በዚምባብዌ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በፈነዳ ቦንብ የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ

ፕሬዝዳንት ምናንጋጓ በቡላዋዮ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ በነበረበት ወቅት ቦንብ ከፈነዳ እና ሰዎች ከተጎዱ በኋላ የህክምና ባለሙያዎች በስፍራው ተገኝተው ህክምና ሲሰጡ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቅዳሜው የዚምባብዌ የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ በፈነዳ ቦንብ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ባለሥልጣኑ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንዳስረዱት ከሆነ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ሕይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

የፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋጓን ሁለት ምክትሎቻቸው ጨምሮ 49 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሐምሌ ወር ማብቂያ ላይ ከሚካሄደው ምርጫ በፊት እርሳቸውን ለመግደል የተደረገ ሙከራ እንደነበር ተናግረዋል።

ከ30 ዓመት በላይ ሥልጣን ላይ የቆዩት ሙጋቤ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ምርጫ የተደረገው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ፕሬዝዳንት ምናንጋጓ ጥቃቱ ምርጫውን አያደናቅፈውም ሲሉ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝዳንት ምናንጋጓ ቅዳሜ ዕለት ቡላዋዮ በምትባል ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ እያካሄዱ ነበር። እርሳቸው ንግግር አድርገው ከመድረክ እየወረዱ እያለ ቦንብ ፈንድቶ 41 ሰዎች ተጎድተዋል።

የሀገሪቱ ባለሥልጣናትም የደኅንነት አጠባበቁ ዳግም ይፈተሻል ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጓግ በምርጫው ያሸንፋሉ ተብሎ ሰፊ ግምት ቢሰጣቸውም ተንታኞች ግን የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ከሥልጣን በማውረዳቸው የውስጥና የውጭ ጠላቶች ማፍራታቸውን ተናግረዋል።