ዕድሜ ጠገቧ የጥድ መፃሕፍት ቤት መደብር ባለቤት አቶ ተስፋዬ አዳል

አቶ ተስፋዬ አዳል

በአሁኑ ወቅት መጽሐፍ የሚፈልግ ቢያሻው ወደ ብሔራዊ ቲያትር ካልሆነም ፒያሳ ጊዮርጊስ ማቅናት የተለመደ ነው። የጠፉ መጻሕፍትን የሚፈልግ ደግሞ ሜክሲኮ ሊወርድ ወይም መርካቶ ሊወጣ ይችላል።

የአጋጣሚ ነገር ሆኖ የመጻሕፍት ጉልቶች እጅብ ብለው ነው የሚገኙት። ከአቶ ተስፋዬ በቀር።

አቶ ተስፋዬ ጋንዲ ሆስፒታል አካባቢ አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን አጥር ጥግ በፅድ ተከርክሞ በተሠራ መጽሐፍ መሸጫ ውስጥ ተቀምጠው ለደንበኞቻቸው መጻሕፍትን ሲያከራዩና ሲሸጡ ለዘመናት ኖረዋል።

ክረምትና ንባብ

“ከወጡት ስራዎቼ ይልቅ ገና የሚወጡት ናቸው ትልቅ ቦታ ያላቸው” አለማየሁ ገላጋይ

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት ሥራ ሲጀምሩ ጋዜጣ በመሸጥ ነበር። በወቅቱ የነበሩትን እነ ታይም፣ አዲስ ዘመን፣ ኒውስ ዊክ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ሪደርስ ዳይጀስት፣ አፍሪካ ጆርናል፣ ሄራልድ ትሪቢዩን፣ የኤርትራ ድምፅ፣ የድሮዋን ቁም ነገር መጽሔት፣ ጎህን እያዞሩ ይሸጡ ነበር።

በንጉሱ ስርዓት መውደቂያ አካባቢ ከመፅሔቶቹ ይልቅ የማኦ ሴቱንግ መፃህፍቶች እየበዙ እንደመጡ ይናገራሉ። እነዚህን መጻሕፍት ከአከፋፋዮች አንዱን በ10 ሳንቲም ዋጋ ተረክበው ሲቀና መቶ ሳይሆን ሀምሳውን በአንድ ቀን ሸጠው ያድራሉ።

በወቅቱም ለነዚህ መፃህፍት ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም የተነሳ አንዳንድ የሀገር ውስጥ አሳታሚዎች የማኦ ጥቅስን የያዙ፣ የፖለቲካ የኢኮኖሚ ሥራዎችን፣ አራቱ ድርሰቶች፣ የቦልሼቪክ ፓርቲ፣ የሴቶች ጥያቄ፣ የቬትናም አብዮት የሚሉ የወቅቱን እንቅስቃሴ የሚያንፀባርቁ መጽሐፎች ብቅ ብቅ ማለት እንደጀመሩ ይናገራሉ።

እነዚህ መጻሕፍት ሲመጡ በከተማው ፈላጊያቸው ብዙ እንደነበር ከትዝታ ከረጢታቸው ፈትተው አጫውተውናል።

አቶ ተስፋዬ እና ባልደረቦቻቸው እነዚህን መጻሕፍት እያመጡ ይቸበችቡት ያዙ። ከዚህ በኋላ ደግሞ በሀገር ውስጥ የነበሩ መፃህፍት የቀድሞ ታላላቅ የሀገራችን ሰዎች የተማሩባቸው፣ ታሪክን የሚነግሩ፣ ከየትምህርት ቤቱ እና ከየድርጅቱ እየወጡ መጣል ጀመሩ።

"እነዚህ መጽሐፎች የሚጣሉና የሚወድቁ አልነበሩም" ይላሉ አቶ ተስፋዬ።

"ፍቅር እስከ መቃብር"ን በአይፎን 7?

