ኢትዮጵያና ኤርትራ፦ ከእራት በኋላ ምን ተወራ?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አማካሪ አቶ የማነ ገብረ አብ Image copyright EBC FaceBook Page

በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልሕና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ በሆኑት የማነ ገብረአብ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የእራት ግብዣ የተደረገላቸው ሲሆን ከእራት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት አማካሪ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ የማነ ገብረአብ አጠር ያለ ንግግር አድርገዋል።

የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ሲታወስ

የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ጦስ በሶማሊያ?

የኤርትራው ፕሬዝዳንት አማካሪ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ የማነ ገብረአብ ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው፣ "ዛሬ ስንገናኝ ከ20 ዓመት በኋላ ነው፤ ነገር ግን 20 ዓመት ተለያይቶ እንደተገናኘ አልነበረም" በማለት የተደረገላቸውን አቀባበል አድንቀዋል።

"በመካከላችን ምንም የአስተሳሰብ ልዩነት የለም። አንድ የሚያሳዝን የታሪክ ምዕራፍ ዘግተን ወደ አዲስ ምዕራፍ ገብተናል የሚል እምነት አለን" ብለዋል።

አቶ የማነ ገብረዓብ አክለውም በሁለቱ አገራት መካከል ትንንሽ ችግሮች ቢኖሩም እንኳ "በመነጋገር በመግባባት እንደምናሸንፋቸው እናምናለን" ብለዋል።

ይህንን እምነታቸውን የሚያፀናው ምን እንደሆነ ሲያስረዱም፣ "የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ቁርጥ ፍላጎትና ውሳኔ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁም "ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ፍቅርን ልዋስና በማለት ላሳያችሁን ፍቅር እናመሰግናለን" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በበኩላቸው አርቲስቶች መጪው መስከረም የምናከብረው አዲስ አበባና አስመራ ስለሆነ ከወዲሁ ዝግጅት እንድታደርጉ በማለት በእራት ግብዣው ላይ ለተገኙ የጥበብ ባለሙያዎች ጥሪ አቅርበዋል።

ምፅዋ ላይ መንሸራሸር ለናፈቃችሁ ኢትዮጵያውያን በማለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ እንደሚጀምር ተናግረዋል።

"ከኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጋር የሚያዋጣን ፍቅር ብቻ ነው" ካሉ በኋላ፣ "ፀቡን ሞክረነዋል በሁለቱም ወገን አክሳሪ ነው" ብለዋል። ጦርነት "ሰው ይበላል፤ ጊዜ ይበላል፤ ሐብት ይበላል፤ ጠቃሚ ሐሳብ ማመንጨት የሚያስችል ጭንቅላትም ይበላል" በማለት ተናግረዋል።

ለእርቅ የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ተከፍሎ ከኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጋር ተደምሮ ለማደግ ከፍተኛ ፍላጎት ያለ መሆኑንንም ተናግረዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ለሚኖረው ሰላምና ፍቅር ተባባሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኤርትራውያን ወንድምና እህቶቻችን በማለት ክረምቱ ሳያልፍ መጥተው እንዲጎበኙ አዲስ ዓመትንም አብረው እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም ሰላምና ብልፅግና ለሁለቱም ሀገራት ተመኝተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