው ብለዋል።

ድርጊቱ ከመድረኩ ባልራቀ ቦታ ላይ መፈጸሙም በእለቱ እንደ ክፍተት የታየ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ቦምብን ያክል መሳሪያ ብዙ ህዝብ በተሳተፈበት ሁኔታ መገኘቱ በፌደራል ፖሊስ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን ገልጸዋል።