በወቅቱ የነበረው መንግሥት ግን መጻሕፍቱ እንዲጣሉ አልያም ተሰብስበው እንዲቃጠሉ ያደርግ እንደነበር አቶ ተስፋየ ያስታውሳሉ።

የየትምህርት ቤቶቹ ርዕሳነ መምህራን ግን እነ አቶ ተስፋዬን እየጠሯቸው ሳይቃጠል ከተጣለበት እንዲወስዱ ያደርጉ ነበር። ስለዚህም እነዚህን መጻሕፍት በትንሽ ዋጋ እየገዙ መሸጥ ጀመሩ።

ያኔ እነዚህን መጻሕፍት እያዞሩ መሸጥ መዘዝ ነበረው። መጻሕፍቱ ውስጥ የጃንሆይ ምስል ከተገኘበት ያለምንም ጥያቄ አምስት ወራትን ያሳስር ነበር። ስለዚህ የጃንሆይን ምሥሎች እየፈለጉ መገንጠልና ማስወገድ የግድ ነበር።

"በመጻሕፍት የተነሳ ታስሬ አውቃለሁ"

የታሰሩበትንም ምክንያት ሲያስረዱም በደርግ ሥርዓት ውስጥ "የሹራብ ነጋዴውም፣ የካልሲ ነጋዴውም አፈሳ ተብሎ ልቅምቅም ተደርጎ ታፈሰ" በማለት ይጀምራሉ።

"መጽሐፍት ነጋዴውም ሕገ ወጥ ነው ብለው ያዙን። ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እስከ መጽሐፎቻችን ታሰርን።"

አቶ ተስፋዩ እና ሌሎች መፃሕፍት ሻጮች ለ15 ቀን ያህል በእስር ሳሉ ደራሲ ማሞ ውድነህ ለግል ጉዳያቸው ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ይመጣሉ። በሩ ላይ መጽሐፍ ተደርድሮም ያያሉ።

ቀዩን ረዥሙን ደራሲ ማሞ ውድነህን ፖሊሱ አላወቃቸውም ነበር።

ጋሽ ማሞ 4 ሰዓት ላይ በእጃቸው ላይ የሆነች ወረቀት ይዘው ነው ወደ ስድስተኛ የገቡት። ቀና ብለው ሲያዩ መጽሐፍ ተደርድሯል።

አቶ ማሞ ለካ መጀመርያ መጽሐፉን ሲያዩ ለእስረኞች እንዲያነቡት የመጣላቸው ነው የመሰላቸው።

"ዛሬስ ለእስረኞቻችሁ መጽሐፍ ቤት ከፈታችሁ እንዴ?" በማለት እንዳደነቁ አቶ ተስፋዬ ይናገራሉ።

የጥበቃ ጓዱ ከመጻሕፍት ነጋዴዎች ጋር አብረው የታሰሩ መጻሕፍት እንደሆኑ አስረዳቸው።

ማሞ ውድነህ ሐዘን ገባቸው።

በተለይም የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን መፃሕፍትን፣ እነ ፍቅር እስከ መቃብር፣ እነ ከአድማስ ባሻገር፣ የከበደ ሚካኤል፣ የራሳቸው የማሞ ውድነህ...እነዚህ ሁሉ መጻሕፍት ታስረውና ያለፍርድ እዛ ተቀምጠው ሲመለከቱ ማሞ ውድነህ ከፋቸው።

በዚህን ጊዜ አቶ ማሞ ከጥበቃ ጓዱ ጋር እሰጥ አገባ ገጠሙ። የጣቢያውን አዛዥም ቢሮው ገብተው ጎትተው በማምጣት ከመፃሕፍቱ ክምር ጋር አፋጠጡት። አዛዡ አላወቅኩም ብሎ ካደ።

"ወቅቱ በራሪ ወረቀት የሚበተንበት ስለነበር..." ይላሉ አቶ ተስፋዬ፣ ማሞ ውድነህ በራሪ ወረቀት በእጃቸው እንዳይገኝ መክረው በሌላ ጉዳይ ግን ከጎናቸው መሆናቸውን ጠቅሰው የጣብያው አዛዡንም የመጻሕፍት ሻጮቹን ዳግመኛ እንዳይታሰሩ አደራ ብለው አስፈቷቸው።

አቶ ተስፋዬም መጻሕፎቻቸውን ይዘው ወደ መሸጫቸው አመሩ።

መጽሐፍን እንደ ጉቦ

ከዚያ በኋላም ቢሆን አቶ ተስፋዬ መጽሐፍ ሲሸጡ ከአብዮት ጥበቃ ጋር እየታገሉ እንደነበር አይዘነጉም። ልክ እንደዛሬዎቹ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ሁሉ ያኔም አብዮት ጥበቃ ሲመጣ መጽሐፎቻቸውን ሰብስበው እየሮጡ፣ ዞር ሲል ደግሞ እየዘረጉ በዚሁ ንግድ ላለፉት 30 ዓመታት ኖረዋል።

