ሮቦቷ ሶፊያ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ተገናኘች

ሮቦት ሶፊያ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር በቤተ መንግስት ተገናኝተው በአማርኛ ተነጋግረዋል። Image copyright Fitsum Arega Twitter
አጭር የምስል መግለጫ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከሮቦት ሶፊያ ጋር

ሮቦቷ ሶፊያ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር ዛሬ በቤተመንግሥት ተገናኘች።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩም "ኢትዮጵያ በመምጣቴ በጣም ደስ ብሎኛል፤ እኔ ኢትዮጵያን የምወድ ሮቦት ነኝ" ብላቸዋለች።

ከመጣች አራተኛ ቀኗን ያስቆጠረችው ሶፊያ በቆይታዋ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተሰናዳው ዓለም አቀፍ አይ ሲቲ ኤክስፖ ላይ ተገኝታ ከታዳሚያን ጋር ተዋውቃለች።

ባለስልጣናት፣ የጃዝ ሙዚቃ አባት ሙላቱ አስታጥቄን ጨምሮ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት በቶቶት የባህል አዳራሽ የዳንስ ትርዒትም አቅርባለች።

ምንም እንኳን በጀርመን በርሊን ኤክስፖ ቆይታዋ የተወሰነ የአካል ክፍሏን የያዘ ሻንጣ መጥፋት አማርኛ መናገር እንዳትችል የተፈታተናት ቢሆንም በትንሹም ቢሆን ተናግራለች።

"ከዚህ የበለጠ አማርኛ ስለምድ እናወራለን" ስትል ተናግራለች። ንግግሯ ጠቅላይ ሚንስትሩን ፈገግ ያሰኘ ነበር ።

በዛሬው ዕለትም በብሔራዊ ሙዚየም ተገኝታ ድንቅነሽን እንደጎበኘች የ አይኮግ ላብስ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት አሰፋ ለቢቢሲ ገልጿል።