አዲስ አበባ የመጡት የልዑካን ቡድኑ አባላት እነማን ናቸው?

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ዑስማን ሳሊህ (ግራ) እና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረ አብ (ቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, Hadasi Er

የምስሉ መግለጫ,

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ዑስማን ሳልሕ(ግራ) እና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረ አብ (ቀኝ)

የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ።

ግንቦት 28 2010 ዓ.ም የኢህአዴግ ስራ እፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካካል ቆይቶ የነበረውን ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበትን ውጥረት ሊቀይር ይችላል የሚል ተስፋን ሰንቋል።

ዛሬ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዑስማን ሳልሕና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ በሆኑት የማነ ገብረ አብ የሚመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ዛሬ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

የልዑካኑን ቡድኑን የሚመሩት ዑስማን ሳልሕ እና የማነ ገብረ አብ እነማን ናቸው?

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ዑስማን ሳልሕ

ወደ ትጥቅ ትግሉ ከመቀላቀላቸው በፊት መምህር የነበሩት የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ዑስማን ሳልሕ በ 1978 ወደ ትግል ሜዳ ከወጡም በኋላም በመምህርነት አገልግለዋል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየች በኋላ እአአ ከ1993-2007 የትምህርት ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ከ2007 እስከ ዛሬ ድረስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው።

ለ20 ዓመታት ያክል ተቋርጦ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሃላፊነት የሚመሩትም እኝህ ሚኒስትር ናቸው።

የፕሬዚደንቱ አማካሪ አቶ የማነ ገብረኣብ

የፕሬዚደንቱ አማካሪና የፖለቲካ ፓርቲው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት የማነ ገብረኣብ በ1977 ከአሜሪካ ነበር የትጥቅ ትግሉን የተቀላቀሉት። በትግሉ ግዜ በዜና ክፍል፣ በ 'ድምፂ ሃፋሽ' ሬድዮ ጋዜጠኛም ሆነው አገልግለዋል። ከኤርትራ ነፃነት በኋላም በተለያዩ ሓላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። ከ 1994 ጀምሮ እስካ አሁን ድረስ የድርጅታቸው የፖለቲካዊ ጉዳዮች ሓላፊ ናቸው።

2017 ላይ አቶ ዑስማን ሳልሕ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ አቶ የማነ ገብረኣብ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሚያደርጓቸው ዲፕሎማሲያዊ ጉዞዎች ላይ አብረው ይጓዛሉ።