አቶ ተስፋዬ መጽሐፍን እንደጉቦ ለአብዮት ጥበቃዎቹ ይከፍሉ እንደነበር አይዘነጉትም። "ለልጆቻቸው እንዲያነቡ እያልን እንሰጣቸው ነበር።" ይላሉ።

አቶ ተስፋዬ አብረዋቸው ይሸጡ የነበሩ ሰዎች በተለያየ ምክንያት እየተንጠባጠቡ እርሳቸው ብቻ እንደቀሩ ያወሳሉ።

እርሳቸው ብቻቸውን ሲቀሩ ደግሞ የአብዮት መጽሐፍ ተፈላጊነት እየቀነሰ መጣ። የነማኦ ሴቱንግ፣ የነካርል ማርክስ መጻሕፍት አንባቢ አጥተው ማዛጋት ጀመሩ።

መንግስትም አድሃሪያን ኢምፔሪያሊስቶች ሲል አወገዘ። አንዳንድ ወጣቶች ግን ሹልክ እያሉ እየመጡ ይገዟቸውም ይሸጡላቸው ነበር።

ፖስታ ቤት አንድ ግሪካዊ ሚስተር ጃኖቡለስ የሚባል አከፋፋይ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ተስፋየ እርሱ መጽሐፍትን እያሾለከ ይሸጣቸው ነበር።

የሶሻሊስት መጻሕፍት እየከሰሙ ሲመጡ በፊት ገዝተው ያነቡ የነበሩ ሰዎች እርሳቸው ጋር እያመጡ ይሸጡላቸዋል።

አንባቢም የጠፋ መጽሐፍ ሲፈልግ እርሳቸው ጋር መምጣት ጀመረ።

እንዲህ እንዲህ እያሉ አቶ ተስፋዬ ያኛውን ትውልድ ከዚህኛው ጋር በንባብ ያጋመዱ ሆነው እስካሁን ዘለቁ።

በተከረከመ ጥድ የተሸፈነው መደብራቸው ለልማት በሚል የፈረሰ ሲሆን ይህ የአቶ ተስፋዬ መፈናቀል በርካታ መፃህፍት አፍቃሪን ያሳዘነ ጉዳይ ነው።

የዘመናት ደንበኞቻቸው በተለይም ወጣቶች ጉዳዩን ወደ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በመውሰድ ትኩረት እንዲያገኝ አድርገዋል።

አብይ ታደሰ ከነዚህ መካከል አንዱ ነው።

እርሱ እንደሚለው የአቶ ተስፋዬ ታሪካዊዋ የጽድ መደብር እንድትፈርስ የሆነው በመንገድ ሥራ ምክንያት ነው።

አቶ ተስፋዬን ከድሮ ጀምሮ ያውቃቸው እንደነበር የሚናገረው አብይ፣ ወዳጆቻቸው ባደረጉት ርብርብ መንግሥት በዚያው አቅራቢያ የቆርቆሮ መደብር እንዲያዋቅሩ ፈቅዶላቸዋል። እነ አብይም ይህንኑ በማስተባበር ላይ ናቸው።

"እርሳቸው ከሰጡት አገልግሎት አንፃር ይህ ሲያንሳቸው ነው" ይላል አብይ።

"ለምሁሩ፣ ወጣቱ እንዲሁም ለከተማው አንባቢ ዕድሜያቸውን የሰጡ እኚህን ሰው እንዴት መጽሐፍ መሸጫ ሥፍራ ያጣሉ" ሲልም ይጠይቃል።

እንደ አብይ ሁሉ ሃወኒ ደበበም ከልጅነቷ ጀምሮ የማንበብ ሱሷን ያስታገሰችው ወደ እርሳቸው ጋር በመምጣት ነበር።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ መጻሕፍት ማንበብ ስትፈልግ ጓደኞቼና መምህሮቿ በጠቋሟት መሰረት አቶ ተስፋዬ ጋር እየመጣች ትከራይ ነበር።

"ያኔ የእንግሊዘኛ መጽሐፍ አይሸጡም ነበር" ትላለች።

አሁን የአቶ ተስፋዬን የዘመን ውለታ ለመመለስ ከሚጣጣሩ ወጣቶች መሐል አንዷ ሆናለች።

ዓውደ ርዕይ በማዘጋጀትና በልዩ ልዩ ዘዴዎች ገቢ በማሰባሰብ ያቺን ታሪካዊ መጻሕፍት መደብር ወደ ሥፍራዋ ለመመለስ እየሞከረች ነው። በጽድ እንኳ ባይሆንም በቆርቆሮ!

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